ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር ለ5000 ኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ ከለላ እንዲያነሳ ፈቀደ
በአሜሪካ የሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት ከ5000 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የተሰጠውን በአገሪቱ የመኖርና የመሥራት መብት ሕጋዊ ከለላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እንዲያቆም ፈቀደ።
የቦስተን ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ዳኛ ብራያን መርፊ፣ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ከተወሰኑ አገራት ለመጡ ሰዎች የተሰጠውን 'ጊዜያዊ የጥበቃ ሁኔታ' (ቲፒኤስ/TPS) እንዳያቋርጥ ይከለክል የነበረውን የመጨረሻ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አንስተዋል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰኔ ወር የትራምፕ አስተዳደር ከሄይቲ እና ከሶሪያ ለመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰጡ ተመሳሳይ ጥበቃዎችን እንዲያቋርጥ ከፈቀደ በኋላ ነው።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ 6 ለ 3 በሆነ አብላጫ ድምጽ ድጋፍ በማግኘቱ ዳኛው ከ13 አገራት ለመጡ ሰዎች የተሰጠውን 'ጊዜያዊ የጥበቃ ሁኔታ' (ቲፒኤስ) ለማቆም የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ የሚያደርገውን ጥረት ለመቃወም የሚያስችላቸውን አቅም አሳጥቷቸዋል።
ጊዜያዊው የሕግ ከለላ (ቲፒኤስ) ከእነዚህ አገራት ለመጡና መስፈርቶቹን ለሚያሟሉ ስደተኞች በሰብዓዊ ምክንያቶች ከአገር እንዳይባረሩ ጥበቃ ይሰጣል።
የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ዋና የሕግ አማካሪ የሆኑት ጄምስ ፐርሲቫል፣ ውሳኔውን በደስታ መቀበላቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል ተቋርጠው የነበሩት ሁሉም የቲፒኤስ ከለላ ጉዳዮች አሁን በይፋ ተፈጻሚ መሆን መጀመራቸውንም ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ ከለላ መቋረጥ በበርካታ ኢትዮጵያውያን እና ለአፍሪካውያን ስደተኞች መብት የሚታገለው 'አፍሪካን ኮሚኒቲስ ቱጌዘር' በተሰኘው የመብት ተሟጋች ቡድን ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል።
ቡድኑ ማክሰኞ ዕለት በተላለፈው ውሳኔ ቅር እንደተሰኘ በመግለጫ አስታውቋል።
"በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ በአሜሪካ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላል" ሲሉ የቡድኑ የፖሊሲ እና የጥብቅና ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዲያና ኮናቴ ተናግረዋል።
ጊዜያዊ ጥበቃ የሚሰጥበት ሁኔታ (ቲፒኤስ) በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጦርነቶች ወይም በሌሎች ከባድ ክስተቶች ለተጎዱ አገራት ዜጎች የሚሰጥ ከለላ ነው። እነዚህን መስፈርቶቹን የሚያሟሉ ስደተኞች በአሜሪካ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ እንዲሰሩ የሚያስችል ሲሆን፣ ከአገር እንዳይባረሩም ጊዜያዊ ጥበቃ ያደርግላቸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን ይህንን ከለላ የሰጡት እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 ዓ.ም. ሲሆን ይህም የአፍሪካን ዜጎች ከትጥቅ ግጭት እና ከሰብዓዊ ስቃይ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ነው።
በታህሳስ ወር፣ በወቅቱ የቀድሞዋ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖኤም ይመራ የነበረው የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ (ዲኤችኤስ)፣ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በመሻሻሉ ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው ቢመለሱ ከባድ ስጋት ስለማይገጥማቸው እነዚህን ጥበቃዎች እንደሚያቆም አስታውቀው ነበር።
መርፊ የዲኤችኤስን እርምጃ በሚያዝያ ወር መሠረታዊ የሕግ ሂደቶችን ችላ ብሏል እንዲሁም ጥበቃዎቹን ለማስቆም "አሳሳች" ምክንያት ሰጥቷል በሚል አግደውት ነበር።
ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ፣ ዳኛ መርፊ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠው ጥበቃ ለጊዜው እንዲቀጥል የሚያደርግ ሌላ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ይህንን ውሳኔ ባስተላለፉበት ወቅት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባልዳሰሳቸው ሌሎች ሕጋዊ ምክንያቶች ላይ በመመስረት፣ የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ይህንን ጥበቃ እንዳያቋርጥ የሚደረገውን እገዳ ማስቀጠል ይገባ እንደሆነ እያጤኑ ነበር።
በፍርድ ቤቶቹ የተደረጉት ክርክሮች በ1990 የወጣው ሕግ፥ ከመባረር መጠበቅን ለማራዘም ወይም ለማቋረጥ ሥልጣኑን የሰጠው ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንጂ ከመስከረም 11፣ 2001 ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ለተቋቋመውን ዲኤችኤስ አይደለም የሚል ነበር።
ከደቡብ ሱዳን፣ ከምያንማር እና ከሶማሊያ የመጡ ሰዎችን የሚመለከቱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ዳኞች በቅርብ ቀናት ውስጥ ይህንን ክርክር ውድቅ አድርገዋል። መርፊም ማክሰኞ ዕለት ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ይህንንም ሆነ ሌሎች የይገባኛል ጥያቄዎችን ውድቅ ያደረጉት ዳኛው፣ የዲኤችኤስ እርምጃ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት በመጣስ በዘር ወይም በብሔር ጥላቻ ተነሳስቶ መሆን አለመሆኑን ከሳሾቹ ክርክር እንዲያደርጉ እንደሚፈቅድላቸው ተናግረዋል።
ከሳሾቹ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ውስጥ አደገኛ ሁኔታዎች ምን ያህል እንደቀጠሉ ችላ ብሎታል ሲሉ ተከራክረዋል። አክለውም የቲፒኤስን ከለላን ማቋረጥ ነጭ ያልሆኑ እና አውሮፓዊ ያልሆኑ ሰዎችን ከአገር የማባረር ተግባር አካል ነው ሲሉ ተደምጠዋል።