ኢራን ሠራዊቷ መጠናከሩን ስትገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ የኢራን መንግሥት መሠረቱ ተናግቷል አለች
ኢራን የጦር ሠራዊቷ ከጦርነቱ በኋላ የበለጠ መጠናከሩን ስትገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ የኢራን መንግሥት ክፉኛ ተዳክሞ ሊወድቅ መቃረቡን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።
የኢራን ሠራዊት የተኩስ አቁም በተደረገበት ጊዜ በሁሉም መስኩ ለውጊያ ዝግጁ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የአብዮታዊው ዘብ ቃል አቀባይ ገለጹ።
ሁሴን ሞሄቢ እንደተናገሩት "በተኩስ አቁሙ ወቅት የሠራዊታችን ተልዕኮ የመፈጸም አቅም ጨምሯል፣ በተፈጠረው ዕድልም የውጊያ አቅሙ፣ ጥንካሬው፣ ዝግጁነቱ እና አደጋን የመቋቋም ብቃቱ ተጠናክሯል። በአሁኑ ወቅትም ጦሩ ቀደም ሲል ከነበረው አቋም በተሻላ ሁኔታ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የኢራን መንግሥት በደረሰበት ጥቃት መሠረቱ መናጋቱን እና መውደቁ የማይቀር መሆኑን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የዚህ የሽብር አገዛዝ መሠረቱ ተናግቷል” በማለት “አገዛዙ ከዚህ በኋላ ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ ፈጽሞ አይመለስም፤ መውደቁ እንደማይቀር እነግራችኋለው” ሲሉ የኢራን መንግሥት መዳከሙን አመልክተዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን አስተያየት የሰጡት የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በተመሳሳይ እስራኤል ክፍኛ መዳከሟን ከተናገሩ በኋላ ነው።
ጠቅላይ መሪው በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት “አስራኤል መጪዎቹን 15 ዓመታት አታይም” በማለት ትጠፋለች የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
እስራኤል በኢራን ላይ ሁለት ጊዜ ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፣ ኢራን በበኩሏ ከባድ የአጸፋ ምላሽ በሚሳዔሎች እና በድሮኖች ፈጽማለች።
ባለፈው የካቲት እስራኤል ከአሜሪካ ጋር አብራ በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።
ኢራንም በበኩሏ በእስራኤል እና በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ ተከታታይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም ከባድ ጉዳትን አድርሳለች።