ስፔን አርጀንቲናን በመርታት ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን አሸነፈች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ስፔን በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠረችው ግብ አርጀንቲናን አሸንፋ የዓለም ዋንጫን አንስታለች።

ፌራን ቶሬዝ ያስቆጠው ጎል ስፔንን ባለ ድል አድርጓል። አርጀንቲና ተጫዋቿ ኤንዞ ፈርናንዴዝ በሁለተኛው አጋማሽ በቀይ ስለወጣ ተጨማሪ ሰዓቱን በ10 ተጫዋቾች ብቻ አካሂዳለች።

ስፔን በመጀመሪያውም በሁለተኛውም አጋማሽ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ስታደርግ ነበር።

በ106ኛው ደቂቃ ቶሬዝ አርጀንቲናዊውን ግብ ጠባቂ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን አልፎ የስፔን ጀግና ሆኗል።

ጨዋታው የተጠበቀውን ያህል የደመቀ አልነበረም። አብዛኛው ሰዓት በግብግብ እና በዳኛ ጣልቃ ገብነት አልፏል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኒው ጀርዚ አቅንተው ውድድሩን ታድመዋል።

ሻኪራ፣ ማዶና እና ጀስቲን ቢበር በጨዋታቸው አጋማሽ ሙዚቃ አቅርበዋል። ይህም 27 ደቂቃ ወስዷል።

ጨዋታው በየመሀሉ እየተቆራረጠ ስለነበር ወጥነት አልታየበትም።

ላሚን ያማል እና ሚኬል ኦያርዛባል በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ሙከራዎች አድርገዋል።

ስፔን በተደጋጋሚ የመሀል ዳኛው ስላቭኮ ቪንሲ ጥብቅ እርምጃ አልወሰዱም ብላ ወቅሳለች።

አርጀንቲናዊው ግብ ጠባቂ በተደጋጋሚ ኳስ በማዳን ብቃቱን አሳይቷል። የላሚን ያማልን ነጻ ምት ጨምሮ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች አድኗል።

አርጀንቲና ግብፅ እና እንግሊዝን አሸንፋ ለመጨረሻው ግጥሚያ ብትደርስም በስፔን ተረትታለች።

ስፔን በሴቶችም በወንዶችም የዓለም ዋንጫ አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

ስፔን የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከኬፕ ቨርዴ ጋር ያለ ጎል በመለያየት ብትጀምርም ጉዟዋን በአሸናፊነት አጠናቃለች።

ስፔን ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ያሸነፈችው በአውሮፓውያኑ 2010 በደቡብ አፍሪካ ነው።

በግማሽ ፍጻሜ ፈረንሳይን አሸንፈው ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን አንስተዋል።

አሠልጣኝ ሉዊስ ላ ፉዌንቴ ብሔራዊ ቡድኑን በብቃት መርተዋል።

በዩሮ 2024 በበርሊን በተካሄደው የዋንጫ ፍልሚያ እንግሊዝን እንዲያሸንፉ አስችለዋል።

አርጀንቲና በስፔን ተጫዋቾች ላይ በተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ስትፈጽም በትዕግስት ማሳለፍ ነበረባቸው።

በተለይ ፈርናንዴዝ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ 10 ተጫዋች የቀረውን የአርጀንቲና ቡድን የማሸነፍ ዕድላቸው ሰፍቷል።

የ2026 የዓለም ዋንጫ የሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ይሆናል።

የ39 ዓመቱ ሜሲ አብዛኛውን የግጥሚያውን ክፍል ያሳለፈው በተረጋጋ ሁኔታ ነው።

በአጠቃላይ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ስምንት ግብ አስቆጥሯል። በተለይም እንግሊዝን 2 ለ 1 ባሸነፉበት ጨዋታ በቡድኑ ያለውን ጉልህ ሥፍራ በግልጽ አሳይቷል።

በመጨረሻው ጨዋታ ስፔኖች ሜሲን ብዙም አላንቀሳቀሱትም። አደገኛ ከሆነው የግብ አካባቢ ማራቅ ችለዋል።

አርጀንቲና ስፔንን ተስፋ ማስቆረጥ ላይ አተኩራ ጨዋታውን አካሂዳለች።

ሆኖም ሙከራው ሳይሳካ ቀርቶ ስፔን ዋንጫውን አንስታለች።