ኢትዮጵያ የሱዳን ኃይሎችን ለማሸማገል ለምን አሁን ጥሪ አቀረበች?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ሰንበት ብለዋል። ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር እየተፋለመ ያለው ጦር ሠራዊት ኢትዮጵያን ለተቀናቃኙ ድጋፍ በመስጠት ይከስሳል። ኢትዮጵያም ሱዳን አማጺያንን ትረዳለች ስትል በተደጋጋሚ ትወቅሳል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየተበላሸ ሄዶ በቅርቡ አንዳቸው የሌላኛውን ዲፕሎማቶች አስከ ማባረር በመድረስ ግንኙነታቸውን ወደ ማቋረጡ አፋፍ ላይ ደርሰዋል።

ነገር ግን ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ በአረብኛ ቋንቋ ባጋሩት ጥሪ ኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ወገኖችን በማቀራረብ ለሱዳን ሰላም ለማውረድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኗን አሳውቀዋል።

ይህንን ጥሪ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ሌሎች የሱዳን ቡድኖች ሲቀበሉት በሱዳን ጦር ኃይል የሚመራው የሱዳን መንግሥት ግን የኢትዮጵያን ገለልተኝነት በማንሳት ውድቅ አድርጎታል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰላም የማውረድ ፍላጎት እና ጥሪ የተለያዩ ወገኖች አስተያየት እየተሰጡበት ይገኛል። ለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ ሰሚ ጆሮ የሚያገኝበት ዕድል ይኖር ይሆን? ለምንስ በዚህ ሰዓት ጥሪውን ማቅረብ አስፈለገ? ቢቢሲ ሦስት የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲሁም ቀጣናውን በቅርበት የሚያጠኑ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዳርስከዳር ታዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳን ተቀናቃኝ ቡድኖች ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ የቀረበው በትክክለኛ ጊዜ ነው ብለው ያምናሉ። ምክንያታቸውንም እንዲህ ይዘረዝራሉ...

ወቅቱ "ሱዳንን የሰላም ጥረት ወይም ድርድር መደገፍ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ይመስለኛል። አንደኛ ሱዳን ላይ የግብፅ ሚና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ አለ። ሁለተኛ ሱዳን በአሁኑ ጊዜ አደገኛ ደረጃ ላይ የደረሰችበት በመሆኑ፣ እየተፈጠሩ ካሉ ጥምረቶች አንጻር ሱዳንን ማትረፍ ከተቻለ መሞከር ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

ነዋሪነታቸው በዩናይትድ ኪንግደም የሆነው እና የቀጣናውን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉት አቶ አብዱራህማን ሰይድ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ምናልባት በኢትዮጵያ ይደገፋል ሚባለው "የፈጥኖ ደራሹ ኃይሉ መዳከምን ተከትሎ የመጣ ይመስለኛል" ይላሉ።

አቶ አብዱራህማን አክለውም የሰላም ጥሪው የቀረበበት ጊዜ ሲታይ የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ክሶች እያቀረበ ባለበት ጊዜ የተሰማ ነው። በኢትዮጵያ በኩልም ተመሳሳይ ክስ በሱዳን ላይ ሲቀርብ ቆይቷል።

"እና ግንኙነቶቹ በጣም በሻከሩበት ጊዜ የቀረበ የአሸማጋይነት ጥሪ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ለአደራዳሪነት የሚሆን አቋም የለም" በማለት ኢትዮጵያ በሱዳን ጦር በኩል በገለልተኛነት አትታይም ይላሉ።

አክለውም "ኢትዮጵያ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋራ ሆነው በመሥራት እና የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ትይዩ መንግሥት እንዲመሠረት ትደግፋለች" በሚል የጄነራል አል ቡርሐን መንግሥት ጦር በበጎ የማይመለከታት በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሳካት ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

ነዋሪነታቸው ኖርዌይ የሆኑት የፖለቲካ ኢኮኖሚ አጥኚው ዶክተር ደርቤ መኮንን በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ በዚህ ወቅት ሊቀርብ ከቻለባቸው ቁልፍ ምክንያቶች መካከል "ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጋሻ ፍለጋ ላይ በመሆኗ ነው" ብለው ያምናሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ለአሁኑ ጥሪ ባለፉት ወራት የተከሰቱ ነገሮችን በዳራነት መመልከት ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እና በጄኔራል አል ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት አስከ አፍሪካ ኅብረት እና የመንግሥታቱ ድርጅት የደረሰ ክስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በድንበር አካባቢዎች ያሏቸውን የቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን በመዝጋት ዲፕሎማቶችን አባርረዋል። ይህ እርምጃም ለወራት በክስ ውስጥ የቆዩት አገራት ግንኙነት እየተባለሻ ወደ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ያመለከተ ነው።

ዓመታትን አስቆጥሮ ሱዳንን ከባድ ቀውስ ውስጥ የከተተው ጦርነት በተለያየ ጊዜ የተለያየ አቅጣጫ እየያዘ ባለፉት ሳምንታት የሱዳን ጦር ኃይል በአንዳንድ አካባቢዎች የበላይነትን እየያዘ ይገኛል። እንዲሁም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁልፍ ወታደራዊ መሪዎች እየከዱ ወደ ሱዳን ጦር እየተቀላቀሉ ነው።

እነዚህ ሁኔታዎች "ከነባራዊው ተጨባጭ መሬት ላይ እየተካሄደ ካለው ሁኔታ አንጻር ሲታይ የአል ቡርሐን የሱዳን ወታደራዊ ኃይል እየገፋ እየመጣ ነው" ይላሉ።

ነገር ግን ያለውን ሁኔታ ሰፋ አድጎ በመመልከት ኢትዮጵያ አሁን የአደራዳሪነት ጥሪ ያቀረበችባቸውን ሌሎች ምክንያቶች መጥቀስ እንደሚቻል እና ዋነኛው ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ለምታቀርበው ክስ "ቀድሞ የዲፕሎማሲ ጋሻ (ሺልድ) ማዘጋጀት ስለሚያስፈልግ ይመስለኛል ኢትዮጵያ የአስታራቂነት ሐሳብን ያነሳችው" ይላሉ ዶ/ር ደርቤ።

ሁለተኛ ምክንያት ደግሞ ኤልአላሚን ላይ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ያደረጉት ስምምነት "ኢትዮጵያን የበለጠ አፍኖ የማቆየት ስምምነት ነው" የሚሉት ዶ/ር ደርቤ፤ ያንን ስብስብ ለመስበር ሱዳን ደካማዋ መግቢያ በር ናት ይላሉ።

የግብፅ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን መሪዎች ባለፈው መስከረም መጨረሻ ላይ በቀይ ባሕር እና አባይን በተመለከተ በተለይ የግብፅ እና የኤርትራን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ የአቋም መግለጫ አውጥተው ነበር።

"ሱዳን በጦርነት ተዳክማለች፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ ከድንበር አዋሳኝነትም አንጻር የቀረበችም ስለሆነ ኢትዮጵያ በዚህ መካከል ገብታ ሁለቱን አካላት አስታርቃ ያንን ስብስብ ለማዳከም ወይም ደግሞ ቢያንስ አንዱን አባል ከውስጥ ለመነጠል የምትጥርበተ መንገድ ይመስለኛል።"

ዶ/ር ደርቤ ለኢትዮጵያ የሽምግልና ጥሪ ሌለው ምክንያት የሚሉትም ደግሞ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተፈጠሩ ችግሮችን በመቀልበስ ከታጣቂ ኃይሎቹ ውጪ የሆነ "ሲቪል መንግሥት በእሱ ምትክ ወይም በእሱ ጥላ ስር እንዲመጣ እና ሕጋዊነትን እንዲያገኝ ለማድረግ የሚደረግም ጥረት ሊሆን ይችላል" ብለው ያምናሉ።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በጄነራል ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ባለፉት ዓመታት በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና ውድመቶች በተደጋጋሚ ይከሰሰሳል።

ይህም አርኤስኤፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ወንጀለኛ ሊታይ የሚችልበት አጋጣሚ ቀጣይ ሊሆን ይችላል። የሱዳን ጦር ሠራዊትም ኢትዮጵያ ኃይሉን በመደገፍ በአገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች ሲል ቆይቷል።

በቅርቡም በዋና ከተማዋ ኻርቱም ላይ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት መነሻው ኢትዮጵያ መሆኗን በመግለጽ ሱዳን ከከሰሰች በኋላ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሸማጋይነት ጥሪ የተሰማው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ገለልተኛ አቀራራቢ ልትሆን የምትችልበት ዕድልን አንዳንዶች ጥያቄ ውስጥ ያስገቡታል።

ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ እንደሚሉት ክሶች ከሁለቱም ወገን ሊሰነዘሩ ቢችሉም "ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት አገር ይሄን ጥሪ ማቅረብ አለባት። ከሁሉም በኩል በጎ ምላሽ ካገኘች ደግሞ ጉዳዩን ማስተባበር የጎረቤት አገር ኃላፊነትም ይመስለኛል" ይላሉ።

"ነገር ግን ምን ያህል ትታመናለች የሚለው በተፋላሚ ኃይሎቹ ዕይታ እና ከእነሱ ጀርባ ካሉ ኃይሎች የሚመጣ ነው ብዬ አስባለሁ። ቢሆንም ግን ለሱዳን በዚህ ሰዓት ከኢትዮጵያ የተሻለ አደራዳሪ ይኖራል ብዬ አላስብም" በማለት በሱዳን ሰላም ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ቁልፍ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽምግልና ጥሪ እንደተሰጋው በሁሉም የሱዳን ኃይሎች ተቀባይነት አላገኘም። የሱዳን ጦር ኃይል የኢትዮጵኣን ወገንተኝነት እንደምክንያት በመጥቀስ ጥሪውን ውድቅ አድርጎታል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ ታሲስ የሚባለው የኃይሉ ፖለቲካዊ አጋር እና የተለያዩ የሱዳን ቡድኖች ስብስብ ሲቪል ዲሞክራቲክ አሊያንስ የተባለው ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለውታል።