"የግድያ ሙከራ የሚያስፈጽም ነገር ኖሮኝ አያውቅም" – የትግራዩ ሊቃነ ጳጳስ ስለ አክሱሙ ክስተቱ ምን ይላሉ?

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል

የፎቶው ባለመብት, Tigray Orthodox Tewahedo Church Diocese Of Humera

የምስሉ መግለጫ, ብፁዕ አቡነ ናትናኤል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በትግራይ ክልል በአክሱም ከተማ ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት "የግድያ ሙከራ" እንደተፈጸመባቸው፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተነጠሉ አባቶች የሚመራው የመንበረ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ላዕላይ ቤተ ክህነት ገልጿል።

ቤተ ክህነቱ "የግድያ ሙከራ" ሲል የጠራው የማክሰኞ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም. ክስተት ያነጣጠረው በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና በብፁዕ አቡነ አረጋዊ ላይ እንደሆነ አስታውቋል። ቤተ ክህነቱ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ በሁለቱ አባቶች መኖሪያ ቤት ላይ ተኩስ የተከፈተው "ሌሊት ሰዓት 6:30" እንደሆነ ጠቅሷል።

ድርጊቱ በተለይም በትግራይ ክልል አባቶች የተመሠረተው ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ በሆኑት አቡነ አረጋዊ "መኝታ ክፍል ላይ" እንደተፈጸመም ገልጿል።

የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል ከተባሉት አባቶች አንዱ የሆኑት አቡነ ናትናኤል ስለ ክስተቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አቡነ ናትናኤል እንደሚናገሩት ተኩስ የተከፈተው የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት ውስጥ በሚገኘው የጳጳሳት መኖሪያ ነው።

የአክሱሙ ዋና ጽህፈት ቤት የሚገኘው የቀድሞው ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባሰሩት 'ሰላማ ሴንተር' የተባለ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ እንደሆነም ገልጸዋል። የጽህፈት ቤቱ "ቀጥሎ ራሱን የቻለ የአባቶች መኖሪያ ሕንጻ" መኖሩን አስረድተዋል።

አቡነ ናትናኤል የማክሰኞ ሌሊቱን ክስተት ሲያስታውሱ "በአጋጣሚ እዚያ መኖሪያ ውስጥ የነበርነው ደግሞ ሁለት አባቶች ነን፤ እኔ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ማለት ነው" ይላሉ።

የተኩስ ድምጽ የተሰማው ሌሊት ስድስት ሰዓት ተኩል እንደሆነ ይናገራሉ።

"ከተኩሱ በኋላ 'ምንድነው?' ብለን ስንወጣ አንድ ጥይት ከቤታችን፣ ማረፊያ ክፍላችን ላይ፤ በተለይ አቡነ አረጋዊ ያረፉበት ማረፊያ ክፍል ሕንጻው ላይ አርፎ በተወሰነ መልኩም ሕንጻውን ነድዶ፤ ግማሽ ብሎኬት ተገንጥሎ ወድቋል" ሲሉ የተመለከቱትን ገልጸዋል።

"በአጠቃላይ ሦስት ጥይቶች" እደተተኮሱ የሚናገሩት አቡነ ናትናኤል፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ በሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ ማደሪያ ላይ ማረፉን አስረድተዋል።

ግቢ ውስጥ የነበሩ የጥበቃ አባላት፤ ተኩስ የከፈተው ሰው "በዚያ በኩል ሆኖ አነጣጥሮ፤ ተኩሶብን አምልጦ ሄደ" የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አስታውሰዋል።

"ዋርድያዎቹ አንዱ 'እኔ ተከትዬው ሄጄ ነበር ግን አላገኘሁትም፣ አልደረስኩበትም። ዝም ብዬ እዚያ ሆኜ ግን አንድ ጥይት ወደ ሰማይ ተኩሻለሁ' የሚል ሃሳብ ነው የሰጠን" ሲሉም ያገኙትን ምላሽ ጠቅሰዋል።

"እስከ ሰባት ሰዓት ተኩል" ምን እንደተፈጠረ ሲጠይቁ ከቆዩ በኋላ ወደ ማረፊያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

"ወደ ራሳችን ስራ፣ ወደ ጸሎታችን ተመልሰናል። ሲነጋ የቅድስት ከተማ አክሱም የፖሊስ አባላትም፣ የፀጥታ ክፍሉም ሁሉም መጥተው የተደረገውን ነገር አይተው የምርመራ ሥራቸውን ጀምረዋል ማለት ነው" ሲሉ የፀጥታ አካላት ወደ ስፍራው የመጡት በማግሥቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የአክሱም ከተማ ፖሊስ፤ በሊቃነ ጳጳሳቱ መኖሪያ ላይ ጥይት ተኩሰዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ማዋሉን ትናንት ምሽት ትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የአክሱም ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ አሰፋ ገብረማርያም፤ በአባቶቹ መኖሪያ ላይ የተተሰኮው "አንድ ጥይት" መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ቴቪ ዘገባ ላይ ተጠቀሱት የከተማዋ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ "በተደረገው ማጣራት" ድርጊቱን "በጥበቃው እንደተፈጸመ መረጋገጡን" ተናግረዋል። ጥበቃውን ጨምሮ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ

የፎቶው ባለመብት, Tigray Orthodox Tewahedo Church Diocese Of Humera

የምስሉ መግለጫ, ቤተ ክህነቱ "የግድያ ሙከራ" ሲል የጠራው የማክሰኞ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም. ክስተት ያጣጠረው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ላይ እንደሆነ አስታውቋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቡነ ናትናኤል ተኩስ የተከፈተነው የአባቶቹ መኖሪያ ላይ እንደሆነ በመጥቀስ፤ "ወደ ቤታችን አነጣጥሮ ከመተኮስ በላይ የግድያ ሙከራ የለም" ይላሉ።

ከዚህ ቀደም ይህ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ኖሯቸው ያውቅ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "ለግድያ የሚያበቃ፣ ለግድያ ሙከራ የሚያስፈጽም ነገር አይኖረኝም፣ ሊኖረኝም አይችልም፣ ኖሮኝም አያውቅም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"በዚህ መልኩ እኔን እና ወንድሜን ይገድላሉ ወይም አንድ ነገር ያደርጋሉ… ብዬ የማስበውም የምጠረጥረውም አካል አይኖረኝም" ሲሉም አክለዋል።

በሁለቱ አባቶች ላይ "የግድያ ሙከራ መፈጸሙ" ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲንሸራሸሩ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ፤ አቡነ ናትናኤል በቅርቡ በትግራይ ክልል የሚታየውን "የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ" በተመለከተ ሰጥተውታል የተባለው አስተያየት ነው።

"ይህን ጉዳይ መቆም አለበት፤ እጃችሁን ከቤተክርስቲያን ላይ አንሱ" በሚል የሰጡት አስተያየትን ተከትሎ የተሰማው አንዳንድ የተቃውሞ አስተያየት ከማክሰኞው ክስተት ጋር ይገናኛል የሚል እምነት ይኖራቸው እንደሆነ ተጠይቀዋል።

አቡነ ናትናኤል፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለንግግራቸው "ይቅርታ እንዲጠይቁ" የተሰጡ አስተያየቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ከአሁኑ ክስተት ጋር ግንኙነት አለው የሚል ምልከታ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

"እኔ ሃሳቤን ነው የተናገርኩት። ለትውልድ ይሆናል፣ ለሀገር ይጠቅማል፣ እውነት መስሎ የታየኝን ነው የተናገርኩት። አንድ ሰው ደግሞ እውነት በመናገሩ ሌላ ነገር ይመጣበታል ብዬ ብዙም አላስብም እና አሁን የዚህ ሙከራ ከእሱ ጋር የተያያዘ ይሆናል ብዬ መገመት አልችልም" ብለዋል።