በኡጋንዳ የተከሰተው ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ቢያንስ 16 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኡጋንዳ ሰሜን ምሥራቃዊ ግዛት ካራሞጃ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ 16 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
በአካባቢው ሰብል ከሚዘራበት ከሚያዝያ ወር መጀመሪያ አንስቶ ዝናብ ባለመዝነቡ ወይም በቂ ዝናብ ባለማግኘታቸው ሰብላቸው እንደወደመባቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ባለሙያዎች በአካባቢው ለሚከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ የአየር ንብረት ለውጥን፣ በቂ ዝናብ አለመኖርን፣ የደን መጨፍጨፍን፣ ከመጠን በላይ ደጋግሞ ማረስን እና የሰብል ተባዮችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
እነዚህም ተደማምረው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለከፋ ረሃብ አጋልጠውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ እንዳሉት የተከሰተው ድርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ያለ ምግብ አስቀርቷል።
በመሆኑም ቢሯቸው በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል ተጨማሪ የምግብ ግዥን ለማጸደቅ ሰኞ ለካቢኔው እንደሚያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እያከፋፈለ እንደሆነም ገልጿል።
በቆሎ፣ ማሽላ እና አኩሪአተር በብዛት የሚመረቱቸባው አካባቢዎች በድርቁ ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን ከፍተኛ ምርት የማግኘት ተስፋን አጨልሟል።
ባለሙያዎች በተሻለ የአየር ትንበያ፣ የመስኖ ግንባታ እና ድርቅን በሚቋቋሙ ሰብሎች ላይ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
ከፊል በረሃማ የሆነው የኡጋንዳ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ከዚህ ቀደምም በከፍተኛ ድርቅ ተመትቷል።
ከአራት ዓመታት በፊት በአካባቢው በረሃብ እና ከረሃብ ጋር ተያያዥ በሆኑ በሽታዎች ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ተቋም ሪፖርት አመልክቷል።
ይህንን ተከትሎ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ኦኬሎ ኦርይም፣ በረሃብ የሞቱት ሰዎችን " ሞኞች' ካሉ በኋላ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።
የቀድሞ ሚኒስትሩ፣ ኡጋንዳ ተስማሚ የሆነ አየር ንብረት እና ለም መሬት ስላላት ሰዎች የራሳቸውን ምግብ ማምረት ይገባቸዋል በማለት ነበር የድርቅ ተጎጂዎቹን " ሞኞች" ሲሉ የጠሯቸው።
" በኡጋንዳ በረሃብ የሚሞቱ ሰዎች ሞኞች ብቻ ናቸው፤ ትክክለኛ ሞኞች" ሲሉ በወቅቱ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
" ጠንክራችሁ ከሠራችሁ በኡጋንዳ መሬት አለ። የአየር ንብረት ለውጥ ቢኖርም አየሩ ተስማሚ ነው። ጠዋት ተነስታችሁ ለማረስ፣ ለመዝራት እና ለመንከባከብ ጥረት ካደረጋችሁ እንዴት ምግብ ለማግኘት ይሳናችኋል?" ብለዋል።
በወቅቱ በሰሜን ምሥራቃዊ የአገሪቷ ክፍል በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከሞቱት በተጨማሪ "ለከፋ ረሃብ የተዳረጉ" ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን የኡጋንዳ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።















