ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፊፋ ፕሬዚደንት ኢንፋንቲኖን ከሥልጣን ለማውረድ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ተቸ
የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ድርጅቱን እና ፕሬዚዳንቱን ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ለማዳከም እየተደረገ ነው ያለውን "የተቀናጀ እና የቀጠለ ዘመቻ" በጥብቅ ተቸ።
ፌደሬሽኑ ባወጣው መግለጫው ይህን ያለው ዴይሊ ቴሌግራፍ፣ ኢንፋንቲኖ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ዋና ፀሐፊ በነበሩበት ወቅት ከኢንፋንቲኖ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለነበራት ሴት የሥራ መልቀቂያ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሰጡ ከዘገበ በኋላ ነው።
የፊፋ ቃል አቀባይ፣ ኢንፋንቲኖ የቀረበባቸውን ክስ "ውድቅ እንዳደረጉት እና ከእውነት የራቀ" ሲሉ እንደገለፁት ለቴሌግራፍ ተናግረዋል።
ፊፋም በበኩሉ "ማስረጃ የሌላቸው እና በግልጽ የሚታዩ የሐሰት ክሶች" ሲል የተቸ ሲሆን "ግምቶች እና አሉቧልታዎች እንደ እውነት መቅረብ የለባቸውም ብሏል።
ኢንፋንቲኖ የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ ባቀረቡት አወዛጋቢ እቅድ ምክንያት ከዩኤፋ እና ከአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበራት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው።
የፊፋን ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስተዳድር እና የግል ባለሀብቶች ድርሻ የሚይዙበት 'ፊፋ ፎርዋርድ ኢንተርፕራይዝ' የሚል ኩባንያ ለማቋቋም የቀረበው እቅድ 21 በመቶ የሚሆነው ድርሻ ለግል ኢንቨስትመንት እንዲሸጥ የሚያደርግ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (ዩኤፋ) በኢንፋንቲኖ ላይ መተማማን እንደሌለው የገለፀ ሲሆን የኖርዌይ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ሊስ ክላቭነስ አርብ ዕለት ስዊትዘርላንዳዊ እና ጣሊያናዊ የሆኑት ፕሬዚደንቱ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ጠይቋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪው አወዛጋቢው እቅድ እንደገና ሊጀመር እንደማይችል ማረጋገጫ አልሰጡም ሲል በፊፋ ዝግጅቶች ላይ ላለመሳተፍ ዝቷል።
ፊፋ በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ " በፊፋ አባል ማኅበራት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዚደንቱ በተሰጣቸው ኃላፊነት እያገለገሉ እንደሆነ" ገልጿል።
ሆኖም "ፊፋን እና ፕሬዚደንቱን ለማዳከም አንድ አካላት የተቀናጀ እና ቀጣይነት ያለው ጥረት እያደረጉ መሆኑ ከዕለት ወደ ዕለት ግልጽ እየሆነ መጥቷል" ብሏል።
መግለጫው ጨምሮም "የፊፋ አባል ማኅበራት ድጋፍ የሌላቸው አካላት ፊፋ በገነባው ዲሞክራሲያዊ ሒደት ሊያሳኩት ያልቻሉትን በክስ ፣ አሉታዊ ትችት እና በሐሰተኛ መረጃ ለማሳካት መሞከር እንደሌለባቸውም" አሳስቧል።
በፕሬደዚዳንት ኢንፋንቲኖ ላይ ተቃውሞ የተሰነዘረው በአብዛኛው ከአውሮፓ ነው።
የሜክሲኮ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከቀጣናው አስተዳዳር አካል (ኮንካካፍ) ጋር በመሆን ለኢንፋንቲኖ ድጋፍ አሳይቷል።
ደቡብ አሜሪካም አባል አገራቱን ባላሳተፈ ድምጽ ኢንፋንቲኖን ከሥልጣን ለማውረድ የሚደረግ ማንኛውንም ጥረት እንደማትቀበል ገልጻለች።
ከዚህም በተጨማሪ ኢንፋንቲኖ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 54 አባል አገራት ድጋፍ አግኝተዋል።
ኢንፋንቲኖ ረቡዕ እለት የፊፋ ቦርድ አባላትን በሞሮኮ ራባት ስብሰባ ጠርተው ነበር።
ከስብሰባው መጠናቀቅ አራት ሰዓታት በኋላ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪው ፊፋ በኢንፋንቲኖ እና በዋና ፀሐፊው ማቲያስ ግራፍስትሮም ስም ባወጣው መግለጫ፤ የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ ለቀረበው አወዛጋቢ ዕቅድ ይቅርታ ጠይቋል።
ሆኖም "በታማኝነት ፣ በመልካም አስተዳዳር እና በፍትሕ ሒደት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን አልታገስም።" ብሏል።
ፊፋ ቅዳሜ ዕለት ያወጣው መግለጫም በተመሳሳይ በድርጅቱ ላይ እየቀረበ ያለውን ትችት መከላከል ላይ ያተኮረ ነው።