ከአሜሪካ ውድድር በመጨረሻው ሰዓት የቀረችው ኢትዮጵያዊት አትሌት የምርመራ ውጤት ያስነሳው ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Athletics Federation/FB
በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ዝግጅት ያደረገችው አትሌት አጃይባ አልዬ በሆርሞን መጠን ውዝግብ ምክንያት ከውድድሩ መቅረቷን ተከትሎ ጉዳይዋ አነጋጋሪ ሆኗል።
አትሌቷ ከውድድሩ ለመቅረቷ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ግልጽነት የጎደለው አካሄድን በምክንያትነት ስትጠቅስ፤ ፌዴሬሽኑ ግን ውሳኔው ከዓለም አትሌቲክስ በመጣ የምርመራ ውጤት ላይ የተመሠረተ ነው ብሏል።
ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ 16 አትሌቶች ወደ አሜሪካ ያቀኑ ሲሆን፣ ሰባት አትሌቶች በተለያዩ ምክንያቶች መጓዝ አለመቻላቸው ተገልጿል።
በውድድሩ ለመሳተፍ የሚያበቃቸውን አነስተኛ ሰዓት ያላስመዘገቡ እና በተጠባባቂነት ተይዘው የነበሩ በአጠቃላይ ስድስት አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ በኩል ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ምክንያት እንዳልተሳተፉ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በሌላ በኩል አትሌት አጃይባ አልዬ፣ ለውድድሩየተደረገላት የሆርሞን ምርመራ ውጤት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ምክንያ ከውድድሩ ውጪ መደረጓን ገልጿል።
ከዚህ ቀደም የ2026 የአፍሪካ የ400 ሜትር ሻምፒዮና የሆነችው የ19 ዓመቷ አትሌት አጃይባ በዘንድሮው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ የሚያበቃትን ፈጣን ሰዓት ሁለተኛ በመሆን አስመዝግባለች።
አትሌቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ልትሳተፍበት በነበረው በዚህ ውድድር ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች እንደነበርም ለቢቢሲ ተናግራለች።
'. . .ማን እንዳስቀረኝ አላውቅም'
የዓለም አትሌቲክስ ባወጣው የተወዳዳሪዎች ዝርዝር ስሟ መካተቱን እና ቪዛዋ ተዘጋጅቶ እንደነበር የገለጸችው አትሌቷ "በሆርሞን ምርመራ ውጤት" በሚል ምክንያት ከውድድር ውጪ መደረጓ እንዳልተዋጠላት አስረድታለች።
"ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ለዓለም ሻምፒዮና ልሄድ የነበረው። ይሄን ዕድል አግኝታ የምትመለስ አይመስለንም የሚል ሃሳብ ኖሯቸው ነው [ያስቀሩኝ]" በማለት ፌዴሬሽኑ እንድትቀር ስለማድረጉ ግምቷን አስቀምጣለች።
ቀደም ሲል እንደዚህ ዓይነት ምርመራ አድርጋ እንደማታውቅ የምትናገረው አጃይባ የምርመራ ውጤቱን በፌዴሬሽኑ በኩል መስማቷን ነው የገለጸችው።
አትሌቷ እንደገለጸችው ከሆነ፣ ከውድድሩ በፊት ሁለት ዓይነት ምርመራዎች ተደርገውላታል። የመጀመሪያው በአገር ውስጥ የተደረገ ሲሆን፣ውጤቱም ሙሉ በሙሉ ለውድድር ብቁ የሚያደርጋት እና ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረበት ገልጻለች።
ሁለተኛው ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ በኩል የተወሰደ የሆርሞን ወይም የፆታ ምርመራ ነው። እንደ አጃይባ ገለጻ "እንደነገሩኝ ከሆነ የዓለም አትሌቲክስ ያደረገው ምርመራ ውጤቱ ከአገር ውስጥ ከተመረመርሽው ጋር አንድ ዓይነት አይደለም የሚል ነው" ስትል አስረድታለች።
አትሌቷ እንደምትለው "የሆርሞን ምርመራ ውጤት ላይ ችግር ቢኖር እንኳ ውድድር ካለቀ በኋላ ሂደቱ እንደሚቀጥል ወይም ውጤቱ ውድቅ ሊሆን እንደሚችል እንጂ ቀድሞ ውድድር የሚያስከለክል ሁኔታ የለም" የሚል እምነት እንዳላት ተናግራለች።
አትሌት አጃይባ አልዬ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንዳትሳተፍ የተደረገችው ከቴክኒክና ከሕግ ውጪ እንደሆነ በመግለጽ የተሰጣትን ውሳኔ ተቃውማለች።
አትሌቷ የስም ዝርዝሯ እና የምትወዳደርበት ቁጥር ይፋ ከሆነ በኋላ ከቡድኑ ውጪ መደረጓ የአሠራር ግድፈትእንዳለበት ጠቅሳለች።
"ስሜ ዝርዝር ላይ ወጥቷል፤ የምወዳደርበት ቁጥር እና ሁሉም ነገሬ ወጥቷል። ከዚህ በላይ ማን. . . እንዳስቀረኝ እኔ አላውቅም። ከውድድሩ ትቅር ከተባለ ስሜ ዝርዝር ውስጥ አይገባም ነበር" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Athletics Federation/FB
"መምጣት አትችልም"
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በበኩላቸው ከአትሌት አጃይባ የቀረበውን ቅሬታ እንደማይቀበሉት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ ለአጃይባ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደነበር የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ ለአትሌቷ የግል አሠልጣኝ እና ሹፌርን ጨምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላት ዝግጅት ስታደርግ እንደነበር አስረድተዋል።
ኮማንደር ስለሺ እንዳሉት፤ ዝግጅቷን ካጠናቀቀች በኋላ ግን ከዓለም አትሌቲክስ "መምጣት አትችልም" የሚል ኢሜይል ለፌዴሬሽኑ በመድረሱ ምክንያት ልትሄድ አልቻለችም።
ፌዴሬሽኑ፣ አጃይባ ወደ አሜሪካ ካመራች በዚያው ልትቀር ትችላለች ብሎ ይገምታል በሚል ከአትሌቷ ስለቀረበበት ቅሬታ ምላሽ የሰጡት ኮማንደር ስለሺ፤ "እንደዚያ ብናስብ ለምን ቪዛ እንጠይቃለን?. . . እኛ አትሌቶቻችን እንደማይቀሩ ሙሉ እምነት አለን" ብለዋል።
በፌዴሬሽኑ የአትሌቲክስ ሕክምና እና የፀረ-አበረታች ቅመሞች ተጠሪ የሆኑት ዶክተር ቅድስት ታደሰ በበኩላቸው የዓለም አትሌቲክስ ሕግ እና የሕክምና የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት የሕክምና ዝርዝር ውጤቶች የሚላኩት ቀጥታ ለአትሌቷ የግል ኢሜይል ብቻ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
"የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እነዚህን ውጤቶች ወይም ሰነዶች የማግኘት መብት የለውም። ለፌዴሬሽኑ የሚደርሰው አትሌቷ መወዳደር ትችላለች ወይም አትችልም የሚለው ማሳወቂያ ብቻ ነው" ሲሉ ዶ/ር ቅድስት አብራርተዋል።
ዶ/ር ቅድስት አክለውም፤ "እኛ በራሳችን ምርመራ አናደርግም፣ እኛ የማስተባበር እና የክትትል ሥራ ነው የምንሠራው። አትሌቷ በራሷ ኢሜይልየመጣውን መረጃ አልተረዳሁትም ብላ ስትጠይቀን ሕጉን እና ሂደቱን የማብራራት ሥራ ነው የሠራነው እንጂ ማሳወቅ አይደለም" ሲሉ አትሌቷ ውጤቱን "በፌዴሬሽኑ ዶክተር በኩል ነው የሰማሁት" ላለችው ምላሽ ሰጥተዋል።
"ልምምዴን እቀጥለላሁ"
ፌዴሬሽኑ በበኩሉ የምርመራ ሂደቱን የሚያካሂዱት በዓለም አትሌቲክስ መስፈርት መሠረት ዕውቅና የተሰጣቸው ገለልተኛ ተቋማት መሆናቸውን በመግለጽ፣ የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት የክትትል እና የማስተባበር ሥራ ብቻ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል።
እንዲሁም በባለሙያዎች የሕክምና ውጤት ላይ ጣልቃ መግባት ከዓለም አትሌቲክስ ሕግ እና ደንብ ውጪ በመሆኑ፣ አሠራሩ በጥብቅ ሕጋዊ መስመር የተከተለ መሆኑን አስረድቷል።
ኤስአርዋይ (SRY) የሚባለው ሳይንሳዊ ፆታን ለመለየት የሚያገለግል ምርመራ በተለይ በታዋቂ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ በሴቶች ምድብ ውስጥ ለሚወዳደሩ ስፖርተኞች እንደ ግዴታ ማጣሪያ ያገለግላል።
በአብዛኛው በወንዶች ዋይ (Y) ክሮሞዞም ላይ የሚገኘውን እና የወንድነት ፆታን የሚወስነውን SRY የተባለውን ጂን መኖር ወይም አለመኖር ይለያል። ይህ ምርመራ በሴቶች ምድብ ውስጥ ለመወዳደር ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ለሴት አትሌቶች ብቻ የሚደረግ ምርመራ ነው።
በውሳኔው ማዘኗን የገለጸችው አትሌት አጃይባ አልዬ፣ በቀጣይም ተስፋ ባለመቁረጥ ልምምዷን እንደምትቀጥል ተናግራለች።
"በቀጣይ ከዚህ በፊት ያቀድኩትን ነው የማደርገው። ከዚህ ውድድር ቀረሁ ብዬ አሁን ልምምዴን እና ሥራዬን አላቆምም። እሮጣለሁ፤ ማድረግ ያለብኝን ነገር ለአገሬም ለራሴም አደርጋለሁ" ስትል ለቀጣይ ውድድሮች የምታደርገውን ዝግጅት እንደምትቀጥል ለቢቢሲ ገልጻለች።
በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት ዩጂን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 21ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ500 ሜትር፣ 3000 ሜትር፣ 1500 ሜትር፣ 800ሜትር፣ 400 ሜትር እንዲሁም በእርምጃ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።















