በትግራይ ክልል ራማ ከተማ በድሮን ጥቃት በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Image
በራማ ከተማ ዓርብ ጥቅምት 20 በተፈፀመ የድሮን ጥቃት በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች ደግሞ መቁሰላቸውን ሁለት የዐይን እማኞች እንዲሁም አንድ የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የድሮን ጥቃቱ ከረቡዕ ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲፈፀም እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል። በሦስቱ ቀናት ጥቃቶች በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸውን የቢቢሲ ምንጮች መረጃ ያመለክታል።
ሐሙስ ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ የተፈፀመው 12 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት በሦስቱ ቀናት ከተፈፀሙት ጥቃቶች ሁሉ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ዐይን እማኞች እና የሆስፒታል ምንጭ ገልፀዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመባት የራማ ከተማ በማዕከላዊ የትግራይ ዞን ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው የመረብ ለኸ ወረዳ ዋና ከተማ ናት።
ከፌዴራል መንግሥት ጋር በውጊያ ላይ የሚገኙ የትግራይ ኃይሎች በአብዛኛው በኤርትራ ድንበር ላይ ባሉ አካባቢዎች እንደሚገኙ ሲገልፅ ነበር።
የራማ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ የድሮን ጥቃቶች እየተፈፀሙ ያሉት በአካባቢው ምንም ዓይነት ውጊያ እና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በሌለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው መካከል ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የዐይን እማኝ፣ አርብ ጠዋት የተፈጸመው ጥቃት "እጅግ አስከፊ" እንደነበር ተናግረዋል።
ጥቃቱ ከሐሙስ የቀጠለ መሆኑን የገለፁት ግለሰቡ፣ ማሽላ ጭኖ ወደ ራማ ከተማ የገባ ተሽከርካሪ ሐሙስ ማታ 4 ሰዓት አካባቢ በድሮን ተመትቶ እንደነበር ገልፀዋል። በዚህ ጥቃት መኪናው ላይ እና በጫነው እህል ላይ ብቻ ጉዳት ደርሶ እንደነበር አስረድተዋል።
አርብ ማለዳ ደግሞ የመኪናው ባለንብረት ሠራተኞች እና የሚያግዙትን ሰዎች ጠርቶ የተበተነውን ማሽላ በማሰባሰብ ላይ እያሉ ጥቃቱ እንደተፈፀመ ተናግረዋል።
"ሕዝቡ ተሰብስቦ እያገዙት እያለ ድምጽ አልነበራትም [ድሮኗ] ቀጥታ መጥታ ነው ላያቸው ላይ የጣለችው። ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉም ከ25 ዓመት በታች የሚሆኑ ወጣቶች ናቸው" ብለዋል።
በዚህ ጥቃት 12 ሰዎች መሞታቸውን እና ከእነዚህም አስሩ ወዲያው የሞቱ ሲሆኑ፣ ሁለቱ በሦስት እግር የጭነት ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ አክሱም ለሕክምና ሲሔዱ ከነበሩ አምስት ሰዎች መካከል ሕይወታቸው ያለፈ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የጥቃቱን ሁኔታ ሲያስረዱ "በጣም የሚዘገንን ነው። ሟቾቹን ለመለየት እንኳን ተቸግረናል። ይህ እንትና ይሆናል፣ እንትና መኪናው ላይ ነበረ እየተባለ በግምት እየለየን ነው ቀብር የተፈፀመው" ሲሉ ገልፀዋል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሌላ እማኝ በበኩላቸው በአርቡ ጥቃት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከፍ አድርገዋል።
"13 ንፁሀን ሞተዋል። ሆስፒታል ከተወሰዱት መካከል ደግሞ ሁለቱ ሞተዋል። ብዙዎቹ ወዛደሮች ነበሩ። አንዳንዶቹን በመናኸሪያ ውስጥ ይሠሩ እንደነበሩ እናውቃለን። አሁን ራሱ አንድ አስከሬን ለመቅበር ወደ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እየተወሰደ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።
አስተያየት ሰጪው እንዳሉት፣ አስሩ ጥቃቱ ሲፈፀም ወዲውኑ የሞቱ ናቸው። "ድሮኗ አካላቸውን ቁርጥርጥ ነው ያደረገቻቸው. . . " በማለት የጥቃቱን አሰቃቂነት አስረድተዋል።
ከሞት የተረፉ ቁስለኞች ራማ ብርሽዋ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሌላ የዐይን እማኝ ፣ በጥቃቱ የሞቱ እና የቆሰሉ ቢያንስ 25 ሰዎችን መቁጠራቸውን ገልፀው፣ በኋላ ላይ ሲያጣሩ ቁጥሩ ከዚያ በላይ እንደሆነ ማረጋገጣቸውንም ጠቅሰዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀስ "ሠራዊት አልነበረም" ያሉት እኚህ እማኝ፣ በጥቃቱ የሞቱት እና የቆሰሉት "የባጃጅ ሹፌሮችን ጨምሮ ሠርተው የሚበሉ ሲቪሎች ናቸው" ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ ምግብ ቤት ላይ በተፈፀመ ሌላ የድሮን ጥቃት ደግሞ 2 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
"ጥቃቱ ምሳ እየበሉ ባሉ ሰዎች ላይ 6 ሰዓት ነው የተፈፀመው፤ ሐጎስ ምግብ ቤት ይባላል፤ ባለቤቱን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ወዲያው ነው የሞቱት" ያሉት ግለሰቡ፣ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና መወሰዳቸውን አስረድተዋል።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጥቃት መፈፀሙ ያሰጋቸው የራማ ከተማ ነዋሪዎች ጥቃቱ "ሊቀጥል ይችላል" በሚል ስጋት ውስጥ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።
ሁለተኛው የዐይን እማኝ ከሁለት ቀናት በፊት ሲቪሎችን በጫነ መለስተኛ "ሚኒባስ" ላይ በደረሰ ሌላ ጥቃት ሁለት ሲቪሎች መገደላቸውንም ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ጥቃቱ ሕዝቡ "ከፍተኛ ስጋት" ላይ እንደወደቀና የከተማዋ እንቅስቃሴም "ሙሉ በሙሉ እንደቆመ" አክለው ገልፀዋል።
ቢቢሲ ባለፉት ሦስት ቀናት በተፈፀሙ ጥቃቶች በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ከሌላ አካል አላረጋገጠም።
ጥቃቱን በተመለከተ መንግሥት የሰጠው መግለጫ የለም። ከፌዴራል መንግሥት እና ከመከላከያ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
አርብ ከሰዓት በኋላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሆስፒታል ምንጭ፣ በአርብ ጠዋቱ የራማ የድሮን ጥቃት 25 ተጎጂዎችን መቀበላቸውን፣ ከነዚህም መካከል በርካቶች ሞተው ሆስፒታል መድረሳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
"ወደ 25 የሚጠጉ ተጎጂዎች ወደ እኛ መጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ ሞተው ነው ሆስፒታል የደረሱት። አንዳንዶቹን እኛ እየረዳናቸው ሳለ ሕይወታቸው አልፏል። ከተረፉት መሀል አምስቱ ወደ አድዋ እና አክሱም ሪፈር ተደርገዋል" ብለዋል።
አክለውም "ሁኔታው በጣም መጥፎ ነበር፣ የሟቾች አካላቸው ራሱ ተቃጥሏል።. . . አንዳንዶቹ ተሰብረዋል፤ ጭንቅላታቸው አይታይ፤ ፊታቸው አይለይ። አስክሬን ለመለየት ተቸግረን ነበር፤ ቤተሰቦቻቸውን እየጠራን እያሳየን፣ አንዳንዶቹን በተራረፈ አካላቸው፣ አንዳንዶቹን ደግሞ በመታወቂያ ነበር የለየናቸው" ሲሉ ምንጩ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ በራማ ከተማ "በሲቪሎች ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸውን" ገልፆ፣ ጥቃቱን "ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም" ብሎታል።
ንፁሐን ላይ የሚደርስ የጅምላ ጥቃት እንዲቆምም ጥሪ አቅርቧል።
በትግራይ ክልል ዳግመኛ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ አካባቢዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችም መሰል የድሮን ጥቃቶች የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በተጠለሉበት 'ጃሪ ቁጥር 2' የተፈናቃዮች ካምፕ ላይ ሐሙስ ዕለት በተፈፀመ የድሮን ጥቃት "ሕጻናት እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ" 18 ሰዎች መገደላቸው እማኞች ተናግረዋል።

































