ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ያለው የኢቦላ ስርጭት "እጅግ አሳሳቢ" እንደሆነ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስጠነቀቀ
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የሚታየው ፈጣን የኢቦላ ቫይረስ መስፋፋት "እጅግ አሳሳቢ" ሁኔታ መፍጠሩን ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች ተቋም የሆነው ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) አስጠነቀቀ።
በአገሪቱ የኢቦላ ወረርሽን መቀስቀሱ ከታወጀ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጡት የቡድኑ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አላን ጎንዛሌዝ፤ ከዚህ ቀደም በእንዲህ አይነት ፍጥነት "እጅግ በርካታ ኬዝ" እንዳልተመዘገበ አስረድተዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ ይህንን ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱ እጅግ የተስፋፋበትን የኮንጎ ምሥራቃዊ ግዛት ኢቱሪን በጎበኙበት ወቅት ነው። ዶ/ር ቴድሮስ ወደ ኮንጎ የተጓዙት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለመከታተል ነው።
ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በቫይረሱ ቢያንስ 246 ሰዎች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን በሽታው እንደያዛቸው የተጠረጠሩ ሰዎች ብዛትም ከ1,000 በላይ ሆኗል። በአጎራባቿ አገር ዩጋንዳ ውስጥ ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው እንደተረጋገጠ እና አንድ ሰው እንደሞተ ተገልጿል።
የኤምኤስኤፍ ምክትል ዳይሬክተር ጎንዛሌዝ ቅዳሜ ዕለት ባውጡት መግለጫ፤ "ኢቱሪ ግዛት ውስጥ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወጀ ከሁለት ሳምንት በኋላ፤ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ሆኗል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
"ከዚህ ቀደም የኢቦላ ወረርሽ መከሰቱ በታወጀ በዚህ ፍጥነት እንደዚህ እጅግ በርካታ ኬዞች ተመዝግበው አያውቁም" ብለዋል። በስፍራው የሚገኙ የቡድኑ አባላት "ከወረርሽኙን ፈጣን ስርጭት ጋር ገና ያልተመጣጠነ የምላሽ አሰጣጥ ሂደት እየተመለከቱ" መሆኑንም አስረድተዋል።
"ዛሬ ላይ ባለው እውነታ፤ ማንም ሰው የዚህን ወረርሽኝ መጠን እና ምን ያህል የከፋ እንደሆነ አያውቅም። [ኢቦላ እንደሆኑ] የተጠረጠሩ አዲስ ኬዞች በየቀኑ እየተመዘገቡ ነው፤ እስካሁን ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎች ምርመራ አልተደረገባቸውም" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
እንደ ድንበር እና የአየር ማረፊያዎች መዘጋት ያሉ ተግዳሮቶች ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንቅስቃሴዎች ላይ መዘግየት እንዲኖር እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት፤ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የሚካሄደው ግጭት ለኢቦላ ወረርሽኝ የሚሰጠውን ምላሽ በከፍተኛ ደረጃ እያስተጓጎለ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል።
ቅዳሜ ዕለት ወደ ኢቱሪ ግዛት ዋና ከተማ ቡኒያ የደረሱት ዶ/ር ቴድሮስ፤ ከቡድናቸው ጋር በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተገኙት "የምላሽ አሰጣጡ እንዴት እየተካሄደ እንደሆነ ለመመልከት እና ተግዳሮቶች ካሉ ለማገዝ" መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ያሉ ማኅበረሰቦች "ችግሮቹን በተሻለ እንደሚረዱ፤ መፍትሄውንም እንደሚያውቁ" በመግለጽም በሽታውን ለመግታት ያላቸው ሚና ትልቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሰዎች የሞቱትን ለማክበር የሚያደርጉት የቀብር ስነ ስርዓት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንደሚረዱ የተናገሩት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ይህንን ማድረግ አደገኛ መሆኑን ገልጸዋል።
"በኢቦላ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን አስከሬን እንደመንካት ያሉ አንዳንድ ልማዶች ቫይረሱ ይበልጥ እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። ስላጣናቸው ሰዎች ሀዘናችንን እያወጣን፤ ሌላ ሰው እንዳናጣ እና የሀዘን አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን" ሲሉም አሳስበዋል።