እስራኤል ከመስከረም 2016 ጥቃት ጋር በተያያዙ ክሶች ላይ የሞት ፍርድ እንዲተለላፍ የሚፈቅድ ሕግ አጸደቀች

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል፤ በመስከረም 2016 ዓ. ም. በተፈጸመው በሐማስ የተመራው ጥቃት እና ታጋቾችን በጅምላ የመውሰድ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት እንዲተላለፍ እና ለሕዝብ ክፍት የሆነ የፍርድ ሂደት እንዲከናወን የሚፈቅድ ሕግ አጸደቀች።

የእስራኤል ፓርላማ በ95 ድጋፍ እና ያለ ምንም ተቃውሞ ያጸቀደው ይህ ሕግ፤ ባልተለመደ ሁኔታ የመንግሥት እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በጋራ ያዘጋጁት ነው። የተቀሩት 27 የፓርላማ አባላት በስብሰባው ላይ አልተገኙም አልያም ተዐቅቦ አድርገዋል።

ረቂቅ ሕጉን ካዘጋጁት የፓርላማ አባላት አንዷ የሆኑት ዩሊያ ማሊኖቭስኪ "ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዴት የእነዚያን ገዳዮች፣ ደፋሪዎች እና አጋቾች ዐይን እንደሚያዩ ሁሉም ሰው ይመልከት" ሲሉ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የእስራኤል የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች የሞት ቅጣት መርህ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል። በተጨማሪም ግን ስቅይት ተፈጽሞ የተወሰዱ የጥፋተኝነት ኑዛዜዎች ላይ የተመሠረተ "የፍርድ ትዕይንት" ስለማካሄድ ያላቸውን ተቃውሞም በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ የሚመሩ ተዋጊዎች በደቡባዊ እስራኤል በከፈቱት ጥቃት ከ1,200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከሞቱት ውስጥ አብዛኛዎቹ ንጹኃን ናቸው።

ሕጻናት፣ ሴቶች፣ ወንዶች እና የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ተጨማሪ 251 ሰዎች ደግሞ ከተወሰዱ በኋላ ጋዛ ውስጥ በታጋችነት ተይዘዋል።

ከዚህ ጥቃት በኋላ ደም አፋሳሹ የጋዛ ጦርነት የተነሳ ሲሆን እስራኤል በከፈተችው ዘመቻ 72,740 ሰዎች እንደተገደሉ የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከተገደሉት ውስጥ አብዛኛዎቹ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ናቸው።

የእስራኤል ፓርላማ መጋቢት ላይ የሽብር ወንጀል ክስ የሚቀርብባቸው ፍልስጤማውያን ላይ የሞት ፍርድ እንዲተላለፍ የሚፍቅድ ሕግ አጽድቆ ነበር። ይሁን እንጂ ሕጉ ወደ ኋላ ተመልሶ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም።

ይህም ማለት በ2016ቱ ጥቃት የተወነጀሉ ሰዎች ላይ ይህንን ዓይነቱን ፍርድ ለማስተላለፍ ራሱን የቻለ ሕግ ያስፈልጋል ማለት ነው።

ሕጉን የሚደግፉ የእስራኤል ፖለቲከኞች፤ ጉዳዩን ከናዚው የጦር ወንጀለኛ አዶልፍ ሂክማን ጋር በማነጻጸር ታሪካዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍርድ ሂደቶች እንዲካሄዱ ያደርጋል ይላሉ። የሆሎኮስት አርክቴክት የሆነው ሂክማን በአውሮፓውያኑ 1962 በስቅላት የተቀጣ ሲሆን ከዚህ ቀደም በእስራኤል የሲቪል ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ የተላለፈበት ብቸኛው ሰው ነው።

አዲሱ ሕግ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በሆነው አል ቃሳም ብርጌድ ውስጥ እንደሚገኘው ኑክባህ ልዩ ኃይል አባላት ያሉ በጥቃቱ በቀጥታ ለተሳተፉ ሰዎች ልዩ የሕግ ማዕቀፍ ያበጃል።

በእስራኤል የተያዙት የቡድኑ አባላት የሽብርተኝነት፣ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ዘር ማጥፋት ክሶች እንደሚቀርቡባቸው የሚጠበቅ ሲሆን እነዚህ ውንጀላዎችም በሞት ያስቀጣሉ። ጉዳያቸው የሚታየውም ከመደበኛው የወንጀል ፍርድ ሂደት ውጪ በሆነ ሕግ እና በወታደራዊ ፍርድ ቤት ነው።

ይህንን አሠራር የሚቃወሙት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች፤ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች የተከሳሾችን መብቶች የሚያስጠብቁ መሆናቸውን በማንሳት ይከራራሉ። አንዳንድ የፍርድ ሂደቶች ተከሳሾቹ በአካል ሳይገኙ ሊካሄዱ እንደሚችሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ስቅይትን የሚቃወመው 'ፐብሊክ ኮሚቴ አጌነስት ቶርቸር ኢን እስራኤል' የተሰኘው ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሳሪ ባሺ፤ "የጥምር የመንግሥት አባላት ባቋቋሙት ፍርድ ቤት አማካኝነት የጅምላ ግድያ እንዲፈጸም እንደሚጠብቁ ግልጽ አድርገውታል" ብለዋል።

"የመስከረም 26 ወንጀሎች ተሳትፈዋል በሚል ጥርጣሬ የተያዙ ፍልስጤማውያን ስልታዊ እና መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ስቅይት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ እናውቃለን። ስጋቴ፤ ክስ ይመሠረትባቸዋል፤ ስቅይት ተፈጽሞባቸው በተወሰደ ኑዛዜ መሠረት ይገደላሉ የሚል ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።