በጀርመን አውሮፕላን ማረፊያ ፈንጂ ከተገኘ በኋላ በወታደራዊ ካምፕ ላይ ድሮኖች ሲበሩ ታዩ

በቦን አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ሜቸርኒች የጦር ሰፈር የሚወስድ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Google

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሌፕዚግ አየር ማረፊያ ተቀጣጣይ ፈንጂ የጫነ ድሮን ከተገኘ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሁለት ድሮኖች በምዕራብ ጀርመን በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ሲያንዣብቡ ታዩ።

የጀርመን የጦር ኃይል ሐሙስ ምሽት ላይ በቦን አቅራቢያ በሚገኘው ሜቸርኒች በሚገኘው የጦር ሰፈር ድሮኖቹ መታየታቸውን አረጋግጧል።

ይህ የጦር ሠፈር የአሜሪካን ፓትሪዮት የአየር መከላከያ ሚሳዔል መገጣጠሚያዎች የሚገኝበት እንደሆነ ተዘግቧል።

የቡንደስዌህር የጋራ ኃይል ኮማንድ ቃል አቀባይ እንዳሉት ጉዳዩ ወደ አካባቢው ፖሊስ ከመመራቱ በፊት ወታደራዊ ፖሊሶች ወደ ቦታው ተሰማርተዋል።

ድሮኖች በአውሮፓ አገራት ጦር ሠፈሮች አቅራቢያ ሲታዩ ይህ የመጀመርያው አይደለም።

ከዚህ ቀደምም ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን ጦርነት የሚደግፉ የአውሮፓ አገራት ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ሰፈሮች ወይም አየር ማረፊያዎች አቅራቢያ ታይተው ያውቃሉ።

ሞስኮ ምንም ዓይነት ተሳትፎ የለኝም ስትል በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት እሁድ ዕለት ቢልድ ለተባለ ጋዜጣ እንደተናገሩት ጀርመን "አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ" ጥቃቶች መደበኛ ዒላማ ሆናለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ጦርነት ላይ አይደለንም፤ ነገር ግን በየዕለቱ የተለያዩ መሣሪያዎችን ባካተተ ጦርነት ውስጥ ዒላማ ነን" ብለዋል።

ጀርመን ፈንጂ የተጫነ አንድ ድሮን በሊፕዚግ/ሃሌ አውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ መድረስ እንደቻለ እየመረመረች ነው።

ይህ አውሮፕላን ማረፊያ በጀርመን ጦር ኃይል ስር ኔቶ የሚጠቀምበት ሲሆን የዩክሬን አንቶኖቭ አየር መንገድ እንደ ዋና መቀመጫ በመሆን ያገለግላል።

ቡንደስዌህር እሁድ ዕለት በሜቸርኒች ላይ ስለታዮት ድሮኖች እየተደረገ ስላለው ምርመራ ለቢቢሲ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

ከአካባቢው ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ሙከራም አልተሳካም።

የጀርመን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የጦር ሠፈሩ የፓትሪዮት ሚሳኤል ባትሪዎችን ለመጠገን የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን እና መለዋወጫዎችን ማከማቻን የያዘ ነው።

ዩክሬን የሩሲያን የባላስቲክ ሚሳዔሎች ለማክሸፍ የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ እነዚህ የአየር መከላከያ ስርዓቶች ወሳኝ ሆነዋል።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዚህ ሳምንት ተጨማሪ መሣሪያዎችን ከአጋሮቻቸው ጠይቀው ዩክሬን የሚተኮሱባትን ሚሳዔሎች ለማክሸፍ የምትጠቀምባቸው መሣሪያዎች እያለቁባት መሆኑን ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ለዩክሬን ፓትሪዮት ሚሳዔሎችን እንድታመርት ፈቃድ ከሰጡ በኋላ ባለፈው ሳምንት እንዲህ ዓይነቱን ስምምነት እንደሌለ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በአውሮፓ የአየር ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ የታዩት ድሮኖች አህጉሪቱን በከፍተኛ ስጋት እና ጥንቃቄ ውስጥ እንድትቆይ አድርገዋል።

ይህም የአውሮፓ ኅብረት በአህጉር አቀፍ ደረጃ የአየር መከላከያ ስለማኖር እንዲወያይ አስገድዷል።

አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ለድሮኖቹ ሩሲያን ተጠያቂ ያደረጉ ቢሆንም ሞስኮ ግን ቀድም ብላ ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።