ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፑንትላንድ ግዛት ኃይሎች እና በሶማሊያ መንግሥት ጦር መካከል ከፍተኛ ውጊያ መቀስቀሱ ተገለጸ
በሶማሊያዋ ከተማ ጋልካዮ በፑንትላንድ የፀጥታ ኃይሎች እና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው የተባሉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ መቀስቀሱ ተገለጸ።
የግዛቱ አስተዳደር ከፑንትላንድ ጋር ስለተዋጉት ኃይሎች ሲገልጽ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሷል።
ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የፑንትላንድ ኃይሎች እና በሞቃዲሹ መንግሥት ኃይሎች መካከል የተነሳው ውጊያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት የከፋው ነው ተብሏል።
በምሥራቃዊ የሶማሊያ አካባቢ ረቡዕ በተቀሰቀሰው ግጭት ሁለቱም ወገኖች ከባድ መሣሪያ መጠቀማቸውን የዐይን እማኞች እና ምንጮች ተናግረዋል።
በከተማው የሚገኙ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደገለጹት ቢያንስ አንድ ሰላማዊ ግለሰብ ሲገደል ሁለት ሌሎች ሰዎች በተኩስ ልውውጡ ወቅት ተጎድተዋል።
ቢያንስ አምስት የፀጥታ ኃይል አባላት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተገልጿል።
በሁለቱም ወገኖች በኩል ስለደረሰው ጉዳት ምንም የተባለ ነገር የለም።
ይህ ዘገባ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ስለክስተቱ ያለው ነገርም የለም።
ግጭቱ ከመነሳቱ ከቀናት በፊት የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት የሞቃዲሹ መንግሥት ቀጣናውን ለማወክ መሣሪያ እና ሠራዊት አሰማርቷል ሲሉ ከስሰዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ለዚህ ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ግጭቱ ከተነሳ በኋላ የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት ሰይድ አብዱላሂ ዴኒ በቴቭዥን በተላለፈ ንግግራቸው የፀጥታ ኃይላቸው "የታቀደ ኦፕሬሽን" መፈጸሙን አስታውቀዋል።
ይህ "የተቀናጀ ኦፕሬሽን" የተፈጸመው የፑንትላንድን "ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ የፌደራል መንግሥት የጦር መሣሪያ ክምችት" የሚገኝበትን ወታደራዊ ሰፈር በቁጥጥር ሥር ለማዋል ነው ብለዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድን በመግለጫው በተደጋጋሚ "የሥልጣን ጊዜው ያለፈው ፕሬዝዳንት" በማለት ጠቅሰዋል።
የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ፑንትላንድን "ለማወክ እና በአገሪቱ እጅግ በተረጋጉ ቀጣናዎች ደኅንነትን ለማሰናከል" ሞክረዋል ሲሉም ከስሰዋል።
ቢቢሲ እነዚህን ክሶች በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት፤ የፑንትላንድ ወጣቶች የፌደራል መንግሥቱ በሚደግፋቸው ኃይሎች ተታልለው ጦሩን ተቀላቅለው ከሌሎች የሶማሊያ አካባቢዎች ከመጡ ኃይሎች ጋር በመሆን እየተዋጉ ይገኛሉ።
የፑንትላንድ አስተዳደራዊ መዋቅር ሥር ካሉ ኃይሎች ውጭ ላሉት ዕውቅና እንደማይሰጥም አስታውቋል።
"አሁን በፑንትላንድ ያሉት ኃይሎች የፑንትላንድ ኃይሎች ብቻ ናቸው። ሌላ ኃይል የለም" ብለዋል።
የፌደራል ኃይል መሆናቸውን የሚገልጹት "በፑንትላንድ የፀጥታ ተቋማት" እንዲመዘገቡ አሳስበው ይህንን የማይተገብሩ "እርምጃ እንደሚወሰድባቸው" ተናግረዋል።
የፑንትላንድ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ሲያውሏቸው "ሰብአዊነት በተሞላው መንገድ እንዲይዟቸው፣ ለተጎዱት ድጋፍ እንዲሰጡ እና በኦፕሬሽን ወቅት የተያዙ ላይ ብዝበዛ እንዳያደርሱ" አሳስበዋል።
የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት ያደረጉት ንግግር በአብዛኛው ያመዘነው በጋልካዮ ከተማ የተነሳውን ግጭት ሶማሊያ ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በድንበር ላይ ከምታደርገው ውጊያ ጋር በማያያዝ ነው።
የፑንትላንድ ኃይሎች እንደ አል-ሻባብ እና ኢስላሚክ ስቴት ያሉ እስላማዊ ታጣቂዎችን በመዋጋት ዓመታት ማሳለፉን ተናግረዋል።
በካል ሚስካድ እና ጋልጋላ ተራሮች የተደረጉ ውጊያዎችን በማሳያነት በመጥቀስ ለብሔራዊ ደኅንነት ያበረከተውን አስተዋጽኦም ጠቅሰዋል።
የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት የፌደራል መንግሥቱ አል-ሻባብን ለመዋጋት መዋል የነበረበትን መሣሪያ በሶማሊያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻዎች ላይ አውሏል ብለዋል።
"የፌደራል መንግሥቱ አል-ሻባብን ለመዋጋት መዋል ያለበትን መሣሪያ ከሶማሊያውያን ጋር ለመዋጋት ማዋል እንዲያቆም እናሳስባለን" ብለዋል።
ይህ ክስ የተሰማው ሶማሊያ ደቡባዊ እና ማዕከላዊ የአገሪቱን ክፍል አንዳንድ ሥፍራዎች ከሚቆጣጠረው አል-ሻባብ ጋር ወታደራዊ ውጊያ እያደረገች ባለበት ወቅት ነው።
አል-ሻበብ የአገሪቱ ዋነኛ የደኅንነት ስጋት ነው።
ፑንትላንድ በአውሮፓውያኑ 1998 የተመሠረተች ሲሆን፣ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት አባል ግዛቶች አንዷ ናት።
በጊዜ ሒደት የራሷን የፀጥታ ኃይል በማደራጀት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በፀረ ሽብር እንቅስቃሴ መደገፍ ጀምራለች።
በግዛቲቱ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኃይሎች በአጠቃላይ በፑንትላንድነ ቁጥጥር ሥር መሆን እንዳለባቸውም ገልጻለች።
በጋልካዮ ግዛት ወታደራዊ ስምሪት መበራከቱ ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች በቅርብ ቀናት ውስጥ ሲያስጠነቅቁ ነበር።
የፑንትላንድ ፖለቲከኞች እና የአገር ሽማግሌዎች ወደ ግጭት እንዳይገባ ጥረቶች ሲያደርጉ ነበር።
የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት በንግግራቸው አጎራባች ግዛት የሆነችው ጋልሙዱግ፤ ከፑንትላንድ ጋር የምትጋራውን ጋልካዮ ደኅንነት ለመጠበቅ ትብብር ማድረጓን ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት እንጂ በግጭት ለመፍታት መሞከር እንደማይገባቸው አሳስበዋል።
ይህ ዘገባ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በፑንትላንድ የፀጥታ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥት ጦር መካከል የተነሳው ውጊያ መርገቡን የሚያሳዩ ምልክቶች አልታዩም።
ግጭቱ እንዳይባባስ ድርድሮች እየተደረጉ ስለመሆናቸው ግልጽ መረጃ አልወጣም።
ቢቢሲ የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት በሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ፕሬዝዳንት ላይ ያቀረቧቸውን ክሶች በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።