የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ባደረጉት አወዛጋቢ ጉብኝት ምክንያት ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ

የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, Gallo via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቀድሞ አገሪቱ መሪዎች ወደ ውጭ አገራት የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ላይ "የበለጠ ግልፅነት" እንዲኖር የሚያደርግ አዲስ ሕግ እንዲወጣ ጠየቁ።

ሚኒስትሩ ይህንን ምክረ ሀሳብ ለአገሪቱ ፓርላማ ያቀረቡት፣ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ባለፈው ወር ወደ ሕንድ ያደረጉትን አወዛጋቢ ጉዞ ተከትሎ ነው።

ዙማ በዚህ ጉብኝታቸው ከሥልጣን እንዲወርዱ አንዱ ምክንያት በሆነው ትልቅ የሙስና ቅሌት ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ነጋዴ አግኝተዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት የንግድ ሰው ከሆኑት አጃይ ጉፕታ ጋር መገናኘታቸው ቁጣ ቀስቅሷል። አንድ የአገሪቱ ሚኒስትርም ዙማ ደቡብ አፍሪካ ላይ "የመሃል ጣታቸውን አውጥተዋል" ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸው ነበር።

ከአስር ዓመት ገደማ በፊት፣ የጉፕታ ወንድማማቾች በወቅቱ ፕሬዝዳንት ከነበሩት ዙማ ጋር በነበራቸው ቅርብ ግንኙት ትርፍ አግኝተዋል እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ወንድማማቾቹም ሆነ ዙማ ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል።

የጉፕታ ቤተሰብ አባላት በግዙፍ የማጭበርበር ድርጊት ውስጥ ተሳትፈዋል የሚለው ውንጀላ በአገሪቱ የዳኝነት ኮሚሽን መመርመር ሲጀመር በአውሮፓውያኑ 2018 ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።

ኮሚሽኑ 2022 ላይ፣ ጃኮፕ ዙማ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ረገድ ዋነኛ ሚና የነበራቸውን ሚኒስትሮች በጉፕታ ቤተሰቦች ትዕዛዝ ሲሾሙ እና ሲሽሩ ነበር የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

በመጨረሻም ግን የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት በአጃይ ጉፕታ ወጥቶ የነበረው የእስር ማዘዣ እንዲነሳ አድርገዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጉፕታ ቤተሰብ ሁለት ታናሽ ወንድማማቾች የሆኑት አቱል እና ራጄሽ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሄደዋል። ደቡብ አፍሪካ ወንድማማቾቹ ተላልፈው እንዲሰጧት ያቀረበችውን ጥያቄ ኤምሬቶች አልተቀበለችውም።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ጃኮብ ዙማ ሲመሩ ከነበሩት 'አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ' (ኤኤንሲ) ፓርቲ ተባርረዋል። አሁን 'እምኮንቴ ዌ ሲዝዌ' (ኤምኬ) የተባለውን ተቃዋሚ ፓርቲ ይመራሉ።

የ84 ዓመቱ ዙማ በሕንድ ጉብኝታቸው ከአጃይ ጉፕታ ጋር ቤተ መቅደስ ውስጥ ፎቶ ተነስተዋል። በሕንድ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት አኒል ሶክላልም ከሁለቱ ጋር በፎቶው ታይተዋል።

ይህንን ፎቶ ተከትሎ ዲፕሎማቱ ወደ አገራቸው የተጠሩ ሲሆን እርሳቸው ግን ጥፋት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሮናልድ ላሞላ፣ መስሪያ ቤታቸው የቀድሞ የአገር መሪዎች የሚያደርጓቸውን የውጭ አገራት ጉዞ የፕሮቶኮል ሂደት የተመለከተ ሕግ እንዲወጣ የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብ ለፓርላማ እና ለፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ማቅረቡን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ረቡዕ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ "በተገቢው ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም መልካም ስም ላይ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ ወይም በደህንነት ላይ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ስጋቶች ተያያዥ አስቀድሞ ለመገምገም" እንዲቻል ስለሚያደርጓቸው ጉዞዎች "ሙሉ ዝርዝር ማቅረብ" ነበረባቸው ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዙማ አወዛጋቢ የውጭ አገር ጉዞ ሲያደርጉ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ዓመት ሞሮኮን በጎበኙበት ወቅት ውዝግብ በሚነሳበት መሬት ላይ የአገሪቱን የባለቤትነት ጥያቄ ደግፈው ተናግረው ነበር። ይህ ንግግራቸው ከደቡብ አፍሪካ አቋም የተቃረነ ነበር።

ዙማ ወደ ሞሮኮ የተጓዙት የሚመሩትን ተቃዋሚ ፓርቲ ወክለው ቢሆንም ከአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተገናኙበት ወቅት ከደቡብ አፍሪካ ሰንደቅ ዓላማ ፊት ለፊት ቆመው ፎቶ ተነስተዋል።

ደቡብ አፍሪካ ጉዞውን ያወገዘች ሲሆን ይፋዊ የዲፕሎማሲ ተቃውሞንም ሞሮኮም አቅርባለች።