በጃፓን እድሜያቸው 100 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ ተሻገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጃፓን እድሜያቸው 100 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ መድረሱን የአገሪቷ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጃፓን አሁን ላይ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የኖሩ የ107 ሺህ 677 ሰዎች መኖሪያ ሆናለች። ይህ ቁጥር በዓለም ላይ ከፍተኛው ሲሆን 88 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።
በእድሜ አንጋፋዋ ሴት ኪሺሞቶ ፉዮ የተባሉ የኪዮቶ ነዋሪ ሲሆኑ ዕድሜያቸው 114 ነው። በእድሜ አንጋፋው ወንድ ደግሞ የኩማሞቶ ነዋሪ የሆኑት የ112 ዓመቱ ካቶ ሂካሩ ናቸው።
የጤና ሚኒስትሩ ኪኒቺሮ ኡኖ " በርካታ ሰዎች ረዥም ዕድሜ በመኖራቸው፣ ጤነኛ እና ንቁ የሆነ ሕይወት እያሳለፉ በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን" ገልጸዋል።
ባለሙያዎች ጃፓናውያን ረዥም ዕድሜ ለመኖራቸው ጤናማ አመጋገብ እና ንቁ የሆነ የአኗኗር ዘይቤን ጨምሮ የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል።
የደሴቲቱ አገር ምግቦች ከምዕራባውያኑ በተለየ በአብዛኛው አሳ፣ አትክልት እና ሩዝ እንዲሁም ብዙ ያልተጣራ ስብ የተካተተበት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አረጋውያን በመደበኛነት በእግራቸው ይጓዛሉ፤ የሕዝብ ትራንስፖርት እና ሳይክል ይጠቀማሉ፤ ሰውነታቸውንም ያፍታታሉ።
በአገሪቷ ለዓመታት በእድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ከአስር ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ የአዋቂዎች የዳይፐር ሽያጭ ከሕፃናት ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል።
ኩባንያዎችም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ እና የተለያዩ የአካል ክፍሎችን እንቅስቃሴ የሚደግፍ እንዲሁም ትኩረት ለማድረግ የሚያስችል የዓይን መነጽርን ጨምሮ ለአረጋውያኑ አዳዲስ ምርቶችን እየሰሩ ነው።
ይህንን የማኅበረሰብ ክፍል በአዲስ ትውልድ ለመተካት አንዲት ሴት በአማካይ 2.1 ሕፃናት መውለድ የሚጠበቅባት ቢሆንም ባለፈው ዓመት የአገሪቷ የወሊድ ምጣኔ ዝቅተኛ ሆኖ ወደተመዘገበው 1.14 አሽቆልቁሏል።
እንደ ብሔራዊ የሥነ ሕዝብ እና ማኅበራዊ ደኅንነት ጥናት ተቋም ከሆነ አጠቃላይ የሕዝብ ብዛቷም በ2008 ከፍተኛ ሆኖ ከተመዘገበው 128 ሚሊዮን በ2070 ወደ 87 ሚሊዮን እንደሚወርድ ተገምቷል።
አሁን ባለው መረጃ ካላት አጠቃላይ ሕዝብ 30 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ ሲሆን በ2070 ቁጥሩ ወደ 40 በመቶ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።
የጃፓን ባለሥልጣናት ሁኔታውን " የሕልውና ቀውስ" ያሉት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳኔ ታኪቺ የሕዝብ ብዛት ማሽቆልቆሉን " እጅግ አሳሳቢ" ብለውታል።
እአአ በ2025 የጃፓን አጠቃላይ ሕዝብ በሁሉም ክልሎች የቀነሰ ሲሆን የወሊድ ምጣኔውም በፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው።
መንግሥት ወጣቶች ብዙ ልጆችን እንዲወልዱ በተለያዩ ፕሮግራሞቹ እና ድጋፎቹ እያበረታታ ቢሆንም ምጣኔውን የጨመረው አይመስልም።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለዚህ እንደ ዝቅተኛ የጋብቻ ምጣኔ እና በርካታ ሴቶች ሥራ ላይ መሰማራታቸው ያሉ ውስብበብ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
ጃፓን እአአ በ1963 ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የኖሩ ዜጎቿ ላይ የዳሰሳ ጥናት መስራት ስትጀምር 100 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ዜጎች ቁጥር 153 ብቻ ነበሩ። ይህ ቁጥር በ1981 ወደ 1000 ከዚያም በ1998 10 ሺህ ደርሷል።
አሁን ላይ ያለው የአረጋውያን ቁጥር የተገለፀው " ክብር ለአረጋውያን" በሚል ከሚከበረው ዓመታዊ የሕዝብ በዓል አስቀድሞ ነው። በዚህ ዕለት መንግሥት 100 ዓመት ለደፈኑ ሰዎች ደብዳቤ እና ባህላዊ መጠጫ በማበርከት ክብሩን ይገልጻል።
መንግሥት አንድ ክፍለ ዘመን እድሜ ያላቸውን ሰዎች ቁጥር ቢያሳውቅም ቀደም ሲል ጥናቶች በዓለም አንድ ክፍለ ዘመን የኖሩ ሰዎች ቁጥር ላይ ጥርጣሬ እንዳለ አመልክተዋል።
የመረጃ ግድፈት፣ አስተማማኝ ያልሆነ የሰነድ አያያዝ እንዲሁም የልደት ምስክር ወረቀት መጥፋት ለቁጥሩ ከፍ ማለት ይጠቀሳል ሲሉ ይሞግታሉ።
የጃፓን መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2010 የቤተሰብ ምዝገባውን በፈተሸበት ወቅት ከ230 ሺህ በላይ እድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ ሆኗቸዋል ተብለው ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከአስር ዓመት በፊት በመሞታቸው ጭምር ሊገኙ አልቻሉም።
ይህ መዛባት የተከሰተው በሰነድ አያያዝ ላይ በተፈጠረ ስህተት እንዲሁም አንዳንድ ቤተሰቦች የሞቱ በእድሜ የገፉ ዘመዶቻቸውን ጡረታቸውን ለመቀበል በማሰብ ሳያሳውቁ በመቅረታቸው ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

![ቀነኒ አዱኛ፣ ሜላት ተሰማ፣ ፀጋ በላቸው፣ ዘውዱ ሃፍቱ፣ ሃይማኖት በዳዳ [ከቀኝ ወደ ግራ]](https://bbcinsight.pages.dev/_bbc-assets/ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/1f2f/live/fcf8c5a0-b109-11f1-bc1f-3f186ca4140c.png.webp)













