ቀጥታ, ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ወጥታ ወደ ጂቡቲ ጉዞ ጀመረች

በሆርሙዝ ወሽመጥ መተላለፊያ አጥታ የነበረችው የኢትዮጵያ መርከብ ወደ ጂቡቲ ጉዞ መጀመሯ ተገለጸ። የኢትዮጵያዋ መርከብ ጊቤ ጉዞ መጀመሯን የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ እና ኢራን ቴክኒካዊ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት ድጋሚ እንደሚጀመር ተገለጸ

    የአሜሪካ እና ኢራን ቴክኒካዊ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት በድጋሚ እንደሚጀመር የአሸማጋይዋ ፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

    “ምናልባት ማክሰኞ” ዕለት ይጀመራል የተባለው ቀጣዩ ቴክኒካዊ ንግግር የሚካሄድበት ቦታ ግን ይፋ አልተደረገም።

    ስዊትዘርላድ ውስጥ የተካሄደው የሁለቱ አገራት የመጀመሪያው ዙር ንግግር እሁድ ዕለት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስዊዘርላንድን ለቅቀው ሄደዋል።

    የቴክኒካል ልዑካኖቻቸው ግን ሰኞ ዕለትም ንግግር ማድረግ ቀጥለው ነበር።

    ማክሰኞ ዕለት የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ካዜም ኸሪባባዲ የመጀመሪያው ዙር የቴክኒካል ንግግር መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

    ተደራዳሪዎቹ “የማዕቀብ መነሳት”፣ “የኒውክሌር ጉዳይ”፣ “የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታ እና ልማት” እንዲሁም “የቁጥጥር እና ትግበራ” ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ አራት ቡድኖችን ማቋቋማቸውንም ገልጸዋል።

    እነዚህ የስራ ቡድኖች አሜሪካ እና ኢራን የፈረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ቴክኒካዊ ዝርዝር ጉዳዮች አፈጻጸምን የመከታተል ኃላፊነት ይኖራቸዋል።

  2. ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢቦላ የተያዘ ሰው መገኘቱን አረጋገጠች

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የሰብአዊ ረድኤት ተልዕኮ ላይ ሲሳተፍ ቆይቶ የተመለሰ አንድ ዶክተር ላይ የኢቦላ ቫይረስ መገኘቱን የፈረንሳይ መንግሥት አስታወቀ። የሕክምና ባለሙያው ፈረንሳይ ውስጥ በኢቦላ መያዙ የተረጋገጠ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ዶክተሩ "ወዲያውኑ ወደ ልዩ የህክምና ተቋም መግባቱን" እና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

    ዴሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን ይፋ ያደረገችው ባለፈው ወር ቢሆንም፤ ባለሙያዎች በሽታው መከሰቱ ከመታወጁ ሳምንታት አስቀድሞ ሲሰራጭ እንደነበረ ያምናሉ።

    በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ በተከሰተው በሽታ ምክንያት ከ260 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ተረጋግጧል። አንድ ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

    ባለፈው ወር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በበሽታው የተያዘ ሰው ጀርመን ውስጥ ሕክምና ሲያገኝ የነበረ ቢሆንም በአውሮፓው የኢቦላ መገኘቱ ሲረጋገጠ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

    የኮንጎ ጎረቤት የሆነችው ዩጋንዳም በኢቦላ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አረጋግጣለች። የዓለም ጤና ድርጅት ዩጋንዳ ውስጥ 20 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን እና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እንደተረጋገጠ ገልጿል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው በሕዝቡ ውስጥ በሽታው የመሠራጨቱ የስጋት መጠን “እጅግ ዝቅተኛ” መሆን በአጽንኦት አንስቷል።

    ባለሥልጣናት ከዶክተሩ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየት እየሰሩ መሆኑንም አክሏል።

    የጤና ባለሙያዎች ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች ለሚተላለፈው ኢቦላ የበለጠ ተጋላጭነት አላቸው።

    አሁን የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ቡንዲቡግዮ በተባለው የቫይረሱ ዝርያ የመጣ ሲሆን ይህ ዝርያ እስካሁን ክትባት አልተገኘለትም።

  3. ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ወጥታ ወደ ጂቡቲ ጉዞ ጀመረች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፊያ አጥታ የነበረችው ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ጉዞ መጀመሯ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ።

    ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ሲጀመር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለወራት ዘግታው ቆይታለች።

    ወሽመጡ በቀን አስከ 140 ግዙፍ የጭነት መርከቦች የሚተላለፉበት ወሳኝ መስመር ነበር።

    መተላለፊያው በመዘጋቱ የኢትዮጵያን ጨምሮ 1,150 የጭነት መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ የመርከቦቹ ሠራtኞች ለወራት ቆመው ለመጠበቅ ተገደዋል።

    ሁሉም መርከቦቹ በአጠቃላይ 125 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጭነት ይዘው ነበር የቆሙት።

    በጦርነቱ ወቅት ለማለፍ የሞከሩ 32 የጭነት መርከቦች በሚሳዔል ወይም በድሮን ተመትተዋል። በዚህም ከመርከቦቹ ሠራተኞች 10 ሰዎች መሞታቸው እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተረጋግጧል።

    ኢራን እና አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ሆርሙዝ እንደገና ክፍት ተደርጓል። ለወራት መተላለፊያ አጥተው ከነጭነታቸው የቆሙት መርከቦች አሁን ወደየመዳረሻቸው ጉዞ ጀምረዋል።

    ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያዋ መርከብ 'ኤምቪ ጊቤ' ጉዞ መጀመሯን የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታውቋል።

    የኢትዮጵያ መርከብ በኦማን ገልፍ በኩል ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ መሆኗ ተገልጿል። እሁድ ሰኔ 21 ምሽት 2:00 ሰዓት ጂቡቲ ወደብ እንደምትደርስም እየተጠበቀ ነው።

  4. በኬንያ ታዳጊዎች ከሞቱበት የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ሊከሰሱ ነው

    ባለፈው ወር በኬንያ ትምህርት ቤት ከተነሳው እና ታዳጊዎች ከሞቱበት የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ መሆኑን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

    ከ15 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው አስራ ስድስት ተማሪዎች በእሳት አደጋው ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል። ሌሎች ብዙ ተማሪዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በርካታ ተማሪዎች በግድያ ወንጀል ይከሰሳሉ።

    ከመዲናዋ ናይሮቢ በ120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጊልጊል ከተማ በሚገኝ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች መኝታ ክፍል እሳት መነሳቱ ሕዝቡን አስቆጥቷል።

    ስምንት ተማሪዎች በእሳት አደጋው እጃቸው አለበት በሚል በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ተማሪዎቹ ፍራሽ በማቃጠል እሳቱ እንዲስፋፋ ማድረጋቸው ተገልጿል።

    እሳቱ 135 ተደራራቢ አልጋዎች ባሉበት መኝታ ክፍል የመጀመሪያ ሕንጻ ላይ ነበር የተነሳው። የድንገተኛ ጊዜ በር ለመክፈት ያልቻሉት በሕንጻው የሚኖሩት 202 ተማሪዎች በአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚገኝ በር ለመውጣት ተገድደዋል።

    ፖሊስ እንዳለው በተማሪዎች እና በሠራተኞች ላይ ምርመራ ከተደረገ፣ የደኅንነት ካሜራ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከተፈተሸ እና የፎረንሲክ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ስምንት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ተማሪዎቹ በግድያ ወንጀል ተከስሰው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

  5. የሊባኖስን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ እንዳለው የቴህራን ባለሥልጣን ተናገሩ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ “በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ አለው” ሲሉ ተናገሩ።

    በአዘርባጃን፣ ባኩ እየተካሄደ ባለው የእስላዊ ትብብር ተቋማት የምክር ቤት ኅብረት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር “ለእኛ የሊባኖስ የተኩስ አቁም የኢራን የተኩስ አቁም ያህል ዋጋ አለው። በተጨማሪም በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ አለው” ብለዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ውጊያ ማቆምን ያካትታል።

    ዋነኛው ተደራዳሪ የሆኑት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ “የኢስላማባድ ስምምነት የአሜሪካን ሽንፈት አውጇል” ብለዋል።

    የጦርነቱ ዓላማ “በቀጣናው ስትራቴጂያዊ የአሰላለፍ ለውጥ ለማምጣት እና ይህንንም በነጻ አገር ላይ መጫን” እንደሆነም ተናግረዋል።

    ከቀጣናው “የውጭ ኃይሎችን ማስወጣት ስትራቴጂያዊ ድል ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ኢራን እርስ በርስ በመከባበር እና ጣልቃ ባለመግባት መርህ ከሙስሊም አገራት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

  6. አሜሪካ እና እስራኤል ደቡብ ሊባኖስን ለአገሪቱ ጦር የማስረከብ ዕቅድ ማውጣታቸው ተዘገበ

    አሜሪካ ድጋፏን በሰጠችው ዕቅድ መሠረት እስራኤል እና ሊባኖስ፤ የደቡብ ሊባኖስ አስተዳደርን ለአገሪቱ ጦር ለማስረከብ ማሰባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሮይተርስ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣናት የሆኑ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በዚህ ዕቅድ ውስጥ የሚካተቱ የሊባኖስ ኃይሎች ከአሜሪካ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

    ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ለማረጋገጥም የደኅንነት ማጣራት ይደረጋል።

    የዜና ወኪሉ የጠቀሳቸው ምንጮች እንዳሉት፤ በደቡብ ሊባኖስ ያሉ አካባቢዎች ለአገሪቱ ጦር ተላልፈው እስከሚሰጡ ድረስ እስራኤል ቀጣናውን እየተቆጣጠረች ትቆያለች።

    አሜሪካ እና እስራኤል በይፋ አስተያየታቸውን አልሰጡም። እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ ረቡዕ በዋሽንግተን ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።

  7. ተመድ ከሆርሙዝ ወሽመጥ 11 ሺህ መርከበኞችን እንደሚያስወጣ አስታወቀ

    የተባበሩት መንግሥታት ማሪታይም ባለሥልጣን በኢራን ጦርነት ሳቢያ በሆርሙዝ ወሽመጥ የቀሩ 11 ሺህ መርከበኞችን እንደሚያስወጣ አስታወቀ።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ሳቢያ መርከበኞቹ ከባሕረ ሰላጤው አካባቢ ለመውጣት ሳይችሉ ቆይተዋል።

    የተመድ ማሪታይም ባለሥልጣን (አይኤምኦ) ዋና ጸሐፊ አርሴኒዮ ዶሚኒገዝ እንደተናገሩት ከኢራን፣ አሜሪካ፣ ኦማን እና ሌሎችም የባሕረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም የማሪታይም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “መጠነ ሰፊ ኦፕሬሽን” ይካሄዳል።

    “ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስወጣት የምንችልበት መንገድ ዘርግተናል” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን የመግባቢያ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ቢያኖሩም ዝርዝሩን በተመለከተ የሚቃረኑ መረጃዎች እያወጡ ይገኛሉ።

    በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በኢራን ፍተሻ ማድረግ እንደሚችል ዋሽንግተን ብትገልጽም፤ ቴህራን አስተባብላለች።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ምንም ዓይነት ክፍያ መጠየቅ እንደማትችል ገልጸዋል።

    ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ክፍያ መጠየቅ የኢራን እና አሜሪካን ስምምነት የሚጥስ እና ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው።

    ኢራን በበኩሏ ከኦማን ጋራ ባወጣችው መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኝበትወሳኝ የባሕር መተላለፊያላይ ሉዓላዊ መብት ያላቸው ሁለቱ አገራት መሆናቸውን አስታውቃለች።

    አገራቱ ጥምር ኮሚቴ አቋቁመው የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር እና መርከቦች ለመተላለፍ የሚፈጽሙትን ክፍያ ጉዳይ በጋራ እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

  8. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ማስከፈል አትችልም ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች

    ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ምንም ዓይነት ክፍያ መጠየቅ እንደማትችል እና ይህንን የምታደርግ ከሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    ማርኮ ሩቢዮ ይህንን ያሉት ኢራን እና ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ስለሚደረጉ የባሕር ላይ ጉዞዎች እና ከሚሰጠው አገለግሎት ጋር ያሉ ወጪዎችን በተመለከተ ውይይት ማድረቸጋውን ተከትሎ ነው።

    ሁለቱ አገራት ኦማን ውስጥ ካደረጉት ውይይት በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮቻቸው አማካኝነት የጋራ ግብረ ኃይል በመመሥረት ከተጎራባች አገራት እና ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ምክክር እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።

    ኢራን እና ኦማን ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት ትግበራ ላይ ለመመካከር ባደረጉት ውይይት አገራቱ በወሳኙ የባሕር መተለላፊያ ላይ ያላቸው ሉዓላዊነት ተከብሮ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለመግለጽ የታለመ ነው።

    አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱበት ከየካቲት ወር መጨረሻ አንስቶ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ዝግ ተደርጎ የቆየ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ በኢራን ላይ የባሕር ላይ እገዳ ጥላ ቆይታለች።

  9. ኢራን እና ኦማን የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር እና ክፍያን በጋራ እንደሚወስኑ አስታወቁ

    ኢራን እና ኦማን በጋራ ባወጡት መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኝበት ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ላይ ሉዓላዊ መብት እንዳላቸው ተናገሩ።

    በመግለጫው የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ ተጠብቆ ዓለም አቀፍ የመርከቦች መተለላፊያ ሆኖ እንዲቀጥል በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

    በቀጣይ የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደርን እና መርከቦች ለመተላለፊ የሚፈጽሙትን ክፍያ ጉዳይ በጥምር ኮሚቴ አማካኝነት እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት ከተወያዩ በኋላ ነው መግለጫውን ያወጡት።

    በስዊትዘርላንድ የነበሩት የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ የእስላማዊ ሪፐብሊክ የፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ወደ ኦማን አቅንተው ከንጉሥ ሐቲሀም ቢን ታሪቂ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር ቡሳዲ ጋር ተወያይተዋል።

  10. እስራኤል የኢንተርኔት መገናኛዎችን በድብቅ ወደ ኢራን ማስገባቷን የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ተናገሩ

    ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎት በሚያቋርጥበት ጊዜ የሚሠሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢንተርኔት መገናኛ መሳሪያዎችን ከዓመታት በፊት እስራኤል ወደ ኢራን አስርጋ ለማስገባት መሥራቷን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት በሥልጣን ላይ ሳሉ ኢራናውያን ተቃዋሚዎች ኢንተርኔት በሚቋረጥ ጊዜ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የስታርሊንክ የኢንተርኔት መቀበያዎችን በድብቅ ወደ ኢራን ለማስገባት ያለመ ዕቅድ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

    ቤኔት ኢየሩሳሌም ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ዓላማቸው የተቃዋሚዎችን ግንኙነት እና እንቅስቃሴ ማቀናጀት በማስቻል የኢራንን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወገድ ማድረግ ነበር።

    "በሚያሳዝን ሁኔታ አሁን ያለው [የኔታኒያሁ] መንግሥት እየተካሄደ የነበረውን ፕሮግራም በማስቆሙ ኢራን ውስጥ ተቃውሞው ሲቀሰቀስ አስፈላጊው የግንኙነት መሳሪያ በቦታው አልነበረም” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ለሰነዘሩት አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

    እንዲሁም የስታርሊንክ ኢንተርኔት መገናኛ አቅራቢ ድርጅት የሆነው ስፔስኤክስም በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

    ናፍታሊ ቤኔት ከእስራኤል ተቃዋሚዎች መካከል ተጠቃሹ ሲሆኑ በመጪው ምርጫ ዋነኛው ዕጩ ሊሆኑ ይችላሉ እየተባለ ነው። ወደ ሥልጣን የሚመለሱ ከሆነ የኢራንን መንግሥት ለማዳከም እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

    ለዚህም በኢራን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ከቅጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ባሻገር “የኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ አሻጥሮችንም” እንደሚያካትቱ ገልጸዋል።

    ናፍታሊ ቤኔት ከአራት ዓመት በፊት ለአንድ ዓመት ያህል ቤንያሚን ኔታኒያሁን ለአጭር ጊዜ ከሥልጣን ያስወገደውን የቀኝ እና የግራ ክንፍ እንዲሁም የመሃል ፓርቲዎች ጥምር መንግሥትን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል።

    ቤኔት ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የኔታኒያሁ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል።

  11. ኢራን የኒውክሌር ቁጥጥር እንዲደረግ ባትስማማ ኖሮ ድርድር ሳይካሄድ ይቀር እንደነበር ትራምፕ ገለጹ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ሙሉ በሙሉ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የኒውክሌር ቁጥጥር እንዲደረግ ፈቅዳለች” አሉ።

    ኢራን ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን ብታስተባብልም፤ ትራምፕ “ለከፍተኛ ደረጃ የኒውክሌር ቁጥጥር ተስማምታለች” ብለዋል።

    ይህ የኢራን ስምምነት “ለረዥም ጊዜ እና እስከ ወዲያኛው” እንደሚዘልቅ ጠቅሰው “የኒውክሌር ታማኝነትን የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ኢራን ለዚህ ባትስማማ ኖሮ ተጨማሪ ድርድሮች አይኖሩም ነበር” በማለት አክለዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢስማኤል ባጋይ ከሰዓታት በፊት ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ እና የደረሰውን ጉዳት እንዲመለከቱ አለመፈቀዱን ገልጸዋል።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን ለኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ መስጠቷን ተናግረዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “በዚህ እና በሌሎችም ኢራን ባቀረበቻቸው ስምምነቶች መነሻነት ነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ እንዲቀጥል እንዲሁም በባሕር መተላለፊያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዳይጣል የተስማማሁት” ብለዋል።

  12. የኬንያው የጤና ሚኒስትር የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቆም ወሰኑ

    የኬንያ የጤና ሚኒስትር ኤደን ዱአሌ በአሜሪካ የሚደገፈው አወዛጋቢው የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቋረጥ ውሳኔ አሳለፉ።

    ሚኒስትሩ ውሳኔውን ከማሳወቃቸው ከአንድ ቀን በፊት ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ መባላቸው አይዘነጋም።

    ዛሬ ማክሰኞ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀው በኛኙኪ ግዛት በሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር የሚገነባው የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል “በአፋጣኝ እና ሙሉ በሙሉ እንዲቆም” ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።

    ባለፈው ወር የመብት ተሟጋች ቡድኖች ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ የኬንያ ፍርድ ቤት 50 አልጋዎች ያሉት የለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቆም ውሳኔ አሳልፏል።

    ሆኖም ግን ሰኞ ዕለት የዋለው ችሎት የጤና ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ችላ ብለው ግንባታው እንዲቀጥል በመወሰናቸው ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

    ማዕከሉ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ የተጠረጠሩ አሜሪካዊያን ለይቶ ማቆያ እንዲሆን ታስቦ ነበር።

    የጤና ሚኒስትሩ ኤደን ዱአሌ “ድርጊቴ፣ ችላ ባይነቴ፣ አለመረዳቴ ወይም የተዛባ ግንዛቤዬ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከብር በማድረጉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ፓትሪሽያ ናዩንዲ የሚኒስትሩን ይቅርታ ተቀብለው “በጥብቅ ማስጠንቀቂያ” አሰናብተዋቸዋል።

    የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ በኬንያውያን ዘንድ ቁጣ እና ተቃውሞ አስነስቷል። ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሲሞክር ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

  13. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ለኢራን ጦርነት ላወጣው 80 ቢሊዮን ዶላር ጥያቄ አቀረበ

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር በአብዛኛው ለኢራን ጦርነት ያወጣውን ወጪ ለመሸፈን ወደ 80 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት አስታወቀ።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የበጀት ጥያቄው ገና በይፋ አለመቅረቡን ቢገልጽም፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት ባለፉት ቀናት ወደ አሜሪካ ምክር ቤት በመሄድ ከእንደራሴዎች ጋር እየተገናኙ መሆናቸው ተዘግቧል።

    አሶሺየትድ ፕሬስ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ነገር ግን በይፋ ለመግለጽ ሥልጣን የሌላቸውን ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ለኢራን ጦርነት የወጣውን ገንዘብ የተመለከተ ጥያቄ ባለፈው ዓመት ለምክር ቤት አባላት ቀርቧል።

    ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ስቴፈን ፋይንበርግ በበኩላቸው ከበርካታ የምክር ቤት አባላት ጋር በቀረበው የገንዘብ ጥያቄ ላይ ከመነጋገራቸው በተጨማሪ ዝርዝሩ ለምክር ቤቱ የአስተዳደር እና የበጀት ጽህፈት ቤት መቅረቡ ተገልጿል።

    ፔንታገን በመባል የሚታወቀው የመከላከያ መሥሪያ ቤት ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ተጠይቆ ምላሽ አልሰጠም።

    ይህ የበጀት ጥያቄ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ከተቃወሙት የምክር ቤት አባላት በአሜሪካውያን ላይ ያጋጠመውን የኑሮ ውድነት እንደምክንያት በማቅረብ ቀላል የማይባል ተቃውሞ እንደሚገጥመው ይጠበቃል።

    ግንቦት ወር ላይ በምክር ቤቱ በተካሄደው የጥያቄ እና መልስ መድረክ ላይ “በርካታ ሕዝብ ለተቃወመው ጦርነት አሜሪካውያን ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ እያወጣችሁ ነው” በማለት ዴሞክራቷ የምክር ቤት አባል ፓቲ መሪ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴትን መናጋራቸው ይታወሳል።

  14. የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የሰው ሕይወት ባጠፋው ቴስላ መኪና ላይ ምርመራ ጀመሩ

    የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት ባለሥልጣናት አንድ ቴስላ መኪና በድንገት ከመንገድ ወጥቶ ከመኖሪያ ቤት ጋር በመጋጨት የአንድ ሰው ሕይወት ካለፈ በኋላ ምርመራ ማድረግ መጀመራቸው ተገለጸ።

    ባለፈው ሳምንት አርብ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት ሁለት ሰዓት ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ከመንገድ ወጥቶ አደጋ ስላደረሰው ቴስላ መኪና የአሜሪካ ብሔራዊ የመንገዶች ትራፊክ ደኅንነት አስተዳደር ሰኞ ዕለት ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።

    በቴስላ በተገጨመው ቤት ውስጥ የነበረችው ሴት ከባድ ጉዳት ከደረሰባት በኋላ በአደጋው ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።

    ፖሊስ ጨምሮም የመኪናው ሹፌር በአደጋው ወቅት በአደገኛ ዕጽም ሆነ በአልኮል ተጽእኖ ስር አልነበረም። አሽከርካሪው ለመርማሪዎች እንደተናገረው አደጋው የደረሰው መኪናው አውቶማቲክ ሆኖ በራሱ እየተሽከረከረ በነበረበት ጊዜ ነው።

    የአሜሪካ መንገዶች ደኅንነት አስተዳደር ቃል አቀባይ እንዳሳወቀው "መሥሪያ ቤቱ በአደጋው ላይ ልዩ ምርመራ ማካሄድ ጀምሯል።”

    የዓለማችን የመጀመሪያው አሜሪካዊው ትሪሊየነር ንብረት የሆነው የዘመናዊው መኪና አምራች ቴስላ ተወካይ መንግሥት በተሽከርካሪው ላይ እያካሄደ ስላለው ምርመራ አስተያየት ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።

    የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሞዴል 3 የተባለው ቴስላ መኪና አሽከርካሪ “መኪናው ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኖ ከመንገድ በመውጣት ከመኖሪያ ቤት ጋር በመጋጨቱ” የሰው ሕይወት ጠፍቷል።

  15. የምያንማር ጦር በስድስት ወር ውስጥ ከ700 በላይ ንጹኃንን መግደሉን የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ

    የምያንማር ጦር ባለፈው ዓመት በምርጫ ወቅት በስድስት ወር ውስጥ ለተመዘገቡት ከ700 በላይ የንጹኃን ሰዎች ሞት ተጠያቂ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ።

    ካለፈው ነሐሴ እስከ ጥር ድረስ ያለውን ጊዜ የሸፈነ አዲስ ሪፖርት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው 224 ሴቶች እና 153 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 702 ሰዎች እንደተገደሉ ከታማኝ ምንጮች ተረጋግጧል።

    ጥናቱ የሸፈነው ከአምስት ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ያወጀው ሠራዊት ምርጫ እንደሚካሄድ ያፋ ካደረገ በኋላ ያሉትን ስድስት ወራት ነው። ምርጫው ተቃዋሚዎች በመገለላቸው ምክንያት የተጭበረበረ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል።

    “የዓለም አቀፍ እገዛ መቀነስ የሚሊዮን ሰዎችን ስቃይ እያባባሰ ነው” ሲል ሪፖርቱ አስጠንቅቋል።

    የምያንማር ጦር በ2021 መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱን ካወጀ በኋላ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፤ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። ሰፊው የአገሪቱ ክፍልም በታጣቂዎች እጅ ወድቋል።

    የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው የአየር ጥቃት “ብቸኛው ግዙፍ የውድመት እና ስቃይ ምክንያት” ሆኖ ቀጥሏል።

    ጥቅምት ወር ላይ በተፈጸመ ጥቃት አራት ሕጻናትን ጨምሮ 23 ሰዎች ተገድለዋል። ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ተሰብስበው 60 ሰዎች ደግሞ ተተኳሽ ሲወድቅ በፍንጥርጣሪ ተጎድተዋል።

    ታኅሣሥ ላይ ደግሞ ሠራዊቱ በሻይ ቤት ላይ በፈጸመው ጥቃት ኳስ ለመመልከት ተሰብስበው የነበሩ ቢያንስ 19 ሰዎች እንደተገደሉ እና 20 ሰዎች እንደቆሰሉ ሪፖርቱ ገልጿል።

  16. ኢራን የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን አስተባበለች

    ጦርነቱን ለመቋጨት ከአሜሪካ ጋር የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ንግግር መጠናቀቁን ተከትሎ ኢራን ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን የቴህራን መንግሥት አስተባበለ።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በስዊትዘርላንድ ከተካሄደው ድርድር ባደረጉት ንግግር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶች “ዛሬ ጭምር” ሊጀመሩ ይችላሉ ብለው ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ለአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ማብራሪያ፤ የኒውክሌር ቁጥጥርን በተመለተከተ የተገባ “አዲስ ቃል የለም” ብለዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ሰኞ ጠዋት ላይ በስዊትዘርላንድ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ ኢራን የሚመለሱት መቼ እንደሆነ ተጠይቀዋል።

    ለዚህም ምላሽ ሲሰጡ ሂደቱ “ቢያንስ በዚህ ሳምንት” እንደሚጀመር፤ ከተቆጣጣሪዎቹ ጋር የሚደረገው ንግግር ግን “ዛሬ ጭምር ሊካሄድ እንደሚችል” ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ኢራን "በዋና ዋና የጦር መሣሪያዎች ላይ ፍተሻ እንዲካሄድ ትስማማለች” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    ‘ኢርና’ ለተሰኘው ለኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ቃለ መጠይቅ የሰጡት የቴህራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባቃኢ ግን አገራቸው የኔውክሌር ተቆጣጣሪዎችን በተመለከተ "ምንም አይነት አዲስ ቃል" እንዳልገባች ተናግረዋል።

    ከተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪዎች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት የሚከናወነው “በፓርላማው እና በጠቅላይ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በተቀመጡት ነባር አሰራሮች" መሠረት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።

    ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።

    ኢራን የኤጀንሲው ወደ የኒውክሌር ስፍራዎች እንዳይጓዝ የከለከለችው ባለፈው ዓመት በተካሄደው የ12 በቀናት ጦርነት ወቅት እስራኤል እና አሜሪካ የኒውክሌር ጣቢያዎችን ከደበደቡ በኋላ ነው።

    ይህንን ውሳኔ ተከትሎም የመንግሥታቱ ድርጅት ተቆጣጣሪ ተቋም የቀሩትን ባለሙያዎቹን ከኢራን አስወጥቷል።

  17. አሜሪካ በኢራን ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አላላች

    ዋሽንግተን ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራን ነዳጅ በአሜሪካ ዶላር እንዲሸጥ በመፍቀድ ቴህራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በጊዜያዊነት አነሳች።

    ለ60 ቀናት የሚቆየውን የማዕቀብ ማላላት እርምጃ ሰኞ ምሽት ይፋ ያደረገው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ነው። ይህ እርምጃ የኢራንን ኢኮኖሚ አንቆ የያዘው እና ለረጅም ጊዜ የቆየው የአሜሪካ ማዕቀብ ዋነኛ ምሰሶዎች እንዲወገዱ ያደርጋል።

    በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ፈቃድ መሠረት ኢራን እስከ ነሐሴ ወር ድረስ ድፍድፍ ነዳጅ እንዲሁም የፔትሮኬሚካል ምርቶችን ማምረት፣ መሸጥ እና መላክ ትችላለች። ይህ የማዕቀብ እፎይታ የኢራን ነዳጅ በቀጥታ ወደ አሜሪካ እንዲገባም ያስችላል።

    በተጨማሪም የኢራን የባንክ ዝውውር፣ ኢንሹራስ እና ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መነሳቱ ቴህራን ከዚህ ቀደም ድፍድፍ ነዳጇን ለመሸጥ ስትከተል የነበረውን ውስብስብ አሰራር ያስቀራል።

    የግምጃ ቤት ኃላፊው ስኮት ቤንሰንት እንደተናገሩት ለ60 ቀናት የሚቆይ የማዕቀብ እፎይታ የተሰጣት ኢራን በምላሹ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመክፈት ቃል ገብታለች።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎችም ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ትፈቅዳለች ብለዋል።

    ኢራን ግን ይህ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው መባሉን አስተባብላለች።

    አሜሪካ የማዕቀብ ማላላት እርምጃውን የወሰደችው ስዊዘርላንድ ውስጥ ሁለቱን አገራት ሲያደራድሩ የነበሩት አሸማጋዮች ጥሩ መሻሻል መታየቱን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ኳታር እና ፓኪስታን ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ አሜሪካ እና ኢራን “በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ” ላይ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስም የመጀመሪያው ዙር ንግግር “በጣም ጥሩ መሠረት” መጣሉን ተናግረዋል።

  18. በኳታር የጋዝ ማቀነባበሪያ ላይ ባጋጠመ ፍንዳታ 13 ሰዎች ሞቱ

    በግዙፉ የኳታር የጋዝ ማምረቻ ተቋም ላይ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 13 ሰዎች እንደሞቱ እና 66 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።

    ራስ ላፋን በተሰኘው የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኘው እና ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ የተፈጥሮ ጋዝ ዋነኛ ማቀነባበሪያው የሆነው ስፍራ እሁድ ምሽት “የቴክኒካል አደጋ” እንዳጋጠመው የኳታር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በዚህ አደጋ ምክንያት የከተማው ሰማይ ብርቱካናማ ቀለም ይዞ ታይቷል። የእሁድ ዕለቱ ፍንዳታ ከራስ ላፋን 70 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው ማዕከላዊ ዶሃ ጭምር ተሰምቷል።

    በዚህ ጥቃት የሞቱት ሰዎች የሕንድ እና የፓኪስታን ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ ተገልጿል።

    ፍንዳታው በአገሪቱ ኤክስፖርት ምርት ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው የተናገሩት የኳታር የኤነርጂ ሚኒስትር ሳዐድ ሸሪዳ አል ካቢ፤ “ያጋጠመው አደጋ ነው፤ በተፈጥሮውም ትንኮል ወይም በጠበኛ ድርጊት [የተከሰተ] አይደለም” ብለዋል።

    ጥቃቱ የደረሰበት ስፍራ የሚገኝበት ራስ ላፋን በዓለም ትልቁ ሰው ሰራሽ ወደብ ሲሆን በውስጡም የዓለም ትልቁን ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ማቅረቢያ ተቋምን ይዟል።

    የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ተከትሎ ስፍራው በኢራን ጥቃቶች ተፈጽመውበት ነበር። የአሁኑን ፍንዳታ ምክንያት ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን የኤነርጂ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

  19. የአሜሪካ እና ኢራን ንግግር ውጤት እያስገኘ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ገለጹ

    አሜሪካ እና ኢራን ስዊትዘርላንድ ውስጥ እየካሄዱት ባለው ንግግር “መልካም ውጤቶች መገኘታቸውን” እና የተሳካ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ “ጥሩ መሠረት መጣሉን” የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ተናገሩ።

    ንግግሩ ከተጀመረ በኋላ የኢራን ልዑካን ረግጠው ለመውጣት ቢዝቱም በሁለቱ አገራት ተወካዮች መካከል የሚካሄደው ድርድር ለረጅም ሰዓታት ቀጥሎ ነው አዎንታዊ ደረጃ ላይ መድረሱ የተነገረው።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ተመልሰው ወደ ኢራን በመግባት በመጀመሪያ ደረጃው ንግግር ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች ማክበሯን ያረጋግጣሉ ተብሏል።

    በአሜሪካም በበኩሏ ኢራን የተለያዩ የእህል ምርቶችን ከውጭ ለመግዛት እንድትችል ለማድረግ ሲባል የታገደባት ሀብት እንዲንቀሰቀስ ትፈቅዳለች።

    ወሳኙ የባሕር ላይ መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ “ክፍት ነው” ያሉት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት፣ በሊባኖስ የሚካሄደውን ጦርነት በተመለከተም ተገቢው ቅንጅት እና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ንግግር ማድረግ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

  20. የመጀመሪያው ቀን ድርድር ሲጠናቀቅ፤ በቀጣይ ቀናት የቴክኒክ ውይይት እንደሚቀጥል ተገለጸ

    የኢራን እና አሜሪካ የመጀመሪያ ቀን ድርድር የተገባደደ ሲሆን፤ ሳምንቱን በሙሉ በስዊትዘርላንድ የቴክኒክ ጉዳዮች ውይይት እንደሚቀጥል ተገልጿል።

    አደራዳሪዎቹ ኳታር እና ፓኪስታን “የኢስላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ማዕቀፍን በተመለከተ የመጀመሪያው ዙር ንግግር ተገባዷል” ብለዋል።

    በተቀረው የሳምንቱ ቀናት የቴክኒክ ውይይት እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን በቀጣይ 60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ላይ መስማማታቸው ተመልክቷል።

    በሊባኖስ ጦርነቱን ማስቆም የሚቻልበት መንገድ መዘርጋት ላይም መግባባት ላይ መደረሱን አሸማጋዮቹ አስታውቀዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ድርድሩን “ትልቅ ለውጥ” የታየበት እንደሆነ በኤክስ ገጻቸው ተናግረዋል።

    “በነዳጅ እና በፔትሮኬሚካል የወጪ ንግድ ላይ የተጣለው እገዳተነስቷል” ሲሉም አክለዋል።