ጋና በፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ውዝግብ የተነሳ የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዝዳንት ጉብኝት ሰረዘች

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በሚቀጥለው ወር ጋናን እንደሚጎበኙ ይጠበቅ ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በደቡብ አፍሪካ የመጤ ጥላቻ ተቃውሞ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ያስወጣችው ጋና፤ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአገሪቱ ሊያደርጉ የነበሩትን ጉብኝት አራዘመች።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በነሀሴ ወር መጀመሪያ ላይ ጋናን ለመጎብኘት አቅደው ነበር። ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ያረግባል የሚል ተስፋም ነበራቸው።

ይሁን እንጂ ጉብኝታቸው በጋና ሰፊ ተቃውሞ ይቀሰቅሳል በሚል ብዙዎች ሰግተዋል።

ሐሙስ ዕለት የጋና መንግሥት ቃል አቀባይ ፍሊክስ ክዋኬይ ኦፎሱ ጉብኝቱ አሁን እንደማይካሄድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በመጤ ጠልነት ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ጉብኝቱ ቢራዘም በጎ ነው በሚል መልዕክት ልከንላቸዋል" ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ ሁኔታውን ቀለል ለማድረግ የሞክራለች። የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግወንያ አገራቸው በሁለቱ እህትማማች አገራት መካከል "ግንኝነትን ለማጠናከር" እና "የአፍሪካ አጀንዳን ለማሳደግ" የማይለወጥ ቁርጠኝነት አላት ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ለሁለቱም አገራት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመጠቀም አመቺ ጊዜ ለማግኘት መነጋገር ይቀጥላሉ።"

የጋና ባለሥልጣናት የራማፎሳ ጉዞ ብሔራዊ ጉብኝት እንደሆነ ቢናገሩም የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ግን ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረ የሁለትዮሽ ስብሰባ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በደቡብ አፍሪካ የሚኖር ጋናዊ ወጣት በፀረ ስደተኛ ተቃዋሚዎች "አገርህን ሄደህ አቅና" ሲባል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በስፋት ከተሰራጨ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ውጥረት አይሏል።

ከዚያ በኋላ ጋና 900 የሚሆኑ ዜጓቿን ከደቡብ አፍሪካ ያስወጣች ሲሆን፤ የመጨረሻዎቹ ዜጎቿ በመጪዎቹ ሳምንታት ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ናይጄሪያ፣ ማላዊ እና ኬንያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በቅርብ ወራት በተደረገ ፀረ ስደተኛ ተቃውሞች ምክንያት ዜጎቿቸውን ከደቡብ አፍሪካ አስወጥተዋል።

አንዳንድ ፀረ ስደተኛ ቡድኖች ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች አገራቸውን ለቅቀው እስከ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም. እንዲወጡ ቀን ቆርጠው ነበር።

እስካሁን ድረስ 25 ሺ የውጭ አገር ዜጎች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ሰዎች ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ የመቃወም መብት እንዳላቸው ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል ከዚህ የበለጠ እንደሚሰሩም አክለዋል።

የጋና እና ደቡብ አፍሪካ መቃቃር የተባባሰው ባለፈው ሳምንት የ40 ዓመቱ ጋናዊ ተገድሏል መባሉን አክራ ካወገዘች በኋላ ነው።

የጋና ባለሥልጣናት ዜጋቸው የተገደለው በሰኔ 23ቱ ፀረ ስደተኛ ተቃውሞ ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት እንዲህ ግን አይነት ግድያ እንዳልተፈፀመ በመግለጽ ውድቅ አድርገውታል። በአገሪቱ የተገደለው ብቸኛ ጋናዊ የ35 ዓመት ግለሰብ እንደሆነ እና ሞቱም ከተቃውሞው ጋር እንደማይያያዝ አስታውቀዋል።

የደቡብ አፍሪካ የፍትኅ ሚኒስትር ጋና "በሕገ ወጥ ስደተኞች ጉዳይ ስለ ደቡብ አፍሪካ ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጨች ነው" በሚል ከስሰዋል።

በጋና እና ደቡብ አፍሪካ መቃቃር ውስጥ የሕግ ጥያቄ ቁልፍ ስፍራ ይይዛል። አክራ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አብዛኞቹ ዜጎቿ ለመኖር የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ አላቸው ስትል፤ ፕሪቶሪያ ግን አትስማማም። ሁለቱም አገራት አቋማቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረቡም።

በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠልነት አዲስ አዝማሚያ አይደለም። በአገሪቱ ላለው ሥራ አጥነት እና ወንጀል የውጭ አገር ዜጎች በተደጋጋሚ ተጠያቂ ይሆናሉ።