በምዕራብ ወለጋ ስለተቃጠሉት ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ቢቢሲ በሳተላይት ምሥሎች ያደረገው ማጣራት ምን ያሳያል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ከተማ አቅራቢያ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለ ጥቃት ከዘጠኝ ያላነሱ ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መቃጠላቸውን ቢቢሲ ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥል አረጋገጠ።

ታጣቂዎች ባለፈው እሑድ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም. በደፈጣ እንደፈፀሙት በተገለፀው በዚህ ጥቃት፣ ከስምነት ያላነሱ ሾፌሮች ታግተው መወሰዳቸውን የኢትዯጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ገልጿል።

ቢቢሲ የተመለከታቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በርካታ የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎችን የሚያሳዩ ሲሆን ከሳተላይት መረጃዎች ጋር በማናበብ በሠራው ትንታኔ በእርግጥም ጥቃቱ በዚያ አካባባቢ በተጠቀሰው ቀን ስለመፈጸሙ አመላካች መረጃዎችን አግኝቷል።

የተቃጠሉ ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች (ቪዲዮዎች) በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተዘዋውረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ነዳጅ ጭነው ከጊምቢ በነጆ አድርገው ወደ አሶሳ በማቅናት ላይ እንደነበሩ የአካባቢው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ስለመፈጸሙ የተሰማው በመኪኖቹ ላይ የደረሰውን ቃጠሎ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መዘዋወር ከጀመሩ በኋላ ነው። ነገር ግን ቪዲዮዎቹ በእሳት የተቃጠሉ ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች (ቦቴዎች) ከማሳየት ውጪ ምንም ዓይነት መረጃ አልነበራቸውም።

ስለዚህም ቢቢሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ምሥሎችን በመፈተሽ በተንቀሳቃሽ ምሥሎቹ ላይ የሚታዩ አመላካቾችን መሠረት በማድረግ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ስፍራ ለመለየት ችሏል።

ቢቢሲ የሳተላይት ምሥሎችን በመጠቀም ለማመሳከር ባደረገው ጥረት ቪዲዮዎቹ በተባለው ቦታ የተቀረጹ እና ጥቃቱም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ እንደተፈጸመ ማረጋገጥ ችሏል።

የሳተላይት ምሥሉ እንደሚያሳያው ጥቃቱ የተፈጸመው ሁዋ የተባለ ወንዝ አካባቢ ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎቹ በቅርቡ ወደ ሚገኘው ዶንጎሮ የተባለው ስፍራ እያመሩ ነበር።

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ፣ ተሽከርካሪዎቹ ሰብሰብ ብለው በሚጓዙበት ወቅት ደንጎሮ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ገጠራማ ስፍራ ላይ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነዳጅ የጫኑት ከባድ ተሽከርካሪዎች ቢያንስ ዘጠኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሌሎች የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎችም እንዳሉ መረጃው እንዳላቸው ገልፀዋል።

ታጣቂዎች መኪኖቹን በተኩስ አስቁመው አሽከርካሪዎቹን አፍነው እንደወሰዷቸው እና ተሽከርካሪዎቹን በእሳት እንዳቀጣጠሉ ከጥቃቱ ካመለጠ አንድ አሽከርካሪ ማረጋገጣቸውንም አብራርተዋል።

ነዳጅ ከጫኑት ውስጥ "ቢያንስ ሦስቱ ሙሉ በሙሉ ሌሎቹ ደግሞ ጋቢናቸው ተቃጥሏል" ያሉት አቶ ሰለሞን፣ የጫኑት ነዳጅ ያልተቃጠለባቸው ተሽከርካሪዎች መኖራቸውንም አክለዋል።

ቢያንስ ስምንት አሽከርካሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን እና ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችልም ነው የተናገሩት።

ማኅበሩ ስለተፈፀመው ጥቃት ከእገታ ካመለጠው አባሉ እንዳረጋገጠ ጉዳዩን ለፀጥታ አካላት ማስታወቁን እና የመንግሥት ኃይሎች ወዲያው ወደ ቦታው መድረሳቸውን ገልፀዋል።

አንድ የምዕራብ ወለጋ ዞን የመንግሥት አመራር፣ ነዳጅ ጭነው ወደ አሶሳ ሲጓዙ የነበሩት ከባድ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ቢያንስ 11 እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዞኑ ሳሎ አሳቢ ወረዳ ላይ በተፈፀመው ጥቃት፣ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን እና አሽከርካሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን የዞኑ አመራር አረገግጠዋል።

ይሁን እንጂ ስለታገቱት አሽከርካሪዎች ቁጥር እንደማያውቁ ገልፀዋል። የመንግሥት ኃይሎች ወደ ስፍራው መድረሳቸውን ተከትሎ ከጉዳት የተረፉ ሌሎች ብዙ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

አስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። ያነጋገርናቸው ምንጮችም ጥቃቱን ስለፈፀሙ ታጣቂዎች ማንነት በግልፅ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

የዞኑ አመራር አባል የሆኑት ግለሰብ፣ በአካባቢው መንግሥት 'ሸኔ' የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም በይፋ የሚታወቅ ስም የሌላቸው በቡድን የተደራጁ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን አረጋግጠዋል።

ነገር ግን ታጣቂዎቹ "ቋሚ ቦታ የሌላቸው እና ክፍተቶችን እየተጠቀሙ ከቦታ ቦታ በድብቅ እየተንቀሳቀሱ" ጥቃት የሚፈፅሙ በመሆናቸው፣ በከባድ ተሽከርካሪዎቹ ላይ የደረሰውን ጥቃት "እገሌ ፈፀመው" ለማለት እንደሚያስቸግር አስረድተዋል።

በጥቃቱ የተገደለ ወይም አካላዊ ጉዳት የደረሰበት ሰው ስለመኖር አለመኖሩ አስተያየት ሰጪዎቹ መረጃ የላቸውም። ታጋቾቹ የት እንዳሉም እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ፣ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች "የተለመደ ሆኗል" ያሉት በአሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የተፈፀመበትን ቦታ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተቆጣጥረው ክትትል እያደረጉ እንደሆነ ምንጮቻችን ቢያረጋግጡም መንግሥት ስለጉዳዩ አስካሁን ምንም አላለም።

ስለጥቃቱ አስተያየት የጠየቅናቸው የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይልን በመሆኑ በተናጥል ምንም ማለት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ከምዕራብ ወለጋ ዞን እና ጥቃቱ ከተፈፀመበት የዞኑ ወረዳ የመንግሥት አመራሮች እና የፖሊስ አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ለስልክ ጥሪ ምላሽ ባለመስጠታቸው አልተሳካም።

በአካባቢው ይንቀሳቀሳል የሚባለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም በዚህ ጥቃት ተሳትፎ ይኖረው እንደሆነ ላቀረብንለት ጥያቄ አስካሁን ምላሽ አልሰጠም።