ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ከጉልበት ብዝበዛ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ በሌሎችም ላይ አዲስ ታሪፍ ጣለች
አሜሪካ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ 60 የዓለም አገራት የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት ተገቢውን ጥረት አላደረጉም በሚል ከ10 እስከ 25 በመቶ ታሪፍ ጣለች።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ጥለውት የነበረውን ታሪፍ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ካደረገባቸው በኋላ አዳዲስ ታሪፎችን ሲጥሉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ከ60ዎቹ የንግድ አጋሮቻቸው መካከል ዩናይትድ ኪንደም፣ አውሮፓ ኅብረት፣ ካናዳ፣ ሕንድ እና ጃፓን የሚገኙበት ሲሆን ለአሜሪካ በሚሸጧቸው ሁሉም ቁሰቁሶች ላይ ታሪፉ እንደሚጣል ይፋ ተደርጓል።
እንዲሁም ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ በተጨማሪም የዓላማችን ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤት ሆነችው ቻይና በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተዋል።
የአሜሪካ ንግድ ቢሮ አገራቱ ታሪፍ የሚጣልባቸው በጉልበት ብዝበዛ የተመረቱ ምርቶች ለአሜሪካ ገበያ እንዳይቀርቡ ማድረግ ባለመቻላቸው ነው ብሏል።
ትራምፕ የሚጥሉት ታሪፈ በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት ዋጋ ንረት እያስከተለ ነው የሚል ትችት ይቀርብበታል።
የአሜሪካ መንግሥት በጉልበት ብዛበዛ የተመረቱ ምርቶችን ከሚገዙ አገራት ጋር መነገድ ለአሜሪካ ኢፍትሃዊ ነው የሚል አቋም ያራምዳል።
የአሜሪካ ንግድ ቢሮ ተወካይ ጃሜይሰን ግሪር ታሪፉ "የአሜሪካ ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ የፉክክር መድረክ እንዲወዳደሩ ያስችላቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
የታሪፉ ውሳኔ የተሰማው አሜሪካ በመጋቢት ወር በ60 የንግድ አጋሮቿ ላይ ምርምራ ማድረግ መጀመሯ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ምርመራውን ተከትሎ የአሜሪካ ንግድ መሥሪያ ቤት ሁሉም 60 አገራት "ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ጉልበት ብዝበዛ መከላከል ወይንም በጉልበት ብዝበዛ የተመረቱ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ሕጋዊ ክልከላ ማድረግ አልቻሉም" ብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር በየካቲት ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 'ሊብሬሽን ዴይ ታሪፍ' እየተባለ የሚጠራውን ቀረጥ ሕገ ወጥ ነው ብሎ ከወሰነ በኋላ አዲስ ታሪፍ አላስተዋወቀም።
ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "አስቀያሚ" ሲሉ የጠሩት ሲሆን የንግድ ፖሊሲያቸውን ውድቅ ያደረጉትን ዳኞች "ሞኞች" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እንዳሳወቀ በዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ መጣሉን ያስታወቁ ሲሆን በኋላ ወደ 15 በመቶ ከፍ አድረገውታል።
ነገር ግን ታሪፉ 10 በመቶ ሆኖ ቀጥሎ ትራምፕ እና ባለሥልጣኖቻቸው ግን ወደ 15 በመቶ ከፍ ይላል ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ምክር ቤት እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ካላራዘመው ቀረጡ ጊዜው ያበቃል።