ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ በከባድ ሙቀት የተነሳ በሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ አልኮል መጠጣትን አገደች
በፈረንሳይ የሙቀት ማዕበል በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ፓሪስ አንዳንድ ግዙፍ ብሔራዊ የሙዚቃ ሁነቶች ላይ አልኮል መጠጣትን ከለከለች።
ዓመታዊው 'ፊቴ ዲ ላ ሚውዚክ' በዓል ሚሊዮኖችን ወደ ጎዳና የሚያስወጣ ሲሆን፤ ከ35 የፈረንሳይ ተቋማት አሳሳቢ የሙቀት ወጀብ ማስጠንቀቂያ ወጥቷል። ይህን ተከትሎም የፈረንሳይ መንግሥት በከፍተኛ ማስጠንቀቂያው በሕዝባዊ ቦታዎች ላይ አልኮል መጠጣትን ከልክሏል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ "በመንግሥት እና በኤጄንሲዎቹ በሚዘጋጁ ሁሉም ሁነቶች ላይ አልኮል እንዳይሰጥ መመሪያ ወርዷል" ብሏል።
እሑድ የሙቀት መጠኑ ከደቡብ ምዕራብ በፓሪስ ክልል በኩል ከ39 ድግሪ እስከ 40 ድግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቀል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ሙቀቱ 41 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ ይችላል ተብሏል።
የሙቀት ትንበያው ሠኞ እንደሚጨምር የሚያሳይ ሲሆን፤ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሙቀቱ በታሪክ ከከፍተኛው መጠን ጋር ሊስተካከል ይችላል ብለዋል።
መንግሥት የአልኮልን መጠን ለመገደብ ያወረደው መመሪያ "የድንገተኛ አደጋ እና የጤና አገልግሎቶችን ለመጠበቅ እና የጤና ባለሙያዎች በጣም የተጎዱ ሰዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማድረግ ነው።"
የሙቀት ወጀቡ ለቀናት የቀጠለ እና አገሪቷን የረበሸ ሲሆን፤ በርካታ የባቡር መስመሮችን እና ትምህርት እንዲቋረጥ አስገድዷል።
የፈረንሳይ የአየር ሁኔታ አገልግሎት የሆነው 'ሜትሮ ፍራንስ' ሲሶው የአገሬው ሕዝብ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ የሚጠበቀው የሙቀት ማዕበል ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ "እርግጠኛ" እንዳልሆነ ተናግሯል።
የፓሪስ ነዋሪዎችን እና ጎብኝዎችን ከሙቀት ማዕበሉ ለመጠበቅ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በፈረንሳይ መዲና ፓርኮች እና የአትክልት ስፍራዎች ምሽቱን ሙሉ ክፍት እንዲሆኑ አድርገዋል።
'ፊቴ ዲ ላ ሚውዚክ' ከ40 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የሙዚቃ ድግስ ሲሆን ሁሌም በፀሐያማ የበጋ ወራት ይሰናዳል።
ባለፈው ዓመት በፓሪስ ሁነቱቶችን ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ታድመዋል።