ስደተኞች ከሞሮኮ ወደ ስፔን መሻገራቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ስደተኞች ከሞሮኮ ወደ ስፔን መሻገራቸው ያስነሳውን ውዝግብ ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ለቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ።
ስብሰባው በስፔን፣ ሲዩታ የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ የኅብረቱ አባል አገራት የሚወያዩበት እንደሆነ ተገልጿል።
የስደተኞቹን ጉዳይ በተመለከተ በስፔን እና በተቀሩት የአውሮፓ አገራት መካከል ጠንካራ የቃላት ልውውጦች ተሰምተዋል።
22 የኅብረቱ አገራት በጋራ ባወጡት ደብዳቤ የአውሮፓን ውጭያዊ ድንበር ለማስጠበቅ በትብብር እርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ወደ 60,000 የሚጠጉ ስደተኞች ከሞሮኮ ወደ ስፔን መግባታቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ድንበሮች ጥበቃ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።
ጣሊያን ከስፔን ጋር የነበራትን ነጻ ዝውውር የሚፈቅደውን ሸንገን ማቋረጧን ተከትሎ፤ ስፔን "ራስ ወዳድ፣ ከፋፋይ እና ሕገ ወጥ" ስትል የአውሮፓ አገራትን ምላሽ ኮንናለች።
ፊንላንድ እና ዴንማርክ በበኩላቸው የጣሊያንን እርምጃ ደግፈዋል።
የስፔን ባለሥልጣናት እንደገለጹት ከቀናት በፊት ወደ ሲዮታ የገቡት ስደተኞች ሁሉም በሚባል ደረጃ ተመልሰዋል።
ድንበር ለማቋረጥ በሚደረገው ጥረት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨምሮ 67 ደርሷል።
የኅብረቱ አባል አገራት በጻፉት ደብዳቤ "ወደ አውሮፓ ኅብረት በሕገ ወጥ መንገድ መግባት ይቻላል" የሚል ግንዛቤ እንዲፈጠር ያደረገ ክስተት እንደነበር በመግለጽ ኮንነዋል።
ድንበር ለመሻገር "ተጨማሪ ሙከራዎች" እንዲደረጉ እንደሚያበረታታ እና ይህም የኅብረቱ የጋራ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ያለውን እምነት "የሚሸረሽር" እንደሆነም አስታውቀዋል።
ኔዘርላንድስ፣ ፊንላንድ እና ቤልጂየም በደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን ካኖሩ አገራት መካከል ናቸው።
ደብዳቤው የተጻፈው ለአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ፣ ለኅብረቱ ኮሚሽነር ኧርሰላ ቮን ደር ሊይን እና ለአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አሁናዊ ፕሬዝዳንት ለሆኑት የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማይክል ማርቲን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ለኅብረቱ ኮሚሽነር ኧርሰላ ቮን ደር ሊይን በተናጠል በጻፉት ደብዳቤ፤ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት መንግሥታት ጉዳይ "በጣም እንደሚያሳስባቸው" ገልጸዋል።
የስፔን መንግሥት ድንበሩን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረ እና ከ48 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ "ወደ አውሮፓ የሚደረግ ያልተፈቀደ እንቅስቃሴን እንደገደበ" ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት "ድጋፍ እና ትብብር" ቢያሳዩም አንዳንድ አገራት ግን ስፔን ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደመረጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ለዚህም መነሻው "ጭፍን ጥላቻ፣ ሐሰተኛ ዜና፣ ድንቁርና እና የፖለቲካ ፍላጎት" መሆኑን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ሲዩታ የሸንገን ክልል ውስጥ እንደማትገኝ ጠቁመዋል።
የስፔን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ባስተላለፈው ውሳኔ መንግሥት ባሕር አቋርጠው ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን የመመለስ አቅሙ እንዲገደብ ተደርጓል።
ስደተኞች ይህንን ውሳኔ "በዝብዘዋል" ሲሉ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ወቅሰዋል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትር ፈርናንዶ ግራንድ ማርላስካ እንዳሉት ነገሮች የረገቡ ሲሆን፤ በሕገ ወጥ መንገድ ስደተኞች ባሕር እንዳይሻገሩ መከላከያ ተዘርግቷል።
"ስደተኞቹ ሁሉም በሚቻል መጠን ሲዩታን ለቅቀው ወጥተዋል" ብለዋል።
በአውሮፓ አገራት ድንበር ላይ የሚደረግ ፍተሻን የሚያስቀረው ሸንገንን በተመለከተ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው።
ሸንገን በ29 የአውሮፓ አገራት 450 ሚሊዮን ሰዎችን የሚሸፍን አካባቢ ነው።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ከስፔን ጋር የነበራቸውን የሸንገን ስምምነት ለአንድ ወር ሰርዘዋል።
ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ እና ፖርቹጋል የድንበር ላይ ፍተሻ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን በበኩላቸው የአውሮፓ ኅብረት "የሸንገን ትብብርን ለማቋረጥ ሁሉንም አማራጮች ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ" አሳስበዋል።
የኅብረቱ ኮሚሽነር ኧርሰላ ቮን ደር ሊይን "በሲዩታ የተፈጠረው ተቀባይነት የለውም። ማንም ሰው ሕጋችንን ሳይከተል ወደ ኅብረታችን እንዲገባ መፍቀድ የለብንም" ብለዋል።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ በበኩላቸው ሞሮኮ "በአፋጣኝ ሕገ ወጥ ስደተኞችን እንድትረከብ" ጠይቀዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሀም ከስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተነጋግረው "የሚችሉትን ድጋፍ ለመስጠት" መስማማታቸውን ገልጸዋል።
አምና በሞሮኮ በተነሳው የወጣቶች ንቅናቄ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እና የሕዝብ አገልግሎት እንዲዘረጋ ጥያቄዎች ተስተጋብተዋል።
ሲዩታ አፍሪካ ከአውሮፓ ጋር የምትገናኝበት ብቸኛ የየብስ መንገድ ሲሆን፤ ስደተኞች በርካታ ኪሎሜትሮች በመዋኘት ድንበር ያቋርጣሉ።
በአውሮፓውያኑ 2021 ወደ 8,000 ሰዎች ወደ ሲዩታ ገብተዋል። በዚህ ምክንያት በሞሮኮ እና ስፔን መካከል የዲፕሎማሲ ውጥረት ተከስቷል።
ስፔን ስደተኞች በተመለከተ አወንታዊ አካሄድን ትከተላለች።
በቅርቡ የአገሪቱ መንግሥት ለ500,000 ሰነድ አልባ ስደተኞች ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት ወስኗል።















