የቀረበላቸውን "የይቅርታ ሰነድ" የፈረሙ እና ውድቅ ያደረጉ የሽብር ተከሳሾች በተለያየ ክፍል እንዲታሰሩ መደረጉ ተገለፀ

 (ከግራ ወደ ቀኝ) ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ የአማራ ምክር ቤት አባል ዮሃንስ ቧያለው፣ መስከረም አበራ እና ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ
የምስሉ መግለጫ, "የይቅርታ ሰነዱን" ውድቅ አድርገዋል ከተባሉ ተከሳሾች መካከል (ከግራ ወደ ቀኝ) ዳዊት በጋሻው፣ ዮሃንስ ቧያለው፣ መስከረም አበራ እና ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ይገኙበታል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከአማራ ክልል ቀውስ ጋር በተያያዘ የተከፈተባቸው "የሽብር ክስ እንዲቋረጥ" የቀረበውን "የይቅርታ ሰነድ" የተቀበሉ እና ውድቅ ያደረጉ ተከሳሾች የታሰሩበት ክፍል እንዲለያይ መደረጉን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የተከሳሾቹ ማቆያ እንዲለያይ የተደረገው "በይቅርታ ሰነዱ ምክንያት ከተፈጠረ አለመግባባት" ጋር በተያያዘ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል።

የሽብር ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ሌሎች ተከሳሾች፤ "መንግሥት የይቅርታ ሰነድ" እንዳቀረበላቸው ሦስት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታሳሪዎቹ፣ "ይቅርታ ጠይቀው ክሳቸው እንዲቋረጥ እና ከእስር እንዲለቀቁ" ለቀረበላቸው ጥያቄ የተለያየ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ከማክሰኞ ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም. ጀምሮ "የይቅርታ ሰነዱ" ላይ ፊርማቸው ያኖሩ እና የተቃወሙት ተከሳሾች የነበሩበት ማቆያ ክፍል እንዲለያይ መደረጉንም ምንጮቹ አስረድተዋል።

ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም። የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽንን አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ ቀርቧል።

ሰነዱን ላይ እንደማይፈርሙ ከገለጹ ተከሳሾች መከካል የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ ዮሐንስ ቧያለው፣ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ፣ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው እና ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃይለ ማርያም ይገኙበታል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎቹ ጎበዜ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ አባይ ዘውዱ እና ገነት አስማማውም ሰነዱን ውድቅ ካደረጉት መካከል እንደሆኑ ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአንድ ክፍል ውስጥ ከስልሳ በላይ ተከሳሾች እንደነበሩ የሚገልጹት ምንጮች፣ ሰነዱን ያልፈረሙ 24 ተከሳሾች በእዚያው ክፍል እንዲቆዩ ተደርገዋል። የተቀሩት ደግሞ ማክሰኞ ዕለት ከማቆያው ወጥተው፣ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ወደሚገኝ ሌላ ክፍል መዛወራቸውን ገልፀዋል።

ይህ እርምጃ የተወሰደው "በሁለቱ ቡድኖች መካከል በአቋም መለያየት ምክንያት አለመግባባት" በመፈጠሩ መሆኑን ምንጮች ጠቅሰዋል።

ከክፍል መለያየቱ በኋላ "ሰነዱ ላይ አንፈርምም" ያሉ ተከሳሾች ተደጋጋሚ ፍተሻ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ምንጮች ተናግረዋል።

በተለያዩበት ቀን ማክሰኞ እለት ፍተሻ እንደተደረገ፣ በማግሥቱ ረቡዕ ዕለት የቢቢሲ ዘገባ ከወጣ በኋላ ደግሞ "ከፍተኛ ፍተሻ" መካሄዱን አክለዋል።

የሽብር ተከሳሾቹ፣ "ይቅርታ ጠይቀው ከእስር እንዲለቀቁ" የሚጠይቀው ሰነድ የደረሳቸው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአንድ ወር ያህል ታሳሪዎቹን ከመንግሥት ጋር ካደራደረ በኋላ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሰነዱ ከቀረበላቸው ከ300 በላይ የሽብር ተከሳሾች ውስጥ አብዛኛዎቹ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ቢቢሲ ተገንዝቧል።

ለመፈረም ፈቃደኛ ያልሆኑት ተከሳሾች፣ የቀረበባቸውን ክስ በመቃወም በፍርድ ቤት እየተከራከሩ ባሉበት ሁኔታ፣ "ወንጀለኞች ነን" ብለው ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እንዳሳወቁ ሦስቱ ምንጮቻችን ተናግረዋል።

የይቅርታ መጠየቂያ ሰነዱ፣ ታሳሪዎቹ በተለያዩ መዝገቦች የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች "አምነው ኃላፊነት እንዲወስዱ" የሚጠይቅ መሆኑን ቢቢሲ የተመለከተው እና ሰነዱን አንፈርምም ያሉት የሽብር ተከሳሾች የፃፉት ደብዳቤ ያመለክታል።

ጥያቄያቸው፣ መንግሥት ለክስ ሂደቱ እልባት መስጠት ከፈለገ፣ ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ "ክሱን አቋርጦ በምህረት ይፍታን" የሚል ነው።

በወንጀል ሕግ እና በይቅርታ አዋጅ መሰረት፣ አንድ ተከሳሽ ወንጀለኛ ተብሎ ካልተፈረደበት በስተቀር በይቅርታ ሂደት ውስጥ ማለፍ እንደማይችል የሕግ ባለሞያዎች ይገልፃሉ።