ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እና ኔታኒያሁ ከትራምፕ ጋር ተገናኙ

የፎቶው ባለመብት, Zelensky Social Media Account/Handout
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፤ ዋይት ሐውስ ንግግሩን "አዎንታዊ እና ፍሬያማ" ብሎታል።
ሁለቱ መሪዎች የእስራኤል ደጋፊ እና የዩክሬን ከአሜሪካ እርዳታ እንድታገኝ ወትዋች የነበሩትን የሴናተር ሌንዚ ግራምን ቀብር ለመታደም ዋሽንግተን ከትመው ነበር።
ዜሌንስኪ እና ትራምፕ ኪየቭ አሜሪካ የአየር መከላከያዋን እንድታጠናክር ባላት ተስፋ ዙሪያ መምከራቸው ታውቋል።
ኔታኒያሁ ደግሞ የአሜሪካ እና እስራኤል ወዳጅነት በኢራን ጦርነት ላይ ባለ እይታ ምክንያት በሻከረበት ወቅት ከትራምፕ ጋር ተነጋግረዋል።
ከጉብኝቱ አስቀድሞ ዜሌንስኪ ባለፈው ወር ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ጉባኤ ቃል የገቡትን የሚሳኤል መቃወሚያ እንዲሰጡ ይጫናሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ዩክሬን ለረጅም ጊዜ የአሜሪካን 'ፓትሪዮት' የተሰኘ የሚሳኤል መከላከያ ለማግኘት ስትፈልግ ነበር። የሚሳዔል መቃወሚያው እየተባባሰ ካለው እና በመላው አገሪቱ እየደረሰ ካለው የሩሲያ የድሮን እና የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ከተማዎቿን ለመከላከል እንደሚረዳት ትናገራለች።
በዝግ የተደረገው የሁለቱ መሪዎች ንግግር "በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን" ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ላይ አስታውቀዋል።
ምንም እንኳ የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታን በሚመለከት በይፋ የተረጋገጠ ባይሆንም ዜሌንስኪ ከንግግሩ በኋላ 'ፓትሪዮት ሚሳኤሎችን' አገር ውስጥ ለማምረት ትራምፕ ለዩክሬን ፈቃድ ለመስጠት ተስማምተዋል ብለዋል።
የዩክሬኑ መሪ ለፎክስ ኒውስ "ፈቃዱን እንደሚሰጡ ተቀብለዋል" ብለዋል ። "እናም ከጠንካራ የአሜሪካ የወታደራዊ ኩባንያዎች፤ ከአምራች ተወካዮች ጋር ተገናኝቼ ነበር" ብለዋል።
"ትብብር እናደርጋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ አክለዋል።
ቢቢሲ ከዋይት ሐውስ አስተያየት ጠይቋል።
ዜሌንስለኪ የአሜሪካ ሴኔት የሩሲያን ነዳጅ በሚገዙ አገራት ላይ ማዕቀብ ለመጣል በከፍተኛ ድምፅ ከመወሰኑ በፊት ከአሜሪካ ሕግ አውጭዎች ጋር ተገናኝተዋል።
ማዕቀቡ ከመጣሉ አስቀድሞ ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች እንዲህ ዓይነት ማዕቀቦች "ለአውሮፓ እና ለዩክሬን ትልቅ መልዕክት፤ ለሕዝባችን ትልቅ ድጋፍ ነው" ብለዋል።
'ፓትሪዮት ሚሳኤል' ሩሲያ የዩክሬን ከተሞችን ለመደብደብ እየተጠቀመችበት ያለውን ባሌስቲክ ሚሳኤል ማክሸፍ ከሚችሉ ጥቂት የአየር መቃወሚያዎች ውስጥ አንዱ ነው።
በአንድ ሺ ኪሎ ሜትር እየተምዘገዘገ የሚመጣን ሮኬት ማክሸፍ ይችላል። ይሁን እንጂ ዋጋው የሚቀመስ አይደለም። እያንዳንዱ የፓትሪዮት ሚሳኤል ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያስወጣል።
ዜሌንስኪ እና የዩክሬን ጦር ከዚህ ቀደም ኪየቭ 25 የፓትሪዮት አየር መቃወሚያ ስርዓት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Maâayan Toaf (GPO)/Handout/Anadolu via Getty Images)
ዜሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በኢራን ጦርነት ላይ ያተኩራል ተብሎ የተጠበቀውን ንግግራቸውን ለማድረግ በዋይት ሐውስ ተገኝተዋል።
የቅርብ ወዳጆች የነበሩት ሁለቱ መሪዎች ባለፉት ወራት ውጥረት ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈፀሟን በመቀጠሏ እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን ወደ ጎን በማለቷ በተደጋጋሚ ተችተዋል።
ከሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ "በጣም ጥሩ ውይይት ነበር" ብለዋል።
ኔታኒያሁ ለእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ሁለቱ መሪዎች ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት የጋራ ግባቸው ላይ መስማማት እንዳላቸው ተናግረዋል።
"ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጋር ካደረግኳቸው ምርጥ ውይይቶች አንዱ ነው" ብለዋል።
ከሁለቱ መሪዎች ንግግር በኋላ የአሜሪካ ጦር የኢራን ኃይል በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር እንደሞከረ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በኢራን የሚደገፉ የኢራቅ ኃይሎች በሳዑዲ የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የድሮን ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ ጥቃት መሰንዘራቸውን አስታውቀዋል።
ቴህራን በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።















