ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ድሮን በርካታ ሰዎች በሚዝናኑበት የሩሲያ ባሕር ዳርቻ ላይ ባደረሰው ጥቃት ሰባት ሰዎች ተገደሉ
የዩክሬን ድሮን በርካታ ሰዎች በሚዝናኑበት የደቡባዊ ሩሲያ ባሕር ዳርቻ ላይ ባደረሰው ጥቃት ሦስት ሕጻናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨ እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው አንድ ቪዲዮ ላይ፤ አንድ ድሮን ገደላማ ቦታ አቅራቢያ ወደሚገኝ የውሃ ክፍል በፍጥነት ሲወርድ እና ሲላተም ያሳያል።
ድሮኑ የወደቀበት ውሃ ውስጥ እንዲሁም በባሕር ዳርቻው አካባቢ በርካታ ሰዎች እየተዝናኑ ይታያል።
በዚህ ጥቃት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር 40 መድረሱን እና 17 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የክራስኖዳር ክልል ገዥ ቬኒያሚን ኮንድራቲዬቭ ተናግረዋል።
ዋና አስተዳዳሪው ዩክሬን "ሆነ ብላ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ማድረሷን" በማንሳት ከስሰዋል። እስካሁን ዩክሬን ስለ ክስተቱ አስተያየት አልሰጠችም።
ከዚህ ቀደም ግን ሁለቱም አካላት የቀረቡባቸውን ሆነ ብሎ ሲቪሎችን ዒላማ የማድረግ ክስ ውድቅ አድርገዋል።
በሥፍራው ጥቃት ያደረሰው ድሮን ምንን ዒላማ እንዳደረገም ግልፅ አይደለም።
አንዳንድ የዩክሬን የቴሌግራም ቻናሎች፣ ድሮኑ በባሕር ዳርቻው የተከሰከሰው "በኤሌክትሮኒክ ውጊያ ሲግናሉ በመጠለፉ ነው" የሚል ምክንያት አቅርበዋል።
በርካታ የዓይን እማኞች ከፍንዳታው በፊት የተኩስ ድምፅ ተሰምቶ እንደነበር ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። ይህ እማኝነት የሩሲያ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ድሮኑን ለመጣል ሲሞክሩ እንደነበር የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ክስተቱ ያጋጠመው አርኪፖ ኦሲፖቭካ የተባለ መንደር አቅራቢያ በሚገኝ የጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ ነው። ሞቅ ያለው አየር ንብረት፣ ረጅም የባሕር ዳርቻዎች ያሉት እንዲሁም የቱሪስት መሠረተ ልማት የተገነቡለት ይህ ሥፍራ በሩሲያ ታዋቂ የእረፍት ቀናት መዳረሻ ነው።
የድሮን ጥቃቱ ከመድረሱ አስቀድሞ የማስጠንቀቂያ ደውል ድምጽ አለመሰማቱን በሥፍራው የነበሩ ጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
እየተዝናና የነበረ አንድ እማኝ "የፀሐይ መከለያ ባላቸው ወንበሮች ተሸፍነን ነበር፤ የት እንደፈነዳ አላየንም" ብሏል። ሌላ ጎብኚ ደግሞ ድሮኑ ጥቃት ሲያደርስ ባይመለከትም "የተኩስ ድምጽ፣ ቀጥሎም ፍንዳታ መስማቱን" ገልጿል።
ሦስተኛው ግለሰብ በበኩሉ "ይህ ሁሉ የሆነው ልጆቼ ፊት ነው። ልጄ በድንጋጤ ህመም አጋጥሞታል" ብሏል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ዩክሬን ወደ ሩሲያ ድንበር ዘልቃ በመግባት የምታደርሳቸው የረጅም ርቀት ጥቃቶች ስኬት አስገኝተውላታል።
በጥቃቶቹ ለወታደራዊ ዓላማ ይውላሉ የምትላቸውን የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች እና የንግድ መጋዘኖችን መትታለች።
ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ አብዛኞቹ የንጹኃንን ሕይወት ቀጥፈዋል። በሳምንቱ መጨረሻ በሩሲያ ከተሞች በደረሱ ጥቃቶችም ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።