ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ቀጥሎ ምን ሊከሰት ይችላል?
የፓኪስታን ልዑካን ቴህራን ሲገቡ አሜሪካ ከኢራን ጋር ለሁለተኛ ዙር ድርድር ለመቀመጥ እየተነጋገረች መሆኑ ተሰምቷል።
በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለ40 ቀናት ከተካሄደ በኋላ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሷል።
ነገር ግን ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በፓኪስታን ለሃያ ሰዓታት ያህል የተደረገው ውይይት ያለ ምንም ስምምነት ተቋጭቷል።
የድርድሩ ያለስምምነት መጠናቀቅን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ አዲስ እርምጃ እንደሚወስዱ ይፋ አድርገዋል።
ይህም ለዓለም የነዳጅ እና ጋዝ ገበያ ወሳኝ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለማስከፈት የኢራን ወደቦችን መዝጋት የሚል ነበር።
የመጀመርያው ዙር ንግግር ያለምንም ስምምነት መጠናቀቁን እንዴት ልናየው እንችላለን? ቀጣይ ዙር ንግግርስ ፍሬ ያፈራ ይሆን? አሜሪካ እና ኢራን የተጠና እና የተመጠነ ግጭት ውስጥ ይቆያሉ ወይስ መከላከል ወደማይቻል ሰፊ ጦርነት ያመራሉ?
ቀጣዮቹ አራትን ቢሆኖች በመጪው ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።
1. ደካማ የተኩስ አቁምን "እንደ ጊዜ መግዣ" መጠቀም
ለስድስት ሳምንታት ውጊያ ከተካሄደ በኋላ አሜሪካ እና ኢራን የደረሱበት የተኩስ አቁም ቀውሱን ለመቆጣጠር ፈቃደኝነት መኖሩን ያሳያል።
ይሁን እንጂ ገና ከመጀመርያው በበርካታ ግርታዎች የተሞላ ነበር። የሚነሱት ጥያቄዎች በተኩስ አቁሙ ላይ የተቀመጡትን ነጥቦች ትርጓሜ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ስምምነቱ የትኞቹን አገራት እንደሚያካትት፣ የሚሸፍናቸው ዓላማዎች እንዲሁም 'የተኩስ አቁም ጥሰት' ምን ማለት ነው? የሚለው አንዳንድ ታዛቢዎች ስምምነቱን ከዘላቂ ማዕቀፍ ይልቅ እንደ ጊዜ መግዣ አድርገው እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል።
መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው 'ፋውንዴሽን ፎር ዲፌንስ ኦፍ ዲሞክራሲስ' ባልደረባ የሆኑት ቤህናም ቤን ታሌብሊ "አስቀድሞ ጦርነት ከተጀመረ ስምምነት ላይ የመደረስ ዕድሉ ለዜሮ የቀረበ ነው" ይላሉ።
"እነዚህ ጉዳዮች አሜሪካ እና እስላማዊው ሪፐብሊክ ለዓመታት ያልተስማሙባቸው የመርሆች፣ የአቋም እና የፖሊሲዎች ስብስብ ናቸው፣ እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱ እነዚህን ልዩነቶች ከመቀነስ ይልቅ አጠናክሮታል" ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱም ወገኖች የሚገኙ ባለሥልጣናት የሚናገሯቸው እርስ በርስ የሚጋጩ መግለጫዎች ሁኔታውን የበለጠ ስጋት የሚጭር አድርገውታል።
በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ወገን ያሉ ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተደጋጋሚ መጣሱን ሲገልጹ፣ አሜሪካ እና እስራኤል ግን የገቡት ስምምነት በጣም ውስን መሆኑን መናገር መርጠዋል።
እነዚህ የትርክት መለያየቶች በመካከላቸው ያለውን አለመተማመን እና በተኩስ አቁሙ ዘላቂነት ላይ የተፈጠረውን ጥያቄ እያጠናከሩት ሄደዋል።
ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ካላመጡ፣ የተኩስ አቁሙ ጊዜን ከመግዛት ያለፈ አይሆንም።
ይህም ተፋላሚ ወገኖች ለአፍታ እረፍት ወስደው እንዲያገግሙ፣ እንደገና አቅማቸውን እንዲያሰባስቡ፣ አቋማቸውን እንደገና እንዲገመግሙ እና ለቀጣዩ ምዕራፍ እንዲዘጋጁ ያስችላቸዋል።
ይህ ሁኔታ አንዱ ወገን ከአሁኑ ሁኔታ ብዙም ጥቅም እያገኘ እንዳልሆነ እና ትርጉም ያለው ጫና ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከደመደመ የበለጠ አሳማኝ ይሆናል።
ለምሳሌ፣ አሜሪካ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን የኃይል ማመንጫዎችን፣ ድልድዮችን ወይም የኤነርጂ ተቋማትን መደብደብ እንደ አማራጭ ልትመለከተው ትችላለች።
እንዲህ ያሉ ጥቃቶች የአጭር ጊዜ ጫና ሊፈጥሩ ቢችሉም፣ ሰፊ የሰብዓዊ እና የኢኮኖሚ ቀውሶችን በማምጣት ከኢራን ጠንካራ ምላሽ ሊያስከትሉ ይችላሉ።
በድርድሩ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያላት እስራኤልም በተመሳሳይ ከበድ ያለ ተጽዕኖ ልታሳድር ትችላለች።
"እስራኤል ድርድሩ ውስጥ የተሳተፉትን ጨምሮ ኢራናውያን ግለሰቦችን እና ባለሥልጣናትን ልትገድል ትችላለች" ሲሉ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ የሆኑት ሃሚሬዛ አዚዚ ተናግረዋል።
"የዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን የመዝጋት ፖሊሲ ተፋላሚ ወገኖች ሳያስቡበት እንኳ የግጭት አደጋን ይጨምራል" ሲሉ አክለዋል።
ዳግም ግጭት የመቀስቀስ ዕድሉ ከግምት ውጭ ባይሆንም፣ ይህ የሚከሰት ከሆነ ግን ሰፊ የሆነ ቀጣናዊ ግጭት እና የምጣኔ ሃብት ጫና የመቀስቀስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ይህንን ሁኔታ የመከሰት ዕድሉ አነስተኛ ነው።
2. "የእጅ አዙር ጦርነት"
አንዱ እና ምናልባትም በጣም ከሚጠበቁት መካከል የሆነው ወደ "ተመጠነ እና የተጠና ግጭት" መመለስ ነው።
ይህ ማለት ግጭቱ ወደ ለየለት ጦርነት ባይደርስም ተፋላሚ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ከወታደራዊ እርምጃ አይቆጠቡም ማለት ነው።
ይህ በመሠረተ ልማት፣ በወታደራዊ ዒላማዎች ወይም በአቅርቦት መስመሮች ላይ የተመጠኑ ጥቃቶችን እየፈጸሙ መቀጠልን ሊያካትት ይችላል።
የእጅ አዙር ውጊያ ተሳታፊዎች ሚና በዚህ ውስጥ የበለጠ ጉልህ ይሆናል።
በኢራቅ ወይም በቀይ ባህር ውስጥ በኢራን በሚደገፉ ቡድኖች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መጨመር፣ በእነዚህ ተፋላሚ ወገኖች ላይ የአሜሪካ ጫና ቢጨምርም የግጭቱን መልክዓ ምድር በቀጥታ ሊያሰፋ ይችላል።
አንዳንድ ተንታኞች ይህንን ሁኔታ "የእጅ አዙር ጦርነት" ብለው ይገልጹታል።
"ሁለቱም ወገኖች ወደ ሙሉ ጦርነት ሳይገቡ አማራጮቻቸውን እና ግፊት የመፍጠር አቅማቸውን ተጠቅመው ሌላኛው ወገን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይፈልጋሉ" ሲሉ ሃሚሬዛ አዚዚ ለቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያ ተናግረዋል።
"የተኩስ አቁሙ ከተጣሰ፣ ኢራን በአጋሮቿ በተለይም በየመን አዳዲስ እርምጃዎችን የመውሰድ ዕድሏ ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታል" ሲሉ አክለዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ያለ አደጋ የሚሆን አይደለም። ውጥረቶች እየጨመሩ ሲሄዱ፣ የስሌት ስህተት የመከሰት እድሉ ይጨምራል፤ እና ሁለቱም ወገኖች ወደ ለየለት ግጭት ለመግባት ባያስቡም፣ አንድ የተሳሳተ እርምጃ ግጭቱን መቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ሊወስደው ይችላል።
3. ይፋ የማይደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች
በፓኪስታን የተደረገው ውይይት ቢከሽፍም፣ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ አብቅቶለታል ወይም ድርድሮች ተጠናቅቀዋል ብሎ መደምደም አይቻልም።
በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚደረገውን ድርድር የምታመቻቸው ፓኪስታን፣ ከቴህራን እና ዋሽንግተን የሚመጡ መልዕክቶችን በማቀባበል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥረቷን እንደምትቀጥል ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ጊዜ፣ እንደ ኳታር፣ ኦማን እና ሳዑዲ አረቢያ እና ግብፅ ያሉ አሸማጋዮች ግጭቱ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን በተመለከተ ለሚነሱ ስጋቶች ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። ይህንን
ለመስጠት፣ እንደ ግንኙነት መስመር ሆነው በማገልገል እና ቀውሱ በድንገት እንዳይባባስ ለመከላከል በመፈለግ ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ዋናው ነጥብ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያሉትን መሠረታዊ ክፍተቶች እንዴት ማጥበብ ይቻላል የሚለው ላይ የተመሰረተ ነው።
የአሜሪካ ባለ 15 ነጥብ የመደራደሪያ ሀሳብ እና ኢራን ያቀረበችው ባለ 10 ነጥብ መደራደሪያ ሁለቱም ወገኖች አሁንም ወደ መካከል ከመምጣት ይልቅ የራሳቸውን ማዕቀፍ በሚያስቀድሙ አቋሞች ላይ ተቸንክረው ያሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
ስለዚህ አዲስ ውይይት ሊደረግ ቢችልም፣ ፈጣን እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት መጠበቅ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእውነታው የራቀ ይመስላል።
4. ቀጣይነት ያለው የባሕር ላይ እገዳ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የባህር ኃይላቸው ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡም ሆነ የሚወጡ መርከቦች ላይ እገዳ ለመጣል ማቀዱን አስታውቀዋል።
ይህም ነዳጅ ጫን መርከቦች በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል እንዳያልፉ ይከላከላል።
በተጨማሪም በባህረ ሰላጤው በኩል ለማለፍ ለኢራን ቀረጥ የሚከፍሉ መርከቦችን እንደሚያግድ ዝቷል።
ይህ እርምጃ ኢራን ከነዳጅ የምታገኘውን ገቢ ለማሳጣት፣ ኢኮኖሚዋን ለማነቅ እና በተመሳሳይ ጊዜ የአሜሪካን ዋናተቀናቃኝ ቻይናን የኢራን ነዳጅ ዋና ገዢ በመሆኗ ለማጥቃት ያለመ ይመስላል።
ምንም እንኳ ኢራን ረዥም የባሕር ዳርቻ ያላት ቢሆንም "በቂ የሆነ የስለላ፣ የክትትል እና የቅኝት ኃይሎች ከተመደቡ የእስላማዊ ሪፐብሊክ ወደቦችን ማገድ በጣም ውጤታማ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ቤህናም ቤን ታሌብሉ ተናግረዋል።
"የእንደዚህ ዓይነት እርምጃ ውጤት መንግሥት ዋናውን ሸቀጡን ወደ ውጭ የመላክ አቅሙን ማሳጣት ይሆናል።"
ነገር ግን ሌሎች ተንታኞች ይህ ዓይነቱ ፖሊሲ አሜሪካ ላይ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል። ይህም ወታደራዊ ኃይሏን ወደ ኢራን የበለጠ በማቅረብ ለጥቃት ተጋላጭ ያደርጋታል።
ከዚህም በላይ ዕቅዱ ውጤታማ እንዲሆን የባህር ኃይሎች ለረጅም ጊዜ በኢራን ድንበር አቅራቢያ መሰማራት አለባቸው፣ ይህም ከፍተኛ ወጪ ያስከትላል።
እንዲህ ዓይነቱን ፖሊሲ መጠበቅ የዓለም የነዳጅ እና የኤነርጂ ዋጋ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። እንዲሁም የባብ አል-ማንደብ የባህር ወሽመጥን ለማወክ የሁቲዎች ጣልቃ ገብነት የመከሰቱን እድል ይጨምራል፣ ይህም የነዳጅ ዋጋን የበለጠ ሊያንረው ይችላል።
በቀጠናው ላይ የሚታይ አዲሱ የዓለም ስርዓት መዋቅራዊ አለመረጋጋት
በአሜሪካ እና በኢራን ተደጋጋሚ ድርድር እና ጦርነት ማስተዋል የተቻለው በሰላም እና በግጭት መካከል ያለው መስመር ከመቼውም ጊዜ በላይ መደብዘዙ ነው።
የፓኪስታን ውይይት አለመሳካት የዲፕሎማሲ ጥረት ተንጠፍጥፎ ማለቁን አያሳይም፤ እንዲሁም ወደ ሰፊ ጦርነትሊገባ መሆኑንም አያመለክትም። ይልቁንም የደበዘዘው መስመር መቀጠሉን ያመለክታል።
"ሁለቱም ወገኖች ይህ ጦርነት እንዲያበቃ ቢፈልጉም፣ ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሆን አይመስልም" ሲሉ ሃሚሬዛ አዚዚ ተናግረዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ታክቲካዊ ውሳኔዎች፣ የደኅንነት ጥያቄዎች እና በመሬት ላይ ያሉ ጥቃቅን ጉዳዮች እንኳን በቀውሱ አጠቃላይ አቅጣጫ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
ይህ ብዙ ተንታኞች በቀጣናው ውስጥ ስላለው "የመዋቅር አለመረጋጋት" እንዲናገሩ አድርጓቸዋል።
ይህም የጨዋታው ሕጎች ሙሉ በሙሉ ያልተገለጹበት እና ውጤቱም ሊገመት የማይችልበት ሁኔታን ፈጥሯል።
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ወቅት ምናልባትም በጣም ትክክለኛው መግለጫ ኢራን እና አሜሪካ ጦርነት እና ድርድር በአንድ ጊዜ የሚካሄድበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ነው። ሁለቱም ወገኖች በወታደራዊ መሣሪያዎቻቸው ላይ መመካታቸውን ቀጥለዋል፣ የዲፕሎማሲ በሮችንም በከፊል ክፍት አድርገው ይቆያሉ።