የፊፋ ፕሬዝዳንት የሰረዙት የዓለም ዋንጫን ለባለሀብቶች የመሸጥ ዕቅድ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም ዋንጫ የንግድ ድርሻን ለግል ባለሃብቶች ለማስተላለፍ ተይዞ የነበረው ዕቅድ መሰረዙን ይፋ አድርገዋል።
ዕቅዱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (ዩኢኤፍኤ) በፊፋ ፕሬዝዳንት አመራር "እምነት ማጣቱን" አስታውቋል።
55 አባላት ያሉት ኅብረቱ፤ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ድርሻ ለግል ባለሃብቶች የመሸጥ ዕቅድ ተግባራዊ መሆን የሚጀምር ከሆነ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች እንደማይሳተፍም ገልጿል።
በፊፋ ፕሬዝዳንት ላይ የተቃጡ ጠንካራ ትችቶች በመግለጫው ተካትተዋል። "የተዝረከረከ" እና "ምሥጢራዊ ማጭበርበሮች" የሚሉ ቃላት ተጠቅመዋል።
ክስተቱ በአውሮፓውያኑ 2021 በአውሮፓ ሲፐር ሊግ (ኢኤስኤል) የተፈጠረውን ውዝግብ ያስታውሳል። ሊጉ ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ጨምሮ 12 የአውሮፓ ትልልቅ ክለቦችን ያካተተ ነበር።
የቀድሞው የእንግሊዝ ተከላካይ ጋሪ ኔይቪል የፊፋን ዕቅድ "ፍጹም ስግብግብነት" ሲል ነው የገለጸው።
ኢንፋንቲኖ ይፋ ያደረጉት የዓለም ዋንጫ የንግድ ድርሻን ለግል ባለሃብቶች ለማስተላለፍ ተይዞ የነበረው ዕቅድ ብዙም ይሁንታን አላገኘም።
ዕቅዱ መሰረዙን ቢናገሩም ያስከተላቸው ትችቶች በቶሎ የሚረሱ አይመስልም።
እግር ኳስ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኝ ጨዋታ ነው። ተጫዋቾች እና የክለብ ባለቤቶች የሚያገኙት ትርፍ ደጋፊዎች ከሚያስቡትም በላይ ነው።
በእግር ኳስ ውስጥ የማይታለፍ መስመር የለም? የሚለውን ጥያቄ አጭሯል።
ከኢንፋንቲኖ ዕቅድ ጀርባ ያለውን መረዳት ያስፈልጋል።
ፊፋ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት አይደለም። ሁለት ቢሊዮን ዶላ ርየሚጠጋ የገንዘብ ክምችት አለው።
ከዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ 15 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢንፋንቲኖ አውጥተውት የነበረው ዕቅድ ላይ አገራት እስከ አውሮፓውያኑ መስከረም 19 ድረስ ፊርማቸውን ማኖር እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
ነገር ግን ለእግር ኳስ እድገት የተመደበውን ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር አገራት አይፈልጉትም።
አብዛኞቹ አገራት የዓለም ዋንጫ የንግድ ድርሻን ለግል ባለሃብቶች ማስተላለፍ ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ አልሆነላቸውም።
ጥያቄያቸውን በይፋ ባይገልጹም ከመጋረጃ በስተጀርባ ለፊፋ የሚሰነዘር ጥያቄ መሆኑ አይቀርም።
የፊፋ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ልዩ አማካሪዎች እና ከፍተኛ አመራሮች ጥያቄ ለማንሳት ዕድል አላገኙም። ዕቅዱ እየወጣ እንደሆነም መረጃው አልነበራቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዕቅዱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (ዩኢኤፍኤ) በይፋ ኮንኗል።
ዕቅዱ ሲሰረዝ ባወጣው መግለጫ "በአሁናዊው የፊፋ አመራር እንዲሁም በሌሎችም የእግር ኳሱ ቤተሰብ አባላት እምነት አጥተናል" ብሏል።
መግለጫው አክሎም "ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በ2016 የፊፋ አባል የሆኑ ማኅበራት ፕሬዝዳንታቸው አድርገው ሲመርጡት ሲጠይቅ 'ግልጽ መሆን አለብን' ብሎ ነበር" ይላል።
ኢንፋንቲኖ የተሰበሰቡትን ባለድርሻ አካላት "የፊፋ ገንዘብ የእናንተ ነው" ማለታቸውንም ይጠቅሳል።
"የፊፋ ፕሬዝዳንት ገንዘብ አይደለም። እናንተ ብሔራዊ ማኅበራት ናችሁ፤ የፊፋ ገንዘብ ለእግር ኳስ እድገት እንጂ ለሌላ ዓላማ አይውልም ብሏል" በማለት መግለጫው የፕሬዝዳንቱን ንግግር ያስታውሳል።
"ሁለቱንም ቃል የገባቸውን ነገሮች አፍርሷል" ሲልም ኢንፋንቲኖን ወቅሷል።
ከፊፋ እና ፕሬዝዳንቱ ጋር በተያያዘ የግልጽነት ጉዳይ ሲነሳ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ከስምንቱ የፊፋ ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት የእስያ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ኤኤፍሲ) ፕሬዝዳንት ሼኽ ሳልማን ቢል ኢብራሒም አል ኻሊፋ ከዚህ ቀደም ይሄንኑ ጉዳይ አንስተዋል።
ማንኛውም ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ውሳኔ "በተገቢው ጊዜ፣ በግልጽነት እና ትርጉም ባለው ሁኔታ" ለአባላት መቅረብ አለበት ብለዋል።
"የእግር ኳስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን ያለበት በተገቢው ምክክር፣ በጋራ ውይይት እና ጨዋታውን እንዲመራ ለተቋቋመው አመራር ክብር በማሳየት መሆን አለበት" ሲሉም አክለዋል።
የአውስትራሊያ እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ አንተር አይዛክ በበኩላቸው እምነት ማሳደር የሚቻለው "በጥሩ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ወደ ውሳኔ ባመራው ሒደት ታማኝነት ጭምር ነው" ብለዋል።
"እግር ኳስ አንድ ቦታ ቆም አያውቅም፤ መቆምም የለበትም" ሲሉም ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም "አንዳንድ መርሆች መቀየር የለባቸውም። እነዚህም ታማኝነት፣ ገለልተኛነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ግልጽነት፣ ትርጉም ያለው ምክክር እና ተገቢው ሒደት ናቸው። እነዚህ እድገትን አያሰናክሉም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዕቅዱ ያስነሳው ቅሬታ
ክስተቱ በአውሮፓውያኑ 2021 በአውሮፓ ሲፐር ሊግ (ኢኤስኤል) ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር ተነጻጽሯል።
በወቅቱ ተቃውሞ ያሰሙት የእግር ኳስ ደጋፊዎች ነበሩ። ፕሪሚየር ሊጉ፣ የእግር ኳስ ማኅበር እና ንጉሥ ዊልያምም ድጋፍ ሰጥተዋል።
ሁሉም ክለቦች በየሳምንት እኩሌታው በብሔራዊ ሊግ ሥር ሆነው እርስ በርስ እንዲገጠሙ ዕቅድ ወጥቶ ነበር።
ነገር ግን ክለቦች በሊግ ታጥረው በማስታወቂያ እና እግር ኳስን በማሠራጨት ከሚገኝ ገቢ ራሳቸውን በሃብት የሚያበለጽጉበት ዕቅድ ነው በሚል ተተችቷል።
ለአገር በቀል የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ከለላ መሰጠት አለበት የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር።
ዕቅዱ ለ72 ሰዓታት ትችቶች ከቀረረቡበት በኋላ ተሰርዟል።
ክለቦች አስተያየት የመስጠት ዕድል ሳያገኙ ዕቅዱ ሾልኮ ጋዜጠኞች እጅ ገብቶም ነበር። ስለዚህም የሰላ ትችት ቀርቦበታል።
ፊፋ ባወጣው ዕቅድ የገጠመው ሂስም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ፊፋ የዕቅዱን መከራከሪያ ነጥቦች ይፋ አድርጓል። "አቅጄው የነበረው የምክክር መድረክ በመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ተሰናክሏል" ሲልም ገልጿል።
የፊፋ ዕቅድ እያወዛገበ ሳለ ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ ኬቨን ላሞር "የአንድ ሰው ፕሮጀክት ነው" ማለታቸው ነገሮችን አክርሯል። የፊፋ አስተዳደር "ተታልሏል" ሲሉም ተናግረዋል።
ቢቢሲ ስፖርት ከፊፋ ምላሽ ጠይቋል።
ኬቨን ላሞር ለቀጣሪ ድርጅታቸው ፊፋ ታማኝ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ቢገልጹም "አንዳንድ መርሆችን" በተመለከተ የሥራ ባልደረቦቻቸውን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
"በመቶዎች የምንቆጠር የሙያው ፍቅር ያለን የፊፋ ተምሳሌት የሆንን ሠራተኞች ለእግር ኳስ ታማኝ ነን" ብለዋል።
"ሥራዬን የማጣው ከሆነም ልጣው፤ ውሳኔውን አከብራለሁ። ነገር ግን ቢያንስ ጥሩ እንቅልፍ እተኛለሁ" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢንፋንቲኖ እና ትራምፕ ግንኙነት
ኢንፋንቲኖ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የቅርብ ግንኙነት መሥርተዋል። በጋራ የዓለም ዋንጫን ለስፔን አስረክበዋል።
ትራምፕ ዕቅዳቸውን ደግፈው እንደሆነ የተጠየቁት የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ድጋፍ እንዳላገኙ ተናግረዋል።
ትራምፕም ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጋር አለመነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ኒው ዮርክ ፖስት የዕቅዱን መሰረዝ በሚመለከት ባወጣው ዘገባ ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጭን ጠቅሶ ጉዳዩ ለትራምፕ አማች ወንድም ጆሽዋ ኩሽነር "አስፈሪ ሕልም" መሆኑን ገልጿል።
የትራምፕ ልጅ ባለቤት የሆነው ጃሬድ ኩሽነር ወንድም ጆሽዋ ኩሽነር፤ ዕቅዱን የመራው የአሜሪካው የካፒታል ተቋም 'ትራይቭ ኢተርናል' መሥራች ነው።
የፊፋ ዕቅድ ተግባራዊ ቢሆን መሪ የሚሆነው ይህ ተቋም ነው።
ሆኖም ግን ኢንፋንቲኖ ዕቅዱን ከመሰረዝ ውጭ አማራጭ አላገኙም።
የፊፋው ፕሬዝዳንት ከወራት በኋላ በድጋሚ ለመመረጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ባወጡት ዕቅድ ምክንያት ከገጠማቸው ተቃውሞ ማገገም ይኖርባቸዋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ላውራ መካልስተር ለቢቢሲ "ማኅበራቱ ሁሉንም አማራጭ እያዩ ነው። አሁን ላይ ለመናገር ገና ቢሆንም ሰዎች አቋማቸውን እንዲያሳዩ እንቅስቃሴዎች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።
"የዚህ ሳምንት ቁልፉ ነገር ዕቅዱን ውድቅ ማድረግ ነበር። በአንድነት እና በመግባባት ያንን ማሳካት ችለናል" ሲሉም አክለዋል።
እግር ኳስ ለውጦችን ለማስተናገድ ቢችልም ሁሉም የለውጥ ሐሳቦች ተቀባይ እንደማይሆኑ የታየበት አጋጣሚ ሆኗል።















