የአዲስ አበባን ጉዳይ ቅርቃር ውስጥ ያስገባው "ከበላይ የመጣ" ሃሳብ እና የምክክር ኮሚሽኑ ምላሽ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

አዲስ አበባ ከተማ የምክክር ሒደቱ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ሆናለች።

ለምክክር ከቀረቡ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ በሆነው "የፌዴራል ከተሞች" ስር የተካተተው የአዲስ አበባ ጉዳይ "የምክክሩን ሂደት የጎተተ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል" ይላሉ፤ በዚህ አጀንዳ ላይ ከሚመካከሩት አንዱ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት።

እስከ 250 ቡድን ባለው ምክክር ላይ፤ ከሁሉም አጀንዳዎች በላይ ዘግይቶ፣ በከፍተኛ ልዩነት ታጅቦ የተጠናቀቀው ይኸው የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ነው። ይህን ያሉን ካናገርናቸው የምክክሩ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ናቸው። በሒደቱ ላይ በንቃት ይሳተፋሉ። ማንነታቸውን አንድንገልፅ ግን አልፈቀዱልንም።

ምክክሩ በኢትዮጵያ ላሉ ችግሮች አንዳች መፍትሔ እና አስተዋጽኦ ሊያመጣ እንደሚችል ከፍተኛ ተስፋ ሰንቀው ነው ለመሳተፍ የወሰኑት። ራሳቸው ከሚሳተፉበት የከተሞች አጀንዳ በተጨማሪ የሌሎች ቡድኖችን አጀንዳዎችም በደምብ እንደሚከታተሉ ይገልፃሉ። ሦስት አጀንዳዎች ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ እና ብዙ አጨቃጫቂ የነበሩ ቢሆኑም የአዲስ አበባ ግን "የተለየ ነው" ይላሉ።

በምክክሩ ላይ ዋና አጀንዳ እንደመሆኗ፣ አዲስ አበባ የብዙዎች የልብ ትርታ ሆናለች። የሚዲያው ትኩረት እሷ ነች። የፖለቲካ ፓርቲዎች በመግለጫዎቻቸው ከሚያነሷቸው ዋና ነጥቦችም አንዷ ነች።

"የሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ አጀንዳ እሱ [የአዲስ አበባ ጉዳይ] ብቻ ሆኗል፤ አሁን ሰባቱ አጀንዳዎች መኖራቸውም የተረሳ ይመስለኛል" ይላሉ ግለሰቡ ሁኔታውን ለቢቢሲ ሲያስረዱ።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ አዲስ አበባን ዋነኛ የምክክሩ አስኳል ያደረጋት አጨቃጫቂ ጉዳይ፥ "ከበላይ የመጣ ነው" በሚል "አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ መሆኗን እውቅና የሚሰጥ" ሃሳብ ለአምስት መቶው ቡድን በሚላከው ቃለ-ጉባዔ ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ነው። ይህ ሃሳብ ከታች ጀምሮ በነበረው ምክክር ላይ በአጀንዳነት ያልነበረ እና ምክክር ያልተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል።

መጀመሪያ አካባቢ በአሥር እና በሃምሳ ቡድን ደረጃ በነበረው ምክክር አዲስ አበባ የማን ትሁን በሚለው ጉዳይ ላይ "የፌዴራል ትሁን እና የኦሮሚያ ትሁን" የሚል አማራጭ ሃሳብ ጎልቶ ወጥቶ ነበር።

የፌዴራል ትሁን የሚሉ ተሳታፊዎች ቁጥር ሚዛን ሲደፋ፣ በአጀንዳ ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን የደገፉ ተመካካሪዎች ቁጥር ተጠቅሶ መፃፉ "ብቻውን የሀሳቡን ምርጥነት ሊያሳይ ስለማይችል ሃሳብ ላይ እንዳናተኩር ያደርገናል" የሚል ተቃውሞ ቀርቦ ቁጥር እንዳይጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።

"አብዛኞቹ እና የተወሰኑ" በሚል መጥቀስ እንደ አማራጭ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ይሔም በቁጥር ከመጥቀስ የተለየ አይደለም በሚል ተቃውሞ ተነስቶበት "አማራጭ አንድ፣ አማራጭ ሁለት" እየተባለ እንዲጠቀስ ሆኗል።

ያም ሆኖ፣ በሃምሳ እስከተደራጀው ቡድን ድረስ የጎላ ልዩነት ሳይፈጠር "በብዙ ጉዳዮች ላይ ተስማምነተን ነበር" ይላሉ።

ከተማዋ "ራሷን የቻለች፣ በአስተዳደራዊ መዋቅር ለፌዴራሉ የምትጠራ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ያላት፣ የራሷን ፖሊስ እና ፍርድ ቤት የምታደራጅ፣ በአዲስ አበባ ነዋሪ የተመረጠ አስተዳዳሪ የሚያስተዳድራት፣ የፌዴራሉ መቀመጫ ከተማ ትሁን" የሚለው በአብዛኛው ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበረ አንስተዋል።

አከራካሪ ጉዳይ የተነሳው የዚህ ቃለ-ጉባዔ ሲደራጅ "ከበላይ አካል የመጣ አዲስ ሃሳብ አለ፤ ቃለ-ጉባዔው ውስጥ ቢገባ የሚል ሃሳብ እኛ ጋር መጣ። ይህ ከበላይ መጣ የተባለው ሃሳብ ከታች ጀምሮ ያልመጣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ መሆኗን ዕውቅና የሚሰጥ ነው። ይህ በብዙዎቹ ተወያዮች ዘንድ ቅሬታ ፈጠረ" በማለት አብራርተዋል።

ለአንድ ሳምንት ያህል ያጨቃጨቀው ይህ አጀንዳ ብቻ እንደነበረ ያስታውሳሉ። ምክክር ሳይደረግበት "ከበላይ የመጣ ነው" በሚል ሃሳቡ ለመድረኩ የቀረበበት መንገድ ጭምር "የተሳሳተ ነው" ሲሉ ይገልፃሉ።

በአጀንዳው ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተመደቡ ባለሞያዎችም "የአንድ ወገን ፍላጎትን የሚያንፀባርቁ ነበሩ" ብለዋል።

ለምሳሌ በሕገ-መንግሥቱ ስለተጠቀሰው የልዩ ጥቅም ጉዳይ ሲያብራሩ "አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል በጀታቸውን እና የበጀት ቀመራቸውን እንዲሁም የአስተዳደር ጉዳይን በጋራ ያዘጋጃሉ" ማለት እንደሆነ በማብራሪያቸው ማንሳታቸውን አስታውሰዋል።

ይህ አገላለፅ ለብዙዎቹ ተመካካሪዎች ለመቀበል የሚያስቸግር እንደሆነባቸው እና እንዲያቆሙ መደረጋቸውንም አክለዋል። ለኮሚሽኑም ቅሬታ ቀርቦ ባለሙያዎቹ ከዚያን ጊዜ በኋላ ማብራሪያ እንዳይሰጡ ስለመታገዳቸው ተናግረዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች ጉዳዩን "ካለቅጥ ለጥጠውት ለአምስት መቶዎቹ ማቅረብ ከነበረብን ሦስት፣ አራት ቀን ያህል እንድንዘገይ አድርጎናል" በማለት ገልፀዋል። እንዲያውም "ይህንን [የምክክር መድረክ] ይመራ የነበረ አንድ ሰብሳቢ ጉዳዩ በጣም በውጥረት የተሞላ በመሆኑ ስኳሩ በጣም ከፍ ብሎ ታሞ ለሁለት ቀናት ሆስፒታለል ገብቶ ነበር" ይላሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዱ።

አከራካሪ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል የከተማዋ የባለቤትነት ጉዳይ፣ በግለሰብ ደረጃ ከሚነሱ ሃሳቦች ባለፈ "በብልጽግና ፓርቲም እንደ አጀንዳ የተያዘ ባለመሆኑ" ከሃምሳ ቡድን አልፎ ብዙም ክርክር የተደረገበት እንዳልሆነ ገልፀዋል። ከሁለት መቶ ሃምሳ ቡድን ጀምሮ ያከራከረው የአዲስ አበባ የዋና ከተማነት ጉዳይ ግን የብልጽግና ፓርቲ አባላትን ጭምር ለሁለት ከፍሎ እንደነበር አብራርተዋል።

ሌላው በሂደቱ እንደተስተዋለ ያነሱት ጉዳይ፣ አንዳንድ ባለሥልጣናት አወያዮችን በአካል እና በስልክ በማግኘት "ጫና የመፍጠር እና ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ነበራቸው" የሚል ነው።

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ "ምክክሩ እየተጠናቀቀ ሲመጣ ፍላጎታችን ተጓደለ ብለው የሚያስቡ አካላት በዋናነት ብልጽግና ከአቋሙ መንሸራተት እና ቃል የገባውን ያለመጠበቅ ሁኔታ ታይቷል" ብለዋል።

በዚህ የተነሳ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተወሰኑ አጀንዳዎች በይደር እንዲቆዩ እና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በይፋ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ቢቢሲ እርሳቸውን ባነጋገረ ማግስት አብን በጉዳዩ ላይ ለኮሚሽኑ የጻፈው የአቤቱታ ደብዳቤ ይፋ ሆኗል።

ፓርቲዎች እና ሌሎች የምክክሩ ተሳታፊዎች ምን ይላሉ?

አብን ማክሰኞ ቅሬታውን በገለፀበት ደብዳቤ ላይ ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ ሲሆን "የሒደቱ ወሳኝ ፈተና" መሆኑን አንስቷል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ የተነሳው ውይይት "የምክክሩን ተዓማኒነት በተጨባጭ የሚፈትን ጥልቅ ሀገራዊና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳይ" ሆኖ እንዳገኘው አብን ማክሰኞ ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም ይፋ በሆነው ደብዳቤው ጠቅሷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኗ በሕግ እውቅና አግኝቶ የሚጸናበት ወይንም "አዲስ አገራዊ ውጥረት የሚፈጠርበት አጀንዳ" ሊሆን እንደሚችልም ስጋቱን ገልጿል።

"አንድ ወገን" በሚል የጠቀሰው አካል በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ "በተደራጀ የቁጥር ብልጫ ሌላውን በሚደፈጥጥበት የድምፅ ውድድር ሊስተናገድ አይገባም" ሲል አመልክቷል።

ስለሆነም የአዲስ አበባን አጀንዳ ከዚህ በላይ ለማስኬድ መሞከሩ አገሪቱ ካለችበት ችግር የባሰ ውጥረት ውስጥ የሚከት እንደሚሆን በመግለፅ፣ በአስቸኳይ ንግግሩ እንዲቆምና "አጀንዳው እንዲያርፍ እንዲደረግ" አሳስቧል።

እናት ፓርቲ ሌላው ስጋቱን የገለፀ የምክክሩ ተሳታፊ ነው። ፓርቲው ረቡዕ ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፥ ሀገራዊ ምክክሩ ትኩረት ያደረገባቸውን ጉዳዮች ተችቷል።

". . .አዲስ አበባ[ን] በወከባ ብዛት ለአንድ ቡድን ሆ ብሎ ለማሳቀፍ እና አዲስ የፀብ ግንባር ለመቀስቀስ አልነበረም ለምክክር የተቀመጥነው" ያለው እናት ፓርቲ፣ "የዘርና ጎሳ ፌዴራሊዝምን ማስቀረት/ማለዘብ እንደ ዋና ግብ መያዝ" እንደነበረበት አመልክቷል፡፡

የእናት ፓርቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አያሌው ለቢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት ሊፈፅም የፈለጋቸውን አጀንዳዎች "በምክክር ሽፋን ሊተገብራቸው እየጣረ ነው" የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የሚያስፈልጉ የምክክር አጀንዳዎቸ "በጣም የተለጠጡ መሆን የለባቸውም ነበር" ሲሉ አጀንዳዎቹ መስፋታቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ ባለቤትነት እና የዋና ከተማነት ጉዳይ ላይ በምክክሩ የሚነሱ ጉዳዮች በዋናነት ምክንያታቸው "የጎሳ አደረጃጀት" መሆኑን የሚገልፁት ደ/ር ሰይፈሥላሴ፣ ምንም እንኳን አጀንዳዎቹ ጎን ለጎን ቢቀመጡም አንዱ ችግር የሚመነጨው ከሌላው እንደሆነ ያስረዳሉ።

"የጎሳ አደረጃጀት ችግር ቢፈታ የአዲስ አበባ ጉዳይ መፈታት ይችላል። አሁን የአዲስ አበባ ጉዳይም አጣብቂኝ ውስጥ የገባው በጎሳ ዕይታ ስለሚታይ ነው። ምናልባትም በጣም ከፍተኛ ቀውስ ሊያስነሳ ይችላል" በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ገነነ ገደቡ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ፕሬዝደንት ናቸው። በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እየተሳተፉ ነው። በሌሎች አጀንዳዎች ላይ የነበረው ምክክር በአንጻራዊነት የተሻለ መግባባት ያለበት መሆኑን አብራርተዋል።

እርሳቸው በሚሳተፉበት "የአገር ግንባታ" አጀንዳ ስር በተዳሰሱ ጉዳዮች ላይ የተሻለ መግባባት መኖሩን ያስረዳሉ። በቀረቡት አማራጮች ላይ የነበረው ምክክር፣ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ አዲስ ልማድ እንደመሆኑ "ጥሩ" ሊባል የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ነገር ግን "የፌዴራል ከተሞች" ጉዳይ "አጨቃጫቂ" ሆኖ መሰንበቱን ይጠቅሳሉ። በተመካካሪዎቹ ዘንድ የሚወራውም ይኸው የአዲስ አበባ ጉዳይ "በጣም አጨቃጫቂ" ስለመሆኑ ነው።

የኮሚሽኑ ምላሽ

"የፌዴራል ከተሞች" በሚል የቀረበው ራሱን የቻለ አጀንዳ ትኩረት የሚያደርገው አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ላይ ነው። በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ላይ የሚኒሱ የተለያዩ ጥያቄዎች በመኖራቸው ሳቢያ "ዘላቂ የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ለተግባሪ አካላት ቢቀርብ" በሚል በከተሞቹ ነዋሪዎች እና በሌሎችም አካባቢዎች ነዋሪዎች በከፍተኛ መጠን ጥያቄ በመቅረቡ ራሱን ችሎ በአጀንዳነት መቅረቡን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ በምክክሩ ላይ የአዲስ አበባ ጉዳይ ሰፊ የውይይት አጀንዳ ሆኖ መቆየቱን አረጋግጠዋል።

ነገር ግን የምክክሩ ተሳታፊዎች በአስር እና በሃምሳ ቡድን ደረጃ "በሚገባ" ንግግር አድርገው ምክረ ሃሳብ ከቀረበ በኋላ 250 ላይ ሲደርሱ "የተለያየ የሚመስሉ ሃሳቦች ቀረቡ" ሲሉ ከፍ እያለ ሲመጣ ፈተናዎች እንደገጠሙት ይገልፃሉ። እርሳቸው ያሉት፣ ስለሂደቱ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ የሰጡን በስም ያልጠቀስናቸው የምክክሩ ተሳታፊ ያሉትን የሚያጠናክር ነው።

አዲስ አበባ የፌዴራል ዋና ከተማ ትሁን በሚለው ላይ "በብዛት መግባባት ላይ የተደረሰ ይመስለኛል" የሚሉት ፕ/ር መስፍን፣ ነገር ግን "የባለቤትነቱ ጉዳይ ምን ይሁን? ጥቅምን በተመለከተ ምን ይሁን? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የተራራቁ ሃሳቦች እንደነበሩ አንስተዋል።

በ250 ቡድን ደረጃ የተነሱትን ሃሳቦች ለ500 ቡድን የሚያጠናቅሩ አጠናቃሪዎች "ራሳቸው እንደ ተመካካሪ ሆነው ነው የተገኙት። ራሳቸው ሃሳብ ይሰጣሉ፤ ራሳቸው አለመግባባት ይፈጥራሉ፤ ይሔ መሆን አለበት ብለው ይከራከራሉ" ብለዋል።

እነዚህ ችግሮች የተፈጠሩት ትክክለኛውን አካሔድ ባለመገንዘብ እና የራስን ስሜት ባለመግራት ሊሆን እንደሚችል ነው ዋና ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

"የሒደቱ ዓላማ ሰላሳው [አጠናቃሪዎች] እንዲከራከሩ ሳይሆን አምስት መቶዎቹ እንዲመካከሩበት ነው" ካሉ በኋላ፣ የልዩነት ሃሳቦች እንኳን ቢኖሩ ተመካክረው ወደ መሃል የሚያመጡት አምስት መቶዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል።

"ብዙዎች የሚመስላቸው በዚህ ስብሰባ ላይ ተወስኖ፣ አልቆለት፣ አዲስ አበባ ለአንድ አካል እንደሚሰጥ ነው። በጭራሽ እንደዚያ አይደለም። [በሂደቱ] የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ነው ሊሰጥ የሚችለው፤ እሱንም አምስት መቶው ናቸው። ከዚያም በኋላ ለአራት ሺዎቹ ጉባዔ ይቀርባል" ብለዋል።

አብን ባወጣው መግለጫ፣ በምክክር ሒደቱ ላይ ያነሳቸው ጥያቄዎቹ ምላሽ ካላገኙ ከሒደቱ ሊወጣ እንደሚችል ገልጿል። ፕሮፌሰር መስፍን ግን፣ ፓርቲው ይህን ማለቱን ተችተዋል።

ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ጉዳዮችን በተመለከተ "በዝርዝር እየገመገምን የሚስተካከለውን እያስተካከልን ነው እየሔድን ያለነው" ሲሉ ተናግረዋል። ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከሌሎች አካላት ቅሬታዎች ሲቀርቡ በመነጋገር መፍትሔ እየተሰጠ መቀጠሉን በአጽንኦት ገልፀዋል።

"ወደ ምክክር የመጣነው ነገሮችን እስከ መጨረሻው ለማብላላት ነው። መጨረሻ ላይ ውሳኔ የሚሰጡት አምስት መቶዎቹ እንጂ የተወሰነ አካል አይደለም" በማለት ለሚነሱት ቅሬታዎች መልስ ሰጥተዋል። የፓርቲውን እርምጃ "የምክክር ሂደቱን በሚገባ ባለመገንዘብ ወይም አላግባብ ጫና ለመፍጠር" የተደረገ እንደሆነ ነው የሚገልፁት።

"በተመካካሪዎች መካከል አንዳንዴ መዘላለፍም አጋጥሞናል" ያሉት ፕ/ር መስፍን፣ ይህ ከምክክሩ የሥነ-ምግባር መመሪያ ጋር የማይጣጣም ቢሆንም "ያለውን ስሜት በመረዳት አለመረጋጋት እንዳይፈጠር በተቻለ መጠን በጥበብ ነው እስካሁን ይዘን የመጣነው" ሲሉ አክለዋል።

ከባለሥልጣናት ጣልቃ-ገብነት ጋር በተገናኘ ለተነሳው ቅሬታ በሰጡት ምላሽ፣ ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና የከተማ ከንቲባዎች በተለያዩ ቡድኖች መሀል እየገቡ መታዘብ እና ማዳመጥ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ለዚህም ምክንያቱ፣ ባለሥልጣናቱ የክልላቸውን አንዳንዶቹም የፌዴራሉን መንግሥት ወክለው የመጡ እንደመሆናቸው ኃላፊነት ስላለባቸው ነው። ይሁን እንጂ አስተያየት የሚሰጡት ግን ራሳቸው በተመካካሪነት በሚሳተፉበት አጀንዳ ላይ ብቻ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

ባለሥልጣናት በሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እየሞከሩ እንደሆነ ከዚህ ቀደምም ክሶች ቀርበው፣ ድርጊቱን በመተቸት ባለሥልጣናቱ በመሰል ተግባር እንዳይሳተፉ ፕ/ር መስፍን አሳስበው ነበር።

ስህተት የፈጠሩ ባለሙያዎችም "እንዲታረሙ መደረጋቸውን" ዋና ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን፣ በሁሉም አጀንዳዎች ላይ ምክረ ሃሳብ ሊሰጥ እንደማይችል እና በይደር ሊቆዩ የሚችሉ፣ ለትውልድም የሚሸጋገሩ አጀንዳዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ያናገርናቸው ተሳታፊዎች ዕይታ ምንድነው?

የእስካሁኑን በምክክሩ በመሳተፍ ሂደቱን በሰፊው መገምገማቸውን የሚናገሩት ስማቸውን ያልጠቀስናቸው አስተያየት ሰጪ፣ ብዙ አጀንዳዎች ውሳኔ ሳይሰጥባቸው "በይደር ሊታለፉ ይችላሉ" ብለው ያምናል።

ምንም እንኳን ሂደቱ የሚመራበት መንገድ ወሳኝነት ቢኖረውም፣ በተለይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ያለው አለመግባባት እና የተካረረ ስሜት ጉዳዩን "ቅርቃር ውስጥ የገባ አጀንዳ" አድርጎታል ብለው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል።

በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በ250 ቡድን ደረጃ በአጀንዳው ላይ እንዳልተፈራረሙም ገልፀዋል። በከተማዋ ባለቤትነት ላይ ፌዴራሉ ተጠሪ የሆነች ራሷን የቻለች ከተማ ትሁን እና የኦሮሚያ ክልል አካል እና ተጠሪነቷም ለኦሮሚያ ክልል ይሁን የሚሉ ሁለት አማራጮች ቀርበዋል። የዋና ከተማነት ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ትሁን እና አትሁን የሚሉ ሁለት አማራጮች ቀርበዋል።

ይሁን እንጂ እንደ እርሳቸው ግምት "የአዲስ አበባ ጉዳይ ዴድሎክ ወይም ቅርቃር ውስጥ የገቡ" ጉዳዮችን በሚመለከት በሚወያየው ቡድን ታይቶ ነው ውሳኔ ሊሰጠው የሚችለው። ጉዳዩ በአግባቡ ካልተያዘ፣ አሁን በአገሪቱ ካሉ ቀውሶች ጋር ተዳምሮ ሰላምን እና የሕዝቦችን አንድነት ይበልጥ የሚያናጋ ጉዳት እንዳያስከትል እንደሚሰጉም ገልጸዋል።

አቶ ገነነ ገደቡም እንዲሁ፣ እስካሁን ካለው ሂደት በመነሳት በምክክሩ ላይ ተስፋም ስጋትም አላቸው። ስለምክክሩ በጎ ምልከታ ቢኖራቸውም ቅሉ፣ በኢትዮጵያ የተለመደ ነው የሚሉት "እኔ ያልኩት ካልሆነ" የሚል አካሄድ ከቀጠለ የከፋ ነገር ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

ከብልጽግና ፓርቲ በኩል አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ሆኖም፣ የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኮሚሽኑ ተግባር ላይ ሊኖር የሚችል የመንግሥት እና የፓርቲ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የተነሱ ክሶችን በተደጋጋሚ ማስተባበላቸው ይታወሳል።