ዝናብ ሲመታን የምናገኛቸው አራት ጥቅሞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ በተጠናከረው የክረምት ወቅት ዝናብ እንዳይመታዎ እየሸሹ ከሆነ ይህ ዘገባ ለእርስዎ ነው።
ዝናብ ሰውነታችን ላይ ሲያርፍ ስለሚያሳድረው ጥቅም በዝርዝር እንቃኛለን።
ለዓመታት የተደረጉ ጥናቶች ዝናብ ስሜትን መለወጥ የሚችል አቅም እንዳለው ያሳያሉ።
ሳይንቲስቶች በዝናብ ቅንጣቶች ላይ ያደረጓቸው ምርምሮችም ይሄንን ያረጋግጣሉ።
ዝናብ ስሜትን ከመለወጥ ባሻገር አየርን ከብክለትም ይከላከላል። የዝናብ ሽታ ትውስታ ቀስቃሽም ነው።
ዝናብ ሲመታን የምናኛቸውን አራት ዋና ዋና ጥቅሞች እንመልከት።
1. የሴሮቶኒን መጨመር
ዝናብ ተጨማሪ ኤሌክትሮን ያላቸው የኦክስጅን ሞለኪውሎች ይዟል። ይህም ኔጌቲቭ አዮንስ ይባላል። የዝናብ ቅንጣቶች መሬት ሲነኩም ንጥረ ነገሩ ይሰባበራል።
ንጥረ ነገሩ በከፍተኛ መጠን ሲለቀቅ የሴሮቶኒን ሆርሞን መጠንን ይጨምራል።
ሴሮቶኒን ስሜትን፣ እንቅልፍን እና የምግብ ፍላጎትን ጨምሮ ሌሎችም የአንጎል ክንውኖችን ይቆጣጠራል።
ዝናብ ከሴሮቶኒን በተጨማሪ 'አልፋ ዌቭ' የተባለውን የአንጎል ንቅናቄ መጠን ይጨምራል።
አልፋ ዌቭ ስንረጋጋ ወይም ዐይናችንን ጨፍነን ስንዝናና የሚፈጠረው የአንጎል ንቅናቄ ነው።
እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደስተኛ የሚያደርጉ እና አእምሮን የሚያዝናኑ ናቸው።
ዝናብ መሬት ላይ ወርዶ ኔጌቲቭ አዮንስ (negative ions) የሚለቅበት ሒደት ሌናርድ ኢፌክስ (Lenard effect) ይባላል።
እናም የሴሮቶኒን መጠን የሚጨምር ኔጌቲቭ አዮንስ ማግኘት ከፈለጉ በመብረቅ እንዳይመቱ ተጠንቅቀው በዝናብ ውስጥ ይጓዙ።
አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ኔጌቲቭ አዮንስ በደም ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን ስለሚጨምሩት የስሜት መነቃቃት እንደሚፈጠር ያምናሉ። ይህም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋር የሚስተካከል ነው።
ይሄንን ውጤት የሚያስከትለው ትክክለኛ ሒደት ምን እንደሚመስል ግን ግልጽ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአሜሪካ፣ ፔንስልቬኒያ በሚገኘው ሞኔል ኬሚካል ሴንስስ ሴንተር ውስጥ ኮግኒቲቭ ሳይንቲስት የሆኑት ፓም ዳልቶን እንደሚሉት፤ ኔጌቲቭ አዮንስ የስሜት ለውጥ የሚያመጡበት ምክንያት ግልጽ አይደለም።
ኔጌቲቭ አዮንስ በድካም ወቅት የሚያነቃቁበት፣ የልብ እና ደም ሥር ጤናን እንዲሁም የደም ግፊትን የሚያስተካክሉበት ምክንያትም አልታወቀም።
"በጣም አስደናቂ ነገር ቢሆንም የሰውነት ክፍሎች አሠራር ላይ የሚሰጡት ጠቀሜታን በተመለከተ የሚያግባባ መረጃ የለም። ኔጌቲቭ አዮንስ እንዴት እነዚህን ውጤቶች እንደሚያመጡም በአግባቡ አይታወቅም" ይላሉ ባለሙያዋ።
ኔጌቲቭ አዮንስ ስሜት አነቃቂ መሆናቸውን የሚያሳዩ ጥናቶች መሠራት የጀመሩት በአውሮፓውያኑ በ1950ዎቹ ነው።
በ1990ዎቹ ከፍተኛ መጠን ያላቸው አዮኖች ኔጌቲቭ አዮኖች በውጤታማ ሁኔታ የሚፈጥሩበት መንገድ እስከሚታወቅ ድረስ ግን እርግጠኛ ውጤት ላይ መድረስ አልተቻለም።
በ1995 በተሠራ አንድ ጥናት፤ ከወቅት ጋር የሚከሰት ድባቴ ያለባቸው ሰዎች በየቀኑ ከፍተኛ አዮን እየተሰጣቸው ታክመዋል።
አነስተኛ አዮን ከተሰጣቸው ሰዎች በበለጠ ስሜታቸው ላይ መሻሻል ታይቷል።
ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ማይክል ታሀን እንደሚሉት ከፍተኛ ዝናብም ኔጌቲቭ አዮንስ ይይዛል።
2. ንጹህ አየር ማግኘት
የዝናብ ኔጌቲቪ አዮንስ አየርን ከበካይ ንጥረ ነገሮች ያጸዳል። በቀላሉ መተንፈስ እንድንችልም ይረዳናል።
ንጹህ አየር ስሜትን እና ጤናን ያስተካክላል። የአየር ብክለት ጭንቀትን ጨምሮ ለሌሎችም የአእእምሮ እክሎች ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ኮግኒቲቭ ሳይንቲስት የሆኑት ፓም ዳልቶን "ኔጌቲቭ አዮንስ አቧራ፣ ባክቴርያ፣ አለርጂን እና ሌሎችም ቅንጣቶችን ከአየር እንደሚያጸዱ ጥሩ ማስረጃ አለ። ለመተንፈሻ አካል ጤና ከፍተኛ ሚና አላቸው" ይላሉ።
ተመራማሪዎች የተለያዩ ቅንጣቶችን በጠርሙስ ውስጥ በመበተን የዝናብ ውሃ ጨምረውበት የሠሩት ጥናት ውጤት በአውሮፓውያኑ ይፋ ተደርጓል።
ዝናቡ ቅንጣቶቹን መሰብሰቡን አጥኚዎቹ ደርሰውበታል።
ዝናብ ሲጥል ጥቃቅን ቅንጣቶችን ከአየር እንደሚያጸዳ በአሜሪካ፣ ኢንዲያና በሚገኘው ፑርዱ ዩኒቨርስቲ የመሬት ጥናት ባለሙያ እና ከጥናቱ ፀሐፊዎች አንዱ ዳን ሲስኮ ይናገራሉ።
ኔጌቲቭ አዮንስ አየርን የማጽዳት ሒደት በማድረግ በካይ ቅንጣቶችን እንደሚሰበስቡ ያስረዳሉ።
የግንባታ ቦታ ላይ ውሃ ሲርከፈከፍ አቧራ ወደ መሬት እንደሚመለሰው ማለት ነው።
"የዝናቡ መጠን ከፍተኛ ሲሆን የማጽዳት አቅሙም ይጨምራል" ይላሉ።
በሌላ በኩል ፖዘቲቭ አዮንስ አየርን በመበከል ሰዎች ላይ የጭንቀት እና ቁጣ ባህሪ ያሳድራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
3. ወደ ድሮ ትውስታ መመለስ
የዝናብ ሽታ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ውጤት ሌላው ጠቀሜታው ነው።
ዝናብ መሬትን ሲነካ የሚፈጠው ሽታ ንጹህ እና ትውስታ ቀስቃሽ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ግሪንዊች የእጽዋት ኬምስትሪ አጥኚ ፊል ስቴቨንሰን እንደሚሉት፤ ዝናብ የሚፈጥረው የሥነ ልቦና ውጤት መሬት ላይ ከሚጥለው ቅንጣት ጋር የሚተሳሰር ነው።
"በደረቅ ወቅት ከእጽዋት፣ እንሰሳት እና አፈር የሚነሳ ሞለኪውል ከባቢ አየር ውስጥ ይገባል። ዝናብ ሲጥል እነዚህ ሞለኪውሎች ይፈራርሳሉ" ሲሉ ያብራራሉ።
ዝናብ የሚፈጥረው ንጹህ ሽታ ከኦዞን ሽፋን ጋርም ይተሳሰራል።
ዝናብ አፈርን ሲነካ የሚፈጠው ሽታ የተለየ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ዝናብ በአፈር ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮችን ስለሚያወጣ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ።
የሰው ልጆች ይሄ ሽታ በጉልህ ይሰማቸዋል።
በዝግመተ ለውጥ የሰው ልጆች ይህንን ሽታ በርካታ ንጹህ ውሃ ከማግኘት እና ከመረጋጋት ጋር እንዳስተሳሰሩት ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።
ቀደምት የሰው ልጆች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ሆኖ እንዲሰማቸው ማድረጉንም ይገልጻሉ።
ሽታው ዘና ከማለት ጋር ይተሳሰራል። የቀደመ ትውስታን በማነቃቃት ረገድም ከፍተኛ ሚና አለው።
ኮግኒቲቭ ሳይንቲስቷ ፓም ዳልቶን "ዝናብ ሊመጣ ሲል ያለው ሽታ እና ከዘነበ በኋላ ያለው ሽታ የትውስታን በር ይከፍታል። ወደ ብዙ ቦታዎች እና ስሜቶች ይወስደናል" በማለት ይገልጹታል።
ዝናብ፤ ስሜትን እና ትውስታን የሚያብላላው የአእምሮ ክፍል አሜግድላ እንዲነቃቃ ያደርጋል።
ትውስታችንን ግልጽ ባለ መንገድ የምየውም በዚህ ምክንያት ነው። የዝናብ ሽታ ጥሩ ነው ወይም መጥፎ ነው ብለን ብናስብም ትውስታ መቀስቀሱ አይቀርም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
4. የሚያዝናና ድምጽ መስማት
ዝናብ ሲሸተን፣ ሲነካንም ከሚፈጥረው ጥሩ ስሜት በተጨማሪ ድምጹም ዘና ያደርጋል።
ከጀርባ የዝናብ ድምጽ የታከለባቸው ሙዚቃዎች የሚሠሩም ይሄንን ስሜት ተመርኩዘው ነው።
የዝናብ ድምጽ የኮሪሶል መጠንን በመቀነስ ጭንቀትን ያስወግዳል። የሚያውኩ ደምጾችን ለማስወገድም ያግዛል።
በአሜሪካ፣ ሳውስፊልድ ክሊኒካል ኦውዲዮሎጂስት የሆኑት ኤሚ ሳሮው "የመዝናናት ስሜት የሚፈጥረው የአንጎል ክፍል በዝናብ ድምጽ ይነቃቃል" ይላሉ።
የዝናብ ድምጽ የልብ ምትን በመቀነስ ጭንቀትን የማርገብ ውጤት ያሳያል።
በቅርብ የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው፤ የዝናብ ድምጽ ከፍተኛ ውጤት የሚያሳየው ከ40 እስከ 50 ዴሲባል ደረጃ ላይ ሲሆን (በስሱ የሚሰማበት መጠን) ነው።
በስሱ የሚሰማ የዝናብ ድምጽ 65% ጭንቀትን ይቀንሳል።
የዝናብ ድምጽ የሚፈጥረው የሚያዝናና ስሜት በቀላሉ እንቅልፍ እንዲወስደንም ይረዳል።
ሰዎች ዘና ለማለት ብለው የዝናብ ድምጽ ሲሰሙ ተመስጦ (meditation) ውስጥ በመግባት የተሻለ የአእምሮ መረጋጋት ይፈጠራል።
ዝናብ የተሻለ ስሜት ውስጥ የሚከተን፣ አሁን ላይ እንድንሆን የሚያደርገን፣ የሚያዝናን የሆነውም በእነዚህ ምክንያቶች ነው።















