ቀጥታ, የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

የቀድሞው ኢራን አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም፤ ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል። እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካዊው የቀይ ካርድ ቅጣት ተግባራዊ አለመሆን ከባድ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፊፋ ፕሬዝዳንት ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ የተቀለበሰው የቀይ ካርድ ቅጣት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ላይ ከባድ ተቃውሞ ቀስቅሶበታል።

    ፊፋ የአሜሪካዊውን የቀይ ካርድ ቅጣት ማንሳቱ የእግር ኳስ ጨዋታ ተአማኒነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት የአውሮፓ አገራት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዩኤፋ ተቃውሟል።

    አሜሪካ ከቦሲኒያ ኤርዜጎቪና ጋር በነበራት ጨዋታ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ የተሰናበተው አሜሪካዊ ተጫዋች ፎላሪን ባሎገን አገሩ ከቤልጂየም ጋር ማክሰኞ በምደታርገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ መሰለፍ አይችልም ነበር።

    ይህንን ውሳኔ የአውሮፓ እግር ኳስ ፌዴሬሽን “ያልታየ፣ ለመቀበል አስቸጋሪ እና ምክንያታዊ ያልሆነ” በማለት ፊፋ በውሳኔው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ቅጣቱን ማገዱ “ቀይ መስመር ያለፈ” ነው ሲል ተችቶታል።

    የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ፊፋ ለአሜሪካ ዋነኛ ግብ አስቆጣሪ በሆነው ተጫዋች ላይ የተላለፈውን የቀይ ካርድ ቅጣት ወዲያውኑ ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረግ በቀጣዩ ወሳኝ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ እንዲሳተፍ ዕድል ፈጥሮለታል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ቴሌቪዥን እንዳረጋገጠው ተጫዋቹ በቀጣይ ግጥሚያ ላይ እንዲሰለፍ የሚያደርገው ውሳኔ የተሰማው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

    ከዚያም በኋላ እሁድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ትልቅ ኢፍትሐዊነት” ያሉት የቀይ ካርድ ቅጣት “በመቀልበሱ” ፊፋን አመስግነዋል።

    ማክሰኞ ከአሜሪካ ጋር የሚገጥመው የቤልጂየም እግር ኳስ ማኅበር የፊፋን ውሳኔ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አሜሪካዊው ተጫዋች በቀጣይ ግጥሚያ ላይ እንዲሳተፍ በመፈቀዱ “መገረሙን” ገልጿል።

    የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ፕሪቮት “ለዚህ ተቀባይነት ለሌለው ውሳኔ ስልክ መደወል ምክንያት ከሆነ፣ የእግር ኳስን እና የስፖርትን መሠረታዊ ደንብን በግልጽ መጣስ ነው” በማለት ተቃውመዋል።

    ከሙስና ጋር በተያያዘ በአሁኑ የፊፋ ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ከ10 ዓመት በፊት የተተኩት ሴፕ ብላተር በኤክስ ላይ ጉዳዩን በተመለከተ “እግር ኳስ የፖለቲካ ኃይል የመጫወቻ ሜዳ ፈጽሞ መሆን የለበትም” ሲሉ ጽፈዋል።

    የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር አንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ ሲያገኝ ቀጣይ ጨዋታ ላይ እንዳይሰለፍ የሚጣለው ቅጣት “በፍላጎት የሚፈጸም ምርጫ ሳይሆን ደንብን መሠረት ደያረገ መርኅ ነው” ብሏል።

    የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር እና ፊፋ ባለፉት ወራት በበርካታ ጉዳዮች ሲወዛገቡ የቆዩ ሲሆን፣ ሶማሊያዊው ዳኛ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ሲከለከል ማኅበሩ ተቃውሞውን ለማሳየት ዳኛው የአውሮፓ ጨዋታን እንዲዳኝ ጋብዞታል።

  2. ሐማስ በጋዛ ያለውን አስተዳደር ማፍረሱ ተገለጸ

    ሐማስ ላለፉት ሁለት አሥርታት የነበረውን የጋዛ አስተዳደር ማክሰሙ ተገለጸ። ውሳኔው በጋዛ ሰርጥ የሲቪል አስተዳደር ለመዘርጋት መንገድ የሚከፍት ፖለቲካዊ እርምጃ ነው ተብሏል።

    ሐማስ በአውሮፓውያኑ 2007 ከፋታህ ፓርቲ የጋዛ ሰርጥ አስተዳደርን ከተረከበ አንስቶ በአመራር ላይ ይገኛል። ቀደም ብሎም የፍልስጤም የምክር ቤት ምርጫንም አሸንፏል።

    ሐማስ እና እስራኤል ባለፈው ጥቅምት የተኩስ አቁም ላይ ከደረሱ ወዲህ ሐማስ ከጋዛ ሰርጥ የዕለት ከዕለት አስተዳደር ለመውጣት ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። የሐማስ የትጥቅ መፍታት ጉዳይ ግን እስካሁን እልባት አላገኘም።

    የሐማስ አስተዳደር የመረጃ ክፍል ኃላፊ ለኤኤፍፒ “የአስተዳደሩ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ ኃላፊ መሐመድ ፋራ በይፋ መልቀቂያ አስገብተዋል” ብለዋል።

    “ለጋዛ ብሔራዊ ኮሚቴ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማስተላለፍም ኮሚቴውን ለማፍረስ ተወስኗል” ሲሉም አክለዋል።

    የጋዛ ብሔራዊ አስተዳደር ኮሚቴ አሁን መቀመጫውን ካይሮ ያደረገ ሲሆን፤ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ኮሚቴ የተቋቋመ ነው።

    የትራምፕ የሰላም ልዑካን በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2025 የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማሸማገላቸው ይታወሳል።

    የሐማስ ቃል አቀባይ “ሐማስ አዲስ በወሰደው እርምጃ መሠረት ከዚህ በኋላ የጋዛ ሰርጥን በማስተዳደር ኃላፊነት ውስጥ የለበትም። ይህም ለወራሪዎቹን እና ለማጥፋት ዘመቻቸው ሰበብ ላለመስጠት ነው” ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

  3. በመቶ ሺህዎች እየታደሙበት ያለው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሽኝት

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጀመረው እና በቀጣይ ቀናትም የሚካሄደው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት በመቶ ሺህዎች እየታደሙበት ቀጥሏል።

    ኻሜኒ ከአብዮታዊዋ እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን መሪነታቸው በተጨማሪ በሺዓ እስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው መሪ ነበሩ።

    የቀድሞው መሪ የስንብት ሥነ ሥርዓት ከኢራን በተጨማሪ በኢራቅ ውስጥ የሚከናወን ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይታደማሉ ተብሏል።

    አስካሁን በኢራን ውስጥ የተካሄደውን ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ የተወሰኑ ምሥሎች እነሆ...

  4. ኢራን ለአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ "ፍትሕ እንደምትፈልግ" የጦር አዛዧ ተናገሩ

    የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ የሆኑት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፤ አገሪቱ ለግድያው ፍትሕ እና ተጠያቂነትን ለማግኘት ጥረቷን እንደምትቀጥል የኢራን ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሐታሚ ተናገሩ።

    “ወንጀሉን የፈጸሙት ወገኖች የኢራን ሕዝብ እንባ፣ ሁላችንም ፍትሕ መጠየቃችንን ፈጽሞ እንደማናቋርጥ ሊያውቁ ይገባል” በማለት የጦር አዛዡ መናገራቸውን የኢራን ዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።

    ጨምረውም “ውጤት አስክናገኝ ድረስ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ውሳኔያችን ግልጽ ነው። ጥቃት ፈጻሚዎቹን እንዲሁ አንተዋቸውም” በማለት በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የጠቅላይ መሪው ደም በከንቱ ፈስሶ እንደማይቀር አመልክተዋል።

    ሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለክብር፣ ለነጻነት እና ለብሔራዊ ኩራት ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ጄነራሉ፤ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች “ያለምንም ማወላወል በቆራጥነት እና በጀግንነት” የአዲሱን እስላማዊ አብዮታዊት ኢራን ጠቅላይ መሪ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሞጅታባ ኻሜኒ አመራርን እንደሚከተል ገልጸዋል።

    ጄነራሉ አዲሱን መሪ ባገኙበት ጊዜ “የኢራን ሕዝብ እና መንግሥት ወንጀሉን የፈጸሙት እንዲሁ እንደማይተዋቸው ነግሬያቸዋለሁ” በማለት ለሞጅታባ ኻሜኒ የገቡትን ቃል አስታውሰዋል።

  5. በአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚታየው ቀይ ባንዲራ ምንድን ነው?

    ለቀናት በሚዘልቀው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እየተገኘ ሲሆን በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ከኢራን ባንዲራ ይልቅ ሐዘንተኞቹ ቀይ ባንዲራ ይዘው በስፋት ይታያሉ።

    ሐዘንተኞቹ በጠቅላይ መሪው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ቀይ ቀለም ያለው ሰንደቅ ዓላማ ወይም ረጅም ባነር መያዛቸው በሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ቀዩ ባንዲራ ያለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። ይህም የሟቹን መሪ ደም መበቀል አስፈላጊ መሆኑን ለማመልከት ነው።

    በተጨማሪም ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ጽሁፍ የሰፈረባቸው ቀይ ጨርቆች በስፋት የሚታዩ ሲሆን ጽሁፉ ለኻሜኒን ግድያ በቀል ጥሪ የሚያርቡ ናቸው።

    በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩት ቀይ ባንዲራዎች ሰማዕትነትን፣ ለንጹኃን ግድያ ፍትሕ አለማግኘትን፣ እንዲሁም ለበቀል ሃይማኖታዊ ቃል መግባትን ያመለክታል። ይህ ቀይ ባንዲራ በአጥቂዎች ላይ የበቀል አጸፋ ሲመለስ ወይም በፍርድ ፍትሕ አስኪገኝ ድረስ እየተውለበለበ ይቆያል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት መጨረሻ በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱ ጊዜ በመጀመሪያው ቀን በፈጸሙት ጥቃት ጠቅላይ መሪው አሊ ኻሜኒ፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መገደላቸው ይታወሳል።

    ኢራንን ወደ 40 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጠቅላይ መሪነት ያስተዳደሩት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከአገሪቱ ባሻገር በሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ የሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራቸው።

    ከቅዳሜ ጀምሮ አስከ ሐሙስ ድረስ የሚቆየው የኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከኢራን ባሻገር በጎረቤት አገር ኢራቅ ውስጥም ይካሄዳል። የጠቅላይ መሪው አስከሬን ወደ ኢራን የሚወሰድ መሆኑም ተነግሯል።

  6. የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

    የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል።

    እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

    መጋቢት ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ አንስቶ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒን የጤና ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ይናፈሳሉ። አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት እርሳቸውም እንደተጎዱ ይነገራል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ እስከሞቱበት የካቲት ወር ድረስ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ መርተዋል።

    አርብ ዕለት የተጀመረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ይፋዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዚህ ሳምንትም በተለያዩ የኢራን እና ኢራቅ አካባቢዎች መካሄድ ይቀጥላል።

    የኢራን ባለሥልጣናት “የክፍለ ዘመኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት” ሲሉ በገለጹት በዚህ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ12 እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች ይገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ሰዓት የኻሜኒ አስከሬን ቴህራን ውስጥ በሚገኘው ግዙፉ መስጊድ ግራንድ ሞሳላ ውስጥ ተቀምጧል።

    እሁድ ዕለት በመላው ኢራን ክብረ በዓል ሆኖ የታወጀ ሲሆን አስከሬኑ ከመስጊዱ እንደሚወጣ እና ዛሬ ሰኞ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

    የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በጥንቃቄ የተሰናዳ ነው። በሥነ ሥርዓቶቹ ላይ የሞጅታባ ኻሜኒ አለመገኘት የተስተዋለው እስራኤል ልትገድላቸው ትፈልግ ይሆናል የሚል ስጋት ባደረበት በዚህ ወቅት ነው።

    ተፋላሚዎቹ አገራት በገቡበት ጠንካራ ያልሆነው ተኩስ አቁም ምክንያት ጦርነቱ ጋብ ብሎ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ንግግር ቀጥሏል።

    ይሁን እንጂ አሜሪካም ሆነ ኢራን ወታደራዊ እርምጃ ውስጥ በድጋሚ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እስከሚጠናቀቅ ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር እንዲቆም መደረጉን ለአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ተናግረዋል።

    አሜሪካ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙትን የኢራን ከፍተኛ አመራሮች “በአንድ ጥይት” ልትገድላቸው እንደምትችልም መናገራቸውን አክሲዮስ አስነብቧል። ። ነገር ግን "ይህንን አናደርግም፤ ምክንያቱም ከዚያ የምንደራደረው ሰው አይኖርም" ብለዋል።

    ትራምፕ ሕዝቡ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ ይጠላቸዋል ብለው ያስቡ እንደነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ኢራናውያን ሲያለቅሱ በመመልከታቸው እንደተገረሙ ተናግረዋል።

    በቴህራን በተደረገው ሽኝት ላይ ታዳሚዎች 'ሞት ለትራምፕ' ሲሉ እንደነበር እንዲሁም ሞሐማድ ረሱሊ የተባሉ ገጣሚ ከጸሎት ሥነ ሥርዓት በፊት “ትራምፕን መግደል የእኛ ኃላፊነት ነው” የሚል ግጥም ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ዘ ጋርዲያን ዘግበዋል።