ኢራን የብሪታኒያ ጦር ሠፈሮች “ሕጋዊ ዒላማ” ናቸው ማለቷን ተከትሎ ዩኬ “ራሷን ለመከላከል ዝግጁ” መሆኗን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢራን የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሠፈሮች ለአሜሪካ ጥቃቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለሆነ “ሕጋዊ ዒላማ” እንደሆኑ መግለጿን ተከትሎ፤ የብሪታኒያ መንግሥት "ራሱን ለመከላከል 24/7 ዝግጁ" መሆኑን አስታወቀ።
ዩናይትድ ኪንግደም የአሜሪካ ሠራዊት አባላት እና አውሮፕላኖች ለሚወስዷቸው "የመከላከል" እርምጃዎች የጦር ሠፈሯን እንዲጠቀሙ ፈቅዳለች። ጦር ሠፈሮቹ ኢራን ላይ ለሚደረጉ የማጥቃት እርምጃዎች እንዲያገለግሉ ግን ፍቃድ አልሰጠችም።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ዩናይትድ ኪንግደም የአሜሪካ ጦርነት “ተባባሪ ነች” ሲል ከስሷል። የኢራን እስላማዊ አብዮት ጠባቂ ዘብ በበኩሉ ለአሜሪካ ጦር ድጋፍ የሚያቀርብ ማንኛውም አገር ለሚከተለው “መዘዝ እና ውጤት ኃላፊነቱን ይወስዳል” ብሏል።
ሁለቱ አገራት እዚህ ውዝግብ ውስጥ የገቡት፤ አሜሪካ ለ12ተኛ ተከታታይ ምሽት ኢራን ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ለሚያደርጉት ጦርነት ድጋፍ አልሰጡም በማለት የሚወቅሷቸውን የብሪታንያ መንግሥትን እና የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርን በተደጋጋሚ ሲተቹ ቆይተዋል። ኢራን ትናንት ሐሙስ ያወጣችው መግለጫ በአንጻሩ ዩናይትድ ኪንግደም የጦርነቱ አጋር እንደሆነች አድርጎ የሚያሳይ ነው።
አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱት ጦርነት ከተጀመረ ከቀናት በኋላ መጋቢት ውስጥ ዋሽንግተን እንደ በግሎስተርሻየር የሚገኘው ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ እንዲሁም በሕንድ ውቅያኖስ ያለው ዲዬጎ ጋርሲያ ያሉ የብሪታንያ የጦር ሰፈሮችን እንድትጠቀም ፈቃድ ተሰጥቷታል።
እነዚህ ጦር ሠፈሮች የተፈቀዱት አሜሪካ በፋርስ ባህረ ሰላጤ አገራትን እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚያልፉ መርከቦችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ የሚውሉ የኢራን ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ እንድታደርግ ነበር።
በፈቃዳቸው ከሥልጣን የተለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር የተኩት አንዲ በርንሃም፣ ከአሜሪካ ጋር የተደረገው ስምምነት ስለመራዘሙ የተገለጸላቸው ሲሆን በቀድሞው አስተዳደር የተላለፈውን ይህንን የብሪታኒያ ውሳኔም አልቀየሩም።
ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ሐሙስ ዕለት የወጣው መግለጫ፤ ከቀናት በፊት የተፈጸመው የአሜሪካ የድብደባ ተልዕኮ የተነሳው ከብሪታኒያው ጦር ሠፈር ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ እንደሆነ ገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት ኢራን ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች አገሪቱ ጦር ሠፈሮች ጥቅም ላይ ውለው እንደሆነ አስተያየት አልሰጠም።
ለኢራን ዛቻዎች ምላሽ የሰጡት የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ “ጦር ኃይሎቻችን የዩናይትድ ኪንግደምን ደኅንነት በመሬታችንም ሆነ በውጭ አገራት ከሚፈጸሙ ከማንኛውም ጥቃቶች ለመጠበቅ ዝግጁ ናቸው” ብለዋል። ዩኬ ራሷን ለመከላከል በቀን 24 ሰዓት በሳምንት ሰባት ቀናት ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል።



















