የትራምፕን ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ከ10 በላይ ኩባንያዎች በወር ከ100,000 ዶላር በላይ ይከፍላሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images
ከ10 በላይ ኩባንያዎች አወዛጋቢ በሆነው እና በፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለቤትነት በተያዘው "ትሩዝ ሶሻል" ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጠፉ እና የፋይናንስ ገበያዎችን ሊነኩ የሚችሉ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት መመዝገባቸው ተገለጸ።
ትሩዝ ኤፒአይ የተባለው ይህ አገልግሎት በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ የተጀመረ ሲሆን ኩባንያዎቹ ከማኅበራዊ ሚዲያ ድረ ገጹ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካውንቶች የሚጋሩ መረጃዎችን ቀድመው እንዲያዩ ያስችላቸዋል።
የመጀመሪያዎቹ ደንበኞቹ በአብዛኛው ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚያካሂዱ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ለአገልግሎቱ በወር ከ60,000-100,000 ዶላር እየከፈሉ እንደሆነ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኬቨን ማክጉርን ተናግረዋል።
ኃላፊው ይህንን ያሉት የትራምፕ ሚዲያ በሚያዝያ እና ሰኔ ወራት መካከል 238 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰበት ካስታወቀ በኋላ ነው።
የትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው የሩብ ዓመቱ ኪሳራ ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከተዘገበው በ10 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ቡድኑ የክሪፕቶከረንሲ ምንዛሬን ጨምሮ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ግንኙነት በሌላቸው ንግዶች እየተሰማራ ነው።
እስካሁን ትርፍ አለማስመዝገቡን ያስታወቀው ይህ የትራምፕ ኩባንያ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በሐምሌ ወር የዎል ስትሪት ኩባንያዎች እና ባለሀብቶች ትራምፕ በቋሚነት መረጃዎችን በሚያጋሩበት ትሩዝ ሶሻል ላይ ልጥፎችን በፍጥነት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ይህ መረጃ፣ ተመዝጋቢዎች በአክሲዮኖች እና በሌሎች ግብይቶች ላይ ብልጫ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደ አንድ አማራጭ መንገድ ተደርጎ ይቆጠራል።
ይህ እርምጃ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ቤተሰብ ዋና ባለአክሲዮን በሆነበት ኩባንያ ከራሱ ልጥፎች ትርፍ እንዲያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ የሕግ እና የሥነ ምግባር ጥያቄዎችን አስነስቷል።
የትራምፕ ሚዲያ ሰኞ ዕለት ይፋ ባደረገው የገቢ ማሳወቂያ ላይ ይህ አገልግሎት "ለኩባንያው አዲስ የገቢ ምንጭ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል" ብሏል።
ኩባንያው አገልግሎቱ "ትርጉም ያለው" እና "ዘላቂ" የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ያምናል።
ይህም የኩባንያውን ሰፊ የሚዲያ ስትራቴጂ ማለትም ማስታወቂያ እና ዲጂታል ሀብቶችን ያካትታል ሲሉ ማክጉርን ተናግረዋል።
ትሩዝ ሚዲያ ከቴክኖሎጂ ድርጅቶች፣ ከዜና ተቋማት እና ከውርርድ ገበያዎች ጋር ለመስራት ያሉትን ዕድሎች እየተመለከተ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።
ቢቢሲ ተጨማሪ አስተያየት ለመጠየቅ የትራምፕ ሚዲያ ኤንድ ቴክኖሎጂ ግሩፕን ቢያነጋግርም ምላሽ አላገኘም።
ኩባንያው 1.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስመዝገቡን ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ89% ጭማሪ አሳይቷል። ነገር ግን በክሪፕቶከረንሲ ምንዛሬዎች መውረድ ምክንያት አጠቃላይ ኪሳራ ደርሶበታል።
በሁለተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ፣ በአጠቃላይ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ማፍራቱን ገልጿል። ከዚህ ውስጥ ወደ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋው በጥሬ ገንዘብ፣ በአጭር ጊዜ ኢንቨስትመንቶች እና በዲጂታል ምንዛሬዎች የተገኘ ነው።
ቡድኑ የክሪፕቶከረንሲ ምንዛሬ ክምችት እና የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንቶችን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰሱ ተገልጿል።
በዚህ ወር መጀመርያ ላይ 'ትራምፕ ሚዲያ ክሪፕቶ ዶት ኮም' የተባለ ድርጅት ለመመስረት የነበረውን ዕቅድ የሰረዘው ትሩዝ ሶሻል የተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ የሚኖረውን ገበያ ከተነበየ በኋላ ነው።















