በርካታ ምዕራባውያን አገራት "በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሰሜን ኢትዮጵያ የማሸማገል ጥረት" ድጋፋቸውን ገለጹ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአፍሪካ ኅብረት ፌደራል መንግሥት እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮችን ለማሸማገል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የአውሮፓ ኅብረት አባል የሆኑ የ22 አገራት እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ እና ካናዳ ኤምባሲዎች አስታወቁ።

አገራቱ፣ "ክፉኛ በድርቅ በተጎዳው" ትግራይ ክልል የሚጀመር ወታደራዊ ግጭት ለሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝብ "አስከፊ" እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የእነዚህ አገራት ዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎች ይህንን ያሉት ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት አጭር መግለጫ ነው። በመግለጫው ከተካተቱት የአውሮፓ አገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም እና ስፔን ይገኙበታል።

የአውሮፓ አገራቱ እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ እና ካናዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ "በከፍተኛ ስጋት እየተከታተሉት" እንደሆነ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

አገራቱ ይህንን ያሉት ባለፉት ቀናት በትግራይ ክልል የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን የክልሉን መንግሥት የተቆጣጠረው የህወሓት የሚመራው አስተዳደር እየገለጸ ባለበት ወቅት ነው። ሁለት የድሮን ጥቃቶች በተፈጸሙበት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ከ13 ሰዎች በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጾ ነበር።

በዚህ ሳምንት ሰኞ ዕለትም ንደራ በተባለ አካባቢ በተፈጸሙ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሌላ ሰው ደግሞ መቁሰሉን የክልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ፌደራል መንግሥት እነዚህ ጥቃቶች በተመለከተ እስካሁን በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም። ይሁን እንጂ የህወሓት አመራሮች 'ፅምዶ' የተባለ ጥምረት በመፍጠር ከሌሎች ታጣቂዎች እና የውጭ አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ሲከስስ ቆይቷል።

ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ትብብር መፍጠራቸውን የጠቆሙት የህወሓት አመራሮችም፣ የፌደራል መንግሥትን "ማስወገድን" የተመለከቱ ንግግሮችን ሲያደርጉ በይፋ ተሰምተዋል።

ውጥረቱ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ባለበት ወቅት፣ ከፕሪቶሪያ ስምምነት አደራዳሪዎች አንዱ የሆኑት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰኞ ዕለት ከትግራይ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።

ኦባሳንጆ "በአፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ" ግንቦት ላይ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

የአውፓ ኅብረት እና ሦስቱ አገራት ዛሬ ባወጡት መግለጫ፣ "የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ በአዲስ አበባ እና በመቀለ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች ጨምሮ እንደ አዲስ ምክክሮችን ማስጀመራቸውን በጎ እንቀበላለን" ብለዋል።

"ሁሉም አካላት" በ2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተፈረመው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት "ትግበራ ላይ በገንቢ መንገድ እና በቅን ልቦና እንዲሳተፉ እናበረታታለን" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

አገራቱ አክለውም፤ "አስቀድሞም ከፍተኛ ደረጃ በድርቅ በተጎዳው እና ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ባለበት በትግራይ ክልል የሚያገረሽ ወታደራዊ ግጭት ለሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝብ አስከፊ ይሆናል" በማለት አስጠንቅቀዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ ለኦባሳንጆ የሽምግልና ጥረት ያለውን ድጋፍ ገልጿል።

በፕሪቶሪያ ስምምት ምክንያት "ያበቃው አሰቃቂ ሁኔታ ዳግም ያገረሻል በሚል በሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ውጥረት እና ጥልቅ ፍርሃት በተፈጠረበት" በዚህ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ተወካዩ ኦባሳንጆ ሚና "ወሳኝ" መሆኑን ኤምባሲው ገልጿል።

መግለጫውን ያወጡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ እና በአፍሪካ ኅብረት የአሜሪካ ተልዕኮ ጉዳይ አስፈጻሚ ዋልተር ፓርስ "ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወደፊት እጅግ ወሳኝ በሆነው ጉዳይ ላይ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ጋር" ለመነገጋር እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

በህወሓት የሚመራው የትግራይ አስተዳደር ግን ትናንት ባወጣው መግለጫ ኦባሳንጆ ሰኔ ላይ ወደ መቀለ ከተጓዙ በኋላ ትርጉም ያለው ክትትል እና ቁጥጥር ባለመደረጉ ደስተኛ እንዳልሆነ" አስታውቋል። ከፌደራል መንግሥት ጋር ውይይት ለመጀመር "መሠረታዊ እና ቁልፍ" ናቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎችም አስቀምጧል።

"የኢኮኖሚ ማዕቀብና እገዳ መነሳት"፣ "ወታደራዊ ከበባን ማቆም እና የተፈጠረውን ውጥረት ማርገብ" እንዲሁም "የትግራይ ሉዓላዊ ግዛት ወደ ነበረበት መመለስ" የሚሉት ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል ናቸው።

የፌደራል መንግሥት የአሁኑን የኦባሳንጆ ጉብኝት በተመለከተ በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሐምሌ ላይ በጽሕፈት ቤታቸው ኦባሳንጆን በተቀበሉበት ወቅት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት "የቢያፍራን የሰላም ሂደት በመምራት ያካበቱትን ልምድ" እንዳጋሯቸው ገልጸው ነበር። "ኢትዮጵያ በምክክር ለምታረጋግጠው አንድነትና ዘላቂ የሰላም ጉዞ ላይ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው" ብለው ነበር።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን አፍርሰው የህወሓት መሪዎች ከቶቀጣጠሩት በኋላ ባለፉት ወራት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።

ይህንንም ተከትሎ ሸረሪና በተባለ ስፍራ ላይ ወታደራዊ ግጭት መከሰቱ የተዘገበ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ላይ የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸው ተገልጿል።

በዚህም ሳቢያ በሁለቱ ወገኖች መካከል ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት በሕዝቡ ውስጥ ተፈጥሯል።