ዩክሬን ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ የሆኑትን 'ፓትሪዮት' ሚሳዔሎች የማምረት ፈቃድ ልታገኝ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን 'ፓትሪዮት' የአየር መቃወሚያ ሚሳዔሎችን የማምረት መብት ሊሰጣት እንደሆነ ተናገሩ።

ሚሳዔሉ ዩክሬን የሩሲያን የባሊስቲክ ሚዔኤል ጥቃቶች ለመከላከል ሊረዳት ይችላል ተብሏል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በአንካራ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ " ዩክሬን ፓትሪዮት ሚሳዔሎችን እንድታመርት ፈቃድ እንሰጣታለን" ሲሉ ለዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ነግረዋቸዋል።

"እንዴት እንደሆነ ካስረዳናቸው በፍጥነት ማምረት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ" ብለዋል ትራምፕ።

ሆኖም ስለውሳኔያቸው ለመሣሪያ አምራቾቹ ሎክሂድ ማርቲን እና ራይቶን እስካሁን እንዳላሳወቋቸው ተናግረዋል።

ፓትሪዮት የሚሳዔሎችን ጥቃት ቀድሞ የመለየት እና የማክሸፍ አቅም ያለው ሲሆን በዓለም ካሉ ምርጥና እና እጅግ ውድ የአየር መቃወሚያ ሥርዓቶች አንዱ ነው።

አንዱ ባትሪ ከሚሳኤሎቹ ጋር ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያወጣል።

እንደ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት መረጃ ከሆነ ለማምረት ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሲሆን በዓመት መመረት የሚችሉት 600 ሚሳዔሎች ብቻ ናቸው።

ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው የስትራቴጂ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል እንዳለው አሜሪካ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከኢራን ጋር በነበራት ጦርነት ከክምችቷ ግማሽ ያህሉን ተጠቅማለች።

ትራምፕም " ፓትሪዮቶች አሉን፤ ግን ያን ያህል ብዙ አይደሉም። ለራሳችንም እንፈልጋለን" ብለዋል።

ዩክሬን ግን እነዚህን የጦር ሣሪያዎች በአስቸኳይ ትፈልጋቸዋለች።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ሞስኮ በዩክሬን ላይ የምትፈፅማቸውን የባሊስቲክ ሚሳዔል ጥቃቶች ጨምራለች።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተፈፀመ ጥቃት በኪየቭ ብቻ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

ዜሌንስኪ ዩክሬን ፓትሪዮት ለማምረት የሚያስችላትን ፈቃድ ለማግኘት በይፋ መጠየቋን የተናገሩት ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

አራት ዓመት ከግማሽ ከዘለቀው ጦርነት በኋላ በግንባር የሚደረጉ ውጊያዎች የቆሙ ሲሆን በጥቁር ባሕር ላይ የሚካሄደውም እንደተገታ ነው።

ሩሲያ በየምሽቱ የምትፈፅማቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የድሮን ጥቃቶችም እንዴት መመከት እንዳለባት ዩክሬን አውቃለች።

ሆኖም በፍጥነት የሚምዘገዘጉ እና ለማቆም አስቸጋሪ የሆኑ ባሊስቲክ ሚሳዔሎች ሩሲያ በዋናነት እየተጠቀመችባቸው ያሉ መሣሪያዎች እንደሆኑ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የዩክሬንን የአየር መቃዋሚያ ማለፍ ችለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩክሬን አየር ኃይል "ከፍተኛ የሆነ የመቃወሚያ ሚሳኤሎች እጥረት" መከሰቱን እና እሁድ ምሽት ሩሲያ ከተኮሰቻቸው 23 ባሊስቲክ ሚሳኤሎች አንዱም ተመትቶ አለመውደቁን አስረድቷል።

በዚህ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ትራምፕ አሜሪካ ፓትሪዮት ሚሳኤሎችን ማምረት የምትችልበትን ፈቃድ ለኪየቭ እንደምትሰጥ የገለጹ ሲሆን " ኪየቭ ከዚህ በኋላ በቂ መሣሪያ አልሰጡኝም የሚል ቅሬታ ማቅረብ እንደማትችል" ተናግረዋል።