ህዳሴ ዘመኑ: ቤተ መጻሕፍት የተሰየመላት የዘንድሮ የ12ተኛ ክፍል ፈተና የሴቶች ከፍተኛ ውጤት ባለቤት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ከ550 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 12.8 በመቶ ወይም 70,544 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በዘንድሮው ፈተና ከፍተኛው ውጤት በተፈጥሮ ሳይንስ 591.64 ሲሆን፣ ይህንን ውጤት ያስመዘገበው በኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የተማረው ጃላል ግርማ ነው።

ከሴቶች ከፍተኛው የሆነውን ውጤት ደግሞ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ አገው ምድር ትምህርት ቤት ተማሪዋ ህዳሴ ዘመኑ 583.03 በማምጣት አስመዝግባለች።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ የተወለደችው ህዳሴ፣ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በከተማዋ በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት መከታተሏን ታስረዳለች።

የዘንድሮው ውጤት ህዳሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበችው የትምህርት ስኬት አይደለም። የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለች 99.67 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ በስሟ ቤተ መጻሕፍት ተሰይሞላታል።

ከ28 ዓመታት በፊት የተመሠረተው አገው ምድር አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከፍተኛ ውጤት ባስመዘገቡ ተማሪዎች ስም ቤተ መጻሕፍት የመሰየም ልምድ አለው።

ህዳሴ ቤተ መጻሕፍት እንዲሰየምላት ያደረገው የ11ኛ ክፍል ውጤት በትምህርት ቤቱ ታሪክ የተመዘገበ ከፍተኛው ነጥብ መሆኑን ታስታውሳለች። ትምህርት ቤቷ በወቅቱ የሰጣት ይህ እውቅና ሙሉ በሙሉ ያልጠበቀችው እንደነበረም ትናገራለች።

የ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማምጣቷን ስትሰማም ያልጠበቀችውን ደስታ ከድንጋጤ ጋር እንዳስተናገደች ገልጻለች።

ህዳሴ በአዲስአበባ የሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምሕንድስናና በሒሳብ (STEM) መስኮች ላይ የሚሰጥ ሥልጠን አጠናቅቃ ወደ እንጅባራ ስትመለስ ጓደኞቿ ደውለው ያስመዘገበችውን ውጤት እንደነገሯት አስረድታለች።

"ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ ጠብቄአለሁ፤ ግን ደግሞ ከአገር አቀፍ ደረጃ እንደዚህ ከሴቶች አንደኛ የሚለውን ከፍተኛ ውጤት አልጠበቅኩም ነበር" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። የተሰማትን ስሜትም "በእንባ የታጀበ ነበር" ስትል ገልጻዋለች።

ህዳሴ እንደምታነገረው ይህን ውጤት ያስገኘላት የምትከተለው የጥናት ዘዴ ነው። በተለይም ባዮሎጂ እና ኬሚስትሪን የመሳሰሉ ትምህርቶችን ቪዲዮ በመመልከት መማር እንደሚቀላት ታስረዳለች።

በተጨማሪም በዓመቱ ውስጥ ማጠናቀቅ ያለባትን ትምህርት ወደ ሳምንታትና ቀናት በመከፋፈል እንደምትዘጋጅ ትገልጻለች።

ህዳሴ ይህንን ውጤት ያስመዘገበችው ሦስት ዓመት የደፈነው የአማራ ግጭት የክልሉን የትምህርት ስርዓት ጫና ውስጥ በከተተበት ሁኔታ ነው። በግጭቱ ምክንያት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ "በርካታ ትምህርት ቤቶች" ተዘግተው መቆየታቸውን የዞኑ አስተደዳር በዚህ ሳምንት አስታውቋል።

ይህ ሁኔታ ህዳሴን ነክቷል። በግጭቱ ምክንያት ትምህርቷን ሙሉ በሙሉ በትምህርት ቤት መከታተል አስቸጋሪ ሆኖባት እንደነበር ታስታውሳለች። በተለይም 10ኛ ክፍል እያለች ትምህርት ቤት የማትሄድባቸው ቀናት እንደነበሩ ትናገራለች።

"የሆነ የሆነ ቀን ትምህርት ቤቱ የሚዘጋበት ቀን አለ" ስትል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች። የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን በምትከታተልበት ወቅትም በአካባቢው "ስጋት" እንደነበር አንስታለች።

ህዳሴ 12ኛ ክፍልን በስሟ የተሰየመው ቤተ መጻሕፍት በሚገኝበት ትምህርት ቤት ብትማርም፣ ለማንበብ የምትመርጠው ግን ቤቷን እንደሆነ ትናገራለች።

"እውነቱን ለመናገር ያን ያህል ቤተ መጻሕፍት ተጠቃሚ አልነበርኩም። ምክንያቱም ቤተሰቦቼ በቤት ውስጥ ምቹ የሆነ ሁኔታን ፈጥረውልኛል" ትላለች።

ትምህርት ላይ ካደረገችው ጥረት ባሻገር ከቤተሰቧ ያገኘችው ድጋፍም ለውጤቷ መሠረት መሆኑን አባቷ ዶ/ር ዘመኑ ምህረት ይናገራሉ።

አባቷ ዶ/ር ዘመኑ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እና የፊዚክስ መምህር ናቸው። ከልጅነቷ ጀምሮ "ቁጥብ እና ከእድሜዋበላይ ስነ ስርዓት ያላት ልጅ ናት" ሲሉ ህዳሴን ይገልጿታል።

ሰዎችን በተለያዩ መንገዶች መርዳት እንደምትፈልግ እና ተሳትፎ እንደምታደርግ አባቷ ያስረዳሉ።

የህዳሴን ውጤት ሲሰሙ ውጤቷ አካባቢዋን፣ ትምህርት ቤቷን እና ያስተማሯትን መምህራን በሚያስጠራ ደረጃ መሆኑ "ደስታዬን እጥፍ አድርጎታል" ይላሉ።

በአቅሟ እና በፍላጎቷ ላይ የተመሠረተ ድጋፍ ሲያደርጉላት እንደነበር የሚገልጹት ዶክተር ዘመኑ፣ በቤት እና ከቤት ውጭ ለመማር ምቹ ሁኔታ እንዲኖራት እንደሚያደርጉ እንዲሁም ትምህርቷ ላይ ጫና ሳይኖርባት እንድትከታተል በማድረግ እንደሚያግዟት ያስረዳሉ።

ህዳሴ በቀጣይ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ወይም ኮምፒውተር ሳይንስ ቴክኖሎጂ ማጥናት እንደምትፈልግ ትናገራለች።

በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምሕንድስናና በሒሳብ ላይ የሚያተኩረው 'ስቴም' (STEM) መስኮችን በመፈተሽ ፍላጎቷን እና አቅሟን ማወቋን ትገልጻለች።

"በተከታታይ በወሰድኳቸው የተለያዩ የስቴም መስክ [ሥልጠናዎች] ላይ ራሴን በደንብ አይቼዋለሁ" ስትል ፍላጎቷን እንዴት እንደለየች ታስረዳለች።

ለቀጣይ ትምህርቷ ነፃ የትምህርት ዕድሎችን ለመፈለግም ዝግጅት መጀመሯን ትገልጻለች። ለማመልከቻዎቹ የሚያስፈልጓትን ሰነዶች እና የድጋፍ ደብዳቤዎችን እንዴት መጻፍ እንዳለባት እና ሌሎች መረጃዎችን ስትሰበስብ እንደቆየች ትናገራለች።

በትርፍ ጊዜዋም ፕሮግራሚንግ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና ዳታ ሳይንስ የመሳሰሉ ኮርሶችን ትማር እንደነበር አባቷ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም በ'ስቴም' ፕሮግራም ለተከታታይ ሁለት የክረምት ወቅቶች ሥልጠናዎችን በመውሰድ ያገኘችውን ልምድ መሠረት አድርጋ ቴክኖሎጂን ለማጥናት እንደወሰነች ይናገራሉ።

ዶ/ር ዘመኑ የህዳሴን ጥረትና ፍላጎት መሠረት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ የትምህርት ዕድል እንድታገኝ ድጋፍ እንዲደረግላት ጥሪ ያቀርባሉ። ይህም ለእሷ፣ ለአገሯ እና እንደእሷ ጥረት ለሚያደርጉ ተማሪዎች አርአያ እንደሚሆን ይገልጻሉ።

በ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ 564 ሺህ ገደማ ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ 550,210 ተማሪዎች ፈተናውን እንደወሰዱ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥ 12.8 በመቶ ወይም 70 ሺህ 544 ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ በማምጣት የማለፊያ ውጤት አስመዝግበዋል።

ይህ አሃዝ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው 8.9 በመቶ የማለፍ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ መሻሻል አሳይቷል። ዘንድሮ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥርም ከአምናው በ20 ሺህ በላይ ጨምሯል ብሏል።

በዘንድሮው ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ 16.58 በመቶ፣ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8.33 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት አስመዝግበዋል።

በዘንድው ፈተና ሙሉ በሙሉ ተማሪዎችን ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች ብዛት 88 ነው። በአንጻሩ 565 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም። ባለፈው ዓመት ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ብዛት 1,232 ነበር።