በየመን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች ወሳኝ ወደ ሆነች ከተማ እየገሰገሱ መሆኑ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, AP
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች በየመን ደቡብ ምዕራብ አካባቢ በርካታ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘገበ።
ታጣቂዎቹ በሳዑዲ የሚደገፈውን እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የየመን መንግሥት ወታደሮችን በማጥቃት በአካባቢው ወሳኝ ወደ ሆነች ከተማ ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል።
እሁድ ዕለት የየመን መንግሥት ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በታጣቂዎቹ ላይ ማወጁን በገለፀ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቱርባህ የተባለችውን ከተማ ተቆጣጥረዋል።
ከአራት ዓመታት የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ በሳዑዲ አረቢያ እና በሁቲዎች መካከል ዳግም ግጭት አገርሽቷል።
ቱርባህ የዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው መንግሥት መቀመጫ የሆነችውን ኤደን እና ታኢዝ የተባለችውን የየመን ሦስተኛ ትልቅ ከተማ የሚያገናኝ መንገድ ላይ ትገኛለች።
ታኢዝን ከሁቲዎች ለመከላከል የሚሰማሩት ወታደሮች መቀመጫቸውን ያደረጉት በኤደን ከተማ ነው።
ቀደም ሲል የሁቲ ታጣቂዎች የየመን ሦስተኛ ትልቅ ከተማ ታኢዝ አቅራቢያ የሚገኙ መንደሮችን እና አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ከተማዋን ለመክበብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተዘግቧል።
ከመስከረም ወር ቀደም ባሉት ጊዜያት በቀይ ባሕር ምዕራብ ዳርቻ የሚገኙ የባሕር ዳርቻዎችን መያዛቸው ይታወሳል።
ሞክሃ እና በርከታ የቀይ ባሕር ደሴቶችን በቁጥጥራቸው ስር ያስገቡት ታጣቂዎቹ፣ ከተማዋን የሚይዙ ከሆነ በየመን በኩል የሚገኘውን ባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥን ለመቆጣጣር ያስችላቸዋል ተብሏል።
ባብ አል ማንዳብ የዓለም 12 በመቶ ንግድ የሚተላለፍበት መስመር ነው።
እሁድ ዕለት በሳዑዲ የሚደገፈው የየመን መንግሥት ታጣቂ ቡድኑ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል።



