የኢራን እና የአሜሪካ የተኩስ አቁም ትራምፕ 'አብቅቷል' ከማለታቸውም በፊት የፈረሰው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገራት ማኅበር (ኔቶ) ጉባኤ ቱርክ በነበሩበት ወቅት የአሜሪካ እና የኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት "ማብቃቱን" አውጀዋል።
ይህም ከሦስት ሳምንት በፊት ከፍተውት የነበረውን የድርድር በርን የሚዘጋው ይመስላል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአንካራ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ "የተኩስ አቁሙ አብቅቷል ብዬ አስባለሁ፤ ከዚህ በኋላ ከእነርሱ ጋር መስማማት አልፈልግም፤ አጭበርባሪዎች ናቸው" ብለዋል።
ምንም እንኳን ሁለቱም ወገኖች ሙሉ በሙሉ ተኩስ አቁመው ባያውቁም ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ የመግባቢያ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ ባልታየ መልኩ ጥቃቶች ጠንከር ብለው ተጀምረዋል።
ዋሽንግተን እና ቴህራን ወደ ለየለት ግጭት እያመሩ ይመስላሉ። ሁለቱም እጅ መስጠትን አልፈለጉም።
በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ፔፕ፣ "ችግሩ ትራምፕ የተፈተኑበትን ስትራቴጂያዊ ሽንፈት መቀበል አለመፈለጋቸው ነው" ይላሉ።
ጦርነቱን ያስነሱት ሁሉም ሊባሉ የሚችሉ ምክንያቶች አሁንም እልባት አላገኙም።
የትራምፕ አስተዳደር ከአገዛዝ ለውጥ እስከ የኒውክሌር ስምምነት ከዚያም እስከ የኢራንን የባሊስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራምን ማውደም ድረስ ያስቀመጣቸውን ግቦች አላሳካም።
ይህም አብዛኞቹ እነዚህ ጉዳዮች ለቀጣይ ድርድሮች እንዲተዉ አድርጓል።
ግጭቱ የኢራንን ተፅዕኖ ከመመለሱ በተጨማሪ እስላማዊ ሪፐብሊኳን በቀጠናው ዋነኛ ተዋናይ እንድትሆን አስችሏታል።
ከዚህም በተጨማሪ አገሪቷ ባላት የሆርሙዝ ወሽመጥን የመቆጣጠር እና መርከቦችን ዒላማ የማድረግ አቅም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ምን ያህል ኃያል እንደሆነች በግልጽ አሳይታለች።
"በዚህ ጦርነት ምክንያት ኢራን ይበልጥ ጠንካራ ለመሆን የቻለች ሲሆን፣ በቀጣናው ያለውን የኃይል ሚዛን ቀይራለች" ይላሉ ፔፕ።
የ86 ዓመቱ ጠቅላይ መሪዋ ቢገደሉም የ56 ዓመቱ ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ ሥልጣኑን ተረክበዋል።
አዲሱ የኢራን አስተዳደር በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና በባሕረ ሰላጤው ጎረቤት አገራት ላይ ጥቃት ለመክፈት "ጦርነትም፤ ሰላምም" የሌለበትን ሁኔታ ወደ ጎን ብሏል።
ከቴህራን ድሮኖች እና ባሊስቲክ ሚሳዔል ጥቃቶች በኋላ በባሕረ ሰላጤው ያሉ ነዳጅ ላኪ አገራትም በአሜሪካ እንጠበቃለን የሚለው በራስ መተማመናቸው ስለቀነሰ ሳዑዲ አረቢያ የእርቅ ጉባኤ እያዘጋጀች እንደሆነ ተነግሯል።
ሆኖም ይህ መተራመስ እስካሁን በድርድሩ ላይ አልተገለፀም።
14 ነጥቦችን የያዘው የመግባቢያ ስምምነት የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲከፈት የሚያደርግ እና በዓለም የኢነርጂ ገበያ ላይ ያለውን ጫና የሚያቀል ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ከባድ የሆኑትን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሞች እና በቀጣናው የምትደግፋቸውን ቡድኖችን በተመለከተም ለመደራደር በር የሚከፍት ነው።
ሆኖም የኒውክሌር ጥያቄዎችን ከመፍታት ይልቅ የመግባቢያ ስምምነቱ ትርጓሜ የፉክክር ማጠንጠኛ ሆኗል።
ቴህራንም ሆነች ዋሽንግተን ከጦርነት በኋላ ያሉ ትዕዛዞችን ላለመቀበል አልሸነፍ ባይ ሆነዋል።
ይህን እልህ መጋባት በሦስት ውስን ቦታዎች መረዳት ይቻላል - በሆርሙዝ ወሽመጥ፣ በሊባኖስ እና በኢራን ጦርነቱን እንዲታቆም የቀረበ የመልሶ ግንባታ የገንዘብ ዕቅድ።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሆርሙዝ ወሽመጥ ለዚህ ግልፅ ምሳሌ ይሆናል።
"ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠሯን አይቀበሉትም" የሚሉት ፔፕ፣ የመግባቢያ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተለያዩ የስምምነቱን ነጥቦች ማዳከም ጀመሩ" ብለዋል።
አሜሪካ ከኦማን ጋር በመሥራት ከቴህራን ትብብር እምብዛም የማይጠይቅ አማራጭ መተላለፊያ መሥራት ትፈልጋለች።
ኢራን ግን ወሽመጡ በእርሷ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ አቋሟን ገልፃለች።
በጀርመን ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የደኅንነት ጉዳዮች ተቋም ተጋባዥ መምህር የሆኑት ሃሚድሬዛ አዚዚ እንዳሉት "በቴህራን አመለካከት በ60 ቀናቱ ውስጥ የመተላለፊያ ክፍያ ላለማስከፈል ያላት ፍላጎት ውስን ነበር። በፍቃድም ይሁን ያለፈቃዷ መርከቦችን የመቆጣጠር ሚናዋን ለመተው አልፈለገችም።"
ዋሽንግተንም የወታደራዊ ስምሪትን በመጨመር ወይም አማራጭ መተላለፊያ በመፈለግ ያንን የማረድግ ነፃነቷን ማስጠበቅ ነው የፈለገችው።
ለቴህራን ግን ዋናው ጉዳይዋ ከመተላለፊያ የላቀ ነው። ይህም ወሽመጡ ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ቁልፍ ነው።
ወሽመጡን በማስተዳደር የኢራንን የመሪነት ሚና እውቅና እንዲያገኝ አድርጎታል፤ ምክንያቱም "ያለ ኢራን ፈቃድ አማራጭ መስመሩ ቢዘጋጅም ቴህራን እንደ ስትራቴጂያዊ ውድቀት ነው የምታየው" ይላሉ አዚዚ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በተመሳሳይ የሊባኖስን ጉዳይም ማንሳት ይቻላል።
የመግባቢያ ስምምነቱ ኢራን ሄዝቦላህን ጨምሮ ከቀጠናው ተቀናቃኝ ቡድኖች ጋር ያላትን ግንኙነት ባይጠቅስም፣ ስምምነቱ ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ ዘመቻቸውን እንዲያቆሙ እና የሊባኖስን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን እንዲያከብሩ ይጠይቃል።
በርካታ ተንታኞች እንደሚሉት የመግባቢያ ሰነዱ ሊባኖስን ማካተቱ አንደኛው የኢራን ዋነኛ ስኬት ነው።
ይህም ሰፊ የሆነውን ጂኦፖለቲካዊ ግጭት ለመፍታት ወሳኝ መሆኗ መታወቁን የሚያመለክት ነው።
"አሜሪካ ግን ይህንን የተረጎመችው በጣም በጠባቡ ነው። የሊባኖስ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጫ አድርጋ ነው ያየችው። በአገሪቷ የወደፊት ፖለቲካዊ ሂደት ቴህራን የሚኖራትን ልዩ ሚና አልተመለከቱትም" ይላሉ አዚዚ።
በተመሳሳይ ጊዜም ዋሽንግተን ይህንን ለውጥ ጎን ለጎን በሚካሄድ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ መቀየር ፈልጋ ነበር።
ቴህራን ግን በአሜሪካ አሸማጋይነት በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የሚደረገውን ንግግር ኢራንን የማግለል ሙከራ እንደሆነ ነው የተመለከተችው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን ምን ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ልትጠብቅ እንደምትችል እና ከዚህ ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ነገሮችም ግልጽ አይደሉም።
የተለያዩ ሪፖርቶች የማዕቀብ እፎይታ መጠን እና ጊዜ እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት በምላሹ የታገዱባት ሃብቶች እንዲለቀቁ ማድረግ እንደሆኑ አመልክተዋል።
በጣም አወዛጋቢ የነበረው ግን 300 ቢሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታ ፈንድ ሲሆን፣ የትራምፕን ታማኞች ጭምር ያሳሰበ ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በባሕረ ሰላጤው አገራት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በኢራን የሚደረገው የጋራ ግንባታ ዕቅድ ቅድመ ሁኔታዎች ያሉት እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል።
እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የኢራንን የሚሳዔል እና የድሮን ፕሮግራም ለውጥ እና የእስላማዊ ሪፐብሊክ ቀጣናዊ ሚናን መለወጥ የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። እነዚህ በዋናው የመግባቢያ ስምምነት ውስጥ አልተጠቀሱም።
ዘዴው የኢራን የውጭ ፖሊሲ ላይ ጫና ለማሳደር ኢኮኖሚያዊ ጥቅማጥቅሞችን ለመጠቀም የተቀየሰ ይመስላል።
ድርድሩን እንደ ድል የቆጠረችው ኢራንም እያደጉ የመጡትን ስምምነቶች እንደማትቀበል ገልጻለች።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ አዲሱን የትራምፕን ማስፈራሪያ "የጥንካሬ ምልክት ሳይሆን ኢራንን ማንበርከክ ያልቻሉት ጠንካራ ኃይል፣ ማዕቀቦች፣ የዓመታት ማስፈራሪያዎች የገነባችው ፖሊሲ ውድቀት ነው" ብለዋል።
ሆኖም ሁለቱም ወገኖች ራሳቸውን እየተከላከሉ እንደሆነ ያምናሉ። አዲስ የቀውስ ምዕራፍ በመከፈቱ አንዳቸው የፈፀሙት ተመሳሳይ ድርጊት በሌላ መልኩ ሊተረጎም ይችላል።
የፖለቲካ ተመራማሪው ፔፕ "ይህ እየተባባሰ የመጣ ወጥመድ ነው። እያንዳንዳቸው የሚፈፅሙት ውስን ድርጊት ሌላኛውም ውስን ምላሽ እንዲሰጥ ያነሳሳል። ይህ አዙሪት ሁለቱም ወገኖች ሙሉ ወረራ ላይፈልጉ ይችላሉ። ቀስ በቀስ ግን ወደዚያ ይዟቸው ሊገባ ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሆርሙዝ፣ ሊባኖስ እና የመልሶ ግንባታ ገንዘቡ ቴህራን እና ዋሽንግተንን በድርድር ከግጭት በሚወጡበት የጋራ ጥቅም ላይ በማተኮር ፋንታ ከጦርነት በኋላ ያላቸውን ገፅታ ለመቀየር መራር የሆነ ውድድር ውስጥ አስገብቷቸዋል።















