ፍትሕ የተጠሙ የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎች አቤቱታ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽ
![ቀነኒ አዱኛ፣ ሜላት ተሰማ፣ ፀጋ በላቸው፣ ዘውዱ ሃፍቱ፣ ሃይማኖት በዳዳ [ከቀኝ ወደ ግራ]](https://bbcinsight.pages.dev/_bbc-assets/ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/1f2f/live/fcf8c5a0-b109-11f1-bc1f-3f186ca4140c.png.webp)
የፎቶው ባለመብት, BBC/MELAT/SM
ሜላትን ሳነጋግራት የታዳጊ ልጆቿ ድምጽ ከጀርባዋ ይሰማኝ ነበር። ልጆቿ እንዳይሰሙ በሚመስል ሁኔታ ድምጿን ዝቅ አድርጋ ነበር የምታወራው። የደረሰባት ጥቃት ግን ከልጆቿ ዓይን የተደበቀ አይደለም።
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሜላት ከዓመታት በፊት በተፈፀመባት የአሲድ ጥቃት ከፀጉሯ ጀምሮ በግማሹ የሰውነት ክፍሏ ላይ ጉዳት ደርሶባታል።
የአንድ ዓይኗን ብርሃን አጥታለች፤ አንድ ጆሮዋም መስማት የጀመረው ከብዙ የሕክምና ክትትል በኋላ ነው። ሐኪሞች የቃጠሎው ደረጃ 33 በመቶ እንደሆነ ነግረዋታል።
ሜላት ለቢቢሲ እንደገለፀችው ጥቃቱን በማስፈፀም የተከሰሰው የቀድሞ ባለቤቷ የተፈረደበት16 ዓመታት እስር በይግባኝ እና በአመክሮ ተቀንሶለት አምስት ዓመታትን በእስር ካሳለፈ በኋላ ተለቋል፤ ድርጊቱን በተባባሪነት የፈፀመው ግለሰብ ግን እስካሁን አልተያዘም። ዓመታት ቢነጉዱም ሜላት የደረሰባት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አብሯት አለ።
ምንም እንኳን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ የማለት መብት እንዳላት ብታውቅም ፋይሉ እንዲዘጋ ወስናለች።
"ከጉዳቴ በላይ በፍትሕ ሒደቱ ያሳለፍኩት ውጣ ውረድ ስለከፋ ፍትሕ ሳላገኝ ቀርቻለሁ።" ትላለች።
የእርሷን ስሜት ሌሎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የጥቃት ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው ይጋሩታል።
ፀጋ በላቸው ሐዋሳ ከተማ ከሚገኘው የሥራ ቦታዋ ተጠልፋ የተደፈረችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። ድርጊቱን በፈፀመው ግለሰብ ላይ የ16 ዓመት ፅኑ እስራት ቢወሰንም፣ ካሳለፈቻቸው የሰቆቃ ቀናት እና ጥሎባት ካለፈው ጠባሳ አንፃር ፍርዱ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ነው የሚሰማት።
"ይህም ቢሆን የተገኘው በጩኸት እና በትግል ነው" ትላለች።
በባሕር ዳር ከተማ ተደፍራ ለተገደለችው የሰባት ዓመቷ ሄቨን አወትም 25 ዓመታት እስር ተፈርዶላት የነበረ ሲሆን፣ በይግባኝ ወደ 23 ዓመት ዝቅ ተደርጓል። የክስ መዝገቡ ግን እስካሁን አልተዘጋም።
እናቷ አበቅየለሽ አደባ ከደረሰባት መሪር ሐዘን እና እንግልት አልወጣችም። የልጇ ግድያ ለሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደዳረጋት ትናገራለች።
ከሁለት ዓመት በፊት ሕይወቷ ላለፈው ቀነኒ አዱኛ እንዲሁም በመቀለ ከተማ አሸንዳን አክብራ ስትመለስ በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደለችው ዘውዱ ሃፍቱም ፍትሕ ፊቷን አዙራለች ይላሉ ተሟጋቾች።
በእነዚህ እና በሌሎች ሴቶች ላይ ለደረሰው ጥቃት እና ግድያ ፍትህ ለመጠየቅ እንዲሁም የሴቶች ጥቃት 'ብሔራዊ ቀውስ' ሆኖ እንዲታወጅ የሚጠይቁ "ጥቁር አሸንዳ" እና "ትሰማ!" የሚሉ ንቅናቄዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ቢቢሲ በቅሬታዎቹ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴርን ምላሽ ጠይቋል።
ሚኒስቴሩ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ጥቃቶች የሚደርሱት በአብዛኛው በቅርብ ሰዎች እና በድብቅ መሆኑ የሚፈጥራቸው የባህል፣ የማስረጃ መሰወር፣ መጥፋት እና ሌሎች ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቅሶ፣ ሪፖርት የማይደረጉ ኬዞች ስለሚኖሩ "ተጎጂዎች ሙሉ በሙሉ ፍትሕ አግኝተዋል" ማለት እንደማይችል ገልጿል።
ነገር ግን "ተጎጂዎች ወደ ፍትሕ አካላት ከመጡ በኋላ ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ በልዩ ሁኔታ እየተሰራ ነው" ብሏል።
"ባለፈው ዓመት ብቻ ከ12 ሺህ በላይ ጉዳዮች መጥተዋል"
የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት በዚህ ዓመት ባወጣው መረጃ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሚሆናቸው 24 በመቶ ሴቶች ከ15 ዓመት ዕድሜያቸው አንስቶ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ 8 በመቶ የሚሆኑት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በዘጠኝ ክልሎች ለተጎጂዎች ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጠው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርም ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከ12 ሺህ በላይ ለሆኑ ሴቶች ድጋፍ እንደሰጠ ለቢቢሲ ገልጿል።
የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕብረት አባሆይ እንዳሉት ከእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ 1500 የሚሆኑት መድፈርን ጨምሮ ፆታዊ ጥቃቶች ናቸው።
ጥቃት ከደረሰባቸው 10 ሴቶች መካከል ሪፖርት የሚያደርጉት አራቱ ብቻ እንደሆኑ እና ከእነዚህም ውስጥ የሕግም ሆነ የጤና ድጋፍ ፈልገው የሚመጡት ከሁለት ያነሱት እንደሆኑ ዳይሬክተሯ ጥናቶችን አጣቅሰዋል።
ለዚህም "ባህል፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ለሴቶች ያለው ቦታ እና ግምት፣ ድርጊቱን እንደ ጥቃት አለማየት፣ የፍትሕ አካላት ተደራሽ አለመሆን፣ በፍጥነት ፍትሕ አለማግኘት እንዲሁም የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው" ብለዋል።
ሆኖም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ12 ሺህ በላይ ጉዳዮች ወደ እነርሱ መምጣታቸው፣ ሪፖርት ያልተደረጉ ጉዳዮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከባለፈው ታኅሣሥ ወዲህ ባሉት ወራት ውስጥም ሰባት ሺህ የሚሆኑ ሴቶች የሕግ ድጋፍ ፈልገው ወደ ማኅበሩ እንደመጡ ዳይሬክተሯ አክለዋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር ለቁጥሩ ማሻቀብ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ አሰራር በመዘርጋቱ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሪፖርት እየተደረጉ በመሆናቸው የመጣ እንደሆነ ገልጾ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰሙ ዘገባዎች ወንጀሎች እንዲፈፀሙ እያነሳሱ መሆናቸውንም በምክንያትነት ጠቅሷል።

ገፍተው ወደ ሕግ ከመጡት ጥቂት የጥቃት ሰላባዎች መካከል ምን ያህሎቹ ፍትሕ እንዳገኙ እንዲሁም የተላለፈው ፍርድ ምን ያህል ተመጣጣኝ እና ፈጣን እንደሆነ የሚያሳይ ጥናት የለም።
ሆኖም ቢቢሲ ከዚህ ቀደም በሸፈናቸው ፆታዊ ጥቃትን የተመለከቱ ዘገባዎች ፍትሕ እንዳገኙ የገለጹ ተጎጂዎች ቢኖሩም በርካቶች ግን በተሰጣቸው ፍርድ ፍትሕ እንደተጓደለ ያምናሉ።
ፍትሕ አግኝተናል ብለው የሚያምኑትም ቢሆኑ ለፍትሕ በመታገላቸው እየደረሰባቸው ያለው ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕብረት ከተጎጂዎች የሚቀርቡላቸው ቅሬታዎች እንዳሉ ይገልጻሉ።
"ጥቃቶቹ ቶሎ ሪፖርት ባለመደረጋቸው ማስረጃዎች ተድበስብሰው በመጥፋታቸው፣ የኢኮኖሚ ጥገኛ በመሆናቸው እና በሚደርስባቸው እንግልት ምክንያት ተገቢውን ክርክር አድርጎ ፍትሕ ያልተገኘባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው" ይላሉ።
ምንም እንኳን ከፍተኛ ውሳኔ እና ካሳ የተሰጣቸው ተጎጂዎች ቢኖሩም "በሚፈለገው ልክ ፍትሕ ተገኝቷል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አያስችልም" ብለዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀል ጉዳዮች አቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማስተዋል አዳነም የወ/ሮ ሕብረትን ሃሳብ ይጋራሉ።
በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ውስብስብ እንደሆኑ ያስረዱት ዳይሬክተሯ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ፍርድ ቤት የማይደርሱ ጉዳዮች በመኖራቸው የጥቃት ሰለባዎች ሙሉ በሙሉ ፍትሕ አግኝተዋል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
ሆኖም በ2018 ዓ.ም ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ክሶች አፈጻጸም ምጣኔ መቶ በመቶ ነው ብለዋል።
"በዘንድሮው ዓመት ነፃ የተወጣበት መዝገብ የለም። እስከ የዕድሜ ልክ እስር ድረስ የተፈረደባቸው በርካታ መዛግብት አሉ። ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ በማድረግ እስከ 12 ዓመት ያስቀጣንበት መዝገብ አለ" ሲሉም አብራርተዋል።
ሴቶች እና ሕጻናትን በተመለከተ አቃቤ ሕግ በልዩ ሁኔታ እየሰራ እንደሆነ እና ሥራውም ውጤታማ መሆኑን አክለዋል።
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መድፈር፣ ጠለፋ፣ ግድያ ከአምስት ዓመት እስር እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት ሊያስከትል ይችላል።
ሆኖም የፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት አስተማሪ አለመሆን ለፆታዊ ጥቃቶች መባባስ ምክንያት እንደሆነ የሕግ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የቅጣት ሁኔታው ቢሻሻል የማስጠንቀቅ አቅሙ ከፍተኛ ይሆናል ሲሉም ወንጀለኞች ላይ የሚተላለፉ ቅጣቶችን የሚወስኑት የሕግ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጥቃት ሰለባዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ግን ከዚህም የተሻገሩ ናቸው።
"ፍትሕ ዝና፣ ገንዘብ እና ሥልጣን ተጭኖታል"
"ልጃቸውን በግፍ እንዳጡ" የሚገልጹት የቀነኒ አባት አቶ አዱኛ በዐቃቤ ሕግ የተመሠረተ ክስ እንደሌለ ይናገራሉ።
ምክንያቱን የተጠየቁት አቶ አዱኛ "ግለሰቡን [አርቲስት አንዱዓለም ጎሳ] ታዋቂ ስለሆነ መክሰስ ስላልፈለጉ እንደሆነ" ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"ለድሃ እና ለተጎጂዎች ይቆማል የሚባለው ፍትሕ ሚኒስቴር ቢሆንም፤ ቅሬታየን እንኳን ለማሰማት አንድ ዓመት ሙሉ ብመላለስም መልስ አላገኘሁም" ብለዋል።
ከሞቷ ጋር በተገናኘ የተደረገው ምርመራም "የይስሙላ" እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
"ቤት ውስጥ አብረው የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ቢኖሩም ተወስዶ የተጠየቀው አንድ ግለሰብ ብቻ ነው፤ ምርመራ ሲካሄድ ቤቱ አልታሸገም ነበር" ሲሉ የምርመራው አካሄድም ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ። "ድራማ እንጂ ምርመራ አይደለም" ሲሉም ይከሳሉ።
በጠላፊዋ እና ደፋሪዋ እጅ የሰቆቃ ቀናትን ያሳለፈችው ፀጋም ገጠመኝ የምትለው ከዚህ የተለየ አይደለም።
ጥቃቱን የፈፀመባት ግለሰብ የቀድሞው የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የግል ጠባቂ ስለነበር ቤተሰብ ለፖሊስ የሚሰጠው መረጃ ቀድሞ ይደርሰው ስለነበር ቦታ በመቀያየሩ የጭንቅ ቀናቶቿን እንዳስረዘመባት ገልጻለች።
ከዚህም በተጨማሪ ዐቃቤ ሕግ ክስ ሳይመሠርት "ጉዳዩ በሽማግሌ እንዲያልቅ ጫና ሲደረግም ነበር" ትላለች።
ሒደቱም ከመጀመሪያው ጀምሮ በፍርሃት እና ስጋት የተሞላ እንደነበር የምታስታውሰው ፀጋ፣ "ፍትሕ እንደካደን፣ እንደማንቆጠር ነው የሚሰማኝ" ብላለች።
የመቀለዋን ወጣት ዘውዱ ሃፍቱን በመግደል የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው ግለሰቦችም የተለቀቁት በባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ይነገራል።
አንደኛው ተከሳሽ ያሬድ ገብረሥላሴ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአርሚ 22 አዛዥ እና አሁን የትግራይ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ኮሎኔል ገብረሥላሴ በላይ ልጅ መሆኑ ነው። ኮሎኔል ገብረሥላሴ ደግሞ የሁለተኛ ተከሳሽ አንገሶም ኃይለማርያም ዘመድ ነው።
በፍርድ ሒደቱ ወቅት ዳኞች ላይ "ጫና እየተደረገ" እንደሆነ ሲገለጽ የነበረ ሲሆን፣ ዳኞች በአንድ ወቅት ላይ ሥራቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ፍርደኞቹ በነፃ መሰናበታቸውን ተከትሎ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ዐቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ ለትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱን ገልጿል።
የዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ ባይሩ፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያስተላልፍ "እየደረሰበት ስላለው ጫና" ያነሳው ነገር እንደሌለም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, SM
ተጎጂዎቹ ያነሷቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ በቢቢሲ የተጠየቁት ወ/ሮ ማስተዋል በበኩላቸው በዝና፣ በሥልጣን ወይም በተለያዩ ነገሮች አድልዎ የሚደረግበት ምንም ዓይነት አሰራር የለም ሲሉ አስተባብለዋል።
ዳይሬክተሯ በተነሱላቸው ኬዞች ላይ በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም "የእኩልነት መርህ መሠረታዊ መርህ ነው፤ በፍርድ ቤት ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው የፍትሕ ሥርዓቱ የሚዳኘው" ብለዋል።
ማስረጃዎችን የሚያቀርበው እና የማስረዳት ሸክም ያለበት አቃቤ ሕግ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም አክለዋል።
ማስቀጣት አንዱ የፍትሕ አካል ነው የሚሉት በዚያው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሴቶች እና ባለ ብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ፣ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ከሚፈፀሙ ጥቃቶች 85 በመቶዎቹ በቅርብ ሰው የሚደርሱ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በመሆኑም እነዚህ ጉዳዮች በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ከገቡ በኋላ በሽምግልና ድርድር፣ ለተበዳዮች ማባበያ በመስጠት፣ በሃይማኖት አባቶች እና በሽማግሌዎች እርቅ ምክንያት መዝገቦች የሚበላሹባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ አንስተዋል።
ነገር ግን እነዚህ ተግባራት " የሰብዓዊ መብትን የሚጥሱ፣ ከአካላዊ ጉዳት እስከ ግድያ የሚያደርስ ጉዳትን የሚያመጣ ነው ብለን ባለው ልዩ የወንጀል ባሕርይ ለማየት እየሞከርን ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Melat Tesema
የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕብረት፣ በደፈናው ዝና፣ ገንዘብ እና ሥልጣን ፍትሕን እያጓደሉ ነው ማለት ቢያደግትም እንደ ማንኛውም የወንጀል ድርጊት ያልተገቡ አሠራሮች እና ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
"ማሳያዎች ስላሉ ሙሉ በሙሉ ከዚህ የፀዳ ነው ማለት አይቻለም" ሲሉም ጥቃት አድራሾች ከአገር እንዲወጡ እንዲሁም ለምስክሮች ገንዘብ በመስጠት እንዳይቀርቡ የማድረግ ሁኔታዎች መታዘባቸውን አክለዋል።
እንደ ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ባሉ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ ባሉ ክልሎች ደግሞ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል። በትግራይ ከጦርነቱ በኋላ የፍትሕ ተቋማት ሥርዓት መዳከም ለፍትሕ እጦት በምክንያትነት ይጠቀሳል።
እንደ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ የሕክምና ምርመራ በሚያስፈልጉ ወንጀሎች ላይም ከፌደራል ተቋማት ጋር ያለው ትብብርም ተሰናክሏል።
ሜላትም የፌደራል እና ሌሎች አካባቢዎች ቅንጅት አለመኖር፣ አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ ታምናለች።
ከዚህም በተጨማሪ ተጠቂዎች ፍትሕ በመጠየቃቸው ድጋሚ ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚያደርግ ዋስትናም ሆነ ከለላ አለመኖሩ አስጊ እንደሆነ ትገልጻለች
አንዳንዴ ጥቃቱ ከማኅበረሰቡም ጭምር የሚመጣ እንደሆነ ትናገራለች።
የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሥልጣኗ ወ/ሮ ዳግማዊትም በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የአሰራር፣ የሕግ [የማኅበራዊ ጥበቃ] ፣ የመረጃ ምዘና [በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ረገድ]፣ የንቃተ ሕግ ክፍተቶች መኖራቸውን ያነሱ ሲሆን ይህንንም ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የቀነኒ አባት አቶ አዱኛ የፍትሕን ደጅ መጥናታቸው ተስፋቸውን ቢያዝለውም "የቀን እና የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የልጄ ደም ይወጣል" ብለዋል። የዘውዱ ቤተሰቦችም ልጃቸውን ከማጣት በላይ ለእነርሱም ስጋት ስለገባቸው ዝምታን የመረጡ ይመስላሉ።
በተሰጣቸው ፍትሕ ደስተኛ ያልሆኑት የሄቨን እናት አበቅየለሽ፣ ፀጋ እና ሜላት በሌሎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ እና የደረሰባቸውም ፍትሕ እንዲያገኙ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።















