ለአገሬው ተከልክለው ለቱሪስቶች ብቻ ክፍት የሆኑት የመዝናኛ ስፍራዎች

ባርቡዳ በካሪቢያን የምትገኝ ደሴት ስትሆን በጎብኚዎች ተመራጭ ናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባርቡዳ በካሪቢያን የምትገኝ ደሴት ስትሆን በጎብኚዎች ተመራጭ ናት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ፒንክ ሳንድስ በባሕር ዳርቻ የሚገኝ መዝናኛ ነው። ላለፉት 20 ዓመታት አገሬውንም ቱሪስቶችንም አስተናግዷል።

መዝናኛው በባርቡዳ ካሉ መዳረሻዎች አንዱ ነው። ባርቡዳ በካሪቢያን የምትገኝ ደሴት ስትሆን በጎብኚዎች ተመራጭ ናት።

የመዝናኛው የቀድሞ ባለቤት ሚራንዳ ባዘር "በጣም ምቹ ሥፍራ ነበር" ትላለች።

በመዝናኛው የተለያዩ ጨዋታዎችን የሚጫወቱ፣ እሑድ ከቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት በኋላ ወደ መዝናኛ ሥፍራው የሚሄዱም በርካቶች እንደነበሩ ታስታውሳለች።

መዝናኛው ስያሜውን ያገኘው በአካባቢው ካለው ሮዝ ቀለም ካለው አሸዋ ነው። ኢርማ የተባለው አውሎ ንፋስ እስከሚከሰት ድረስ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ገቢ ያስገኝም ነበር።

አውሎ ንፋሱ በአውሮፓውኑ 2017 ሲከሰት ነገሮች እንዳልነበሩ ሆኑ።

በአውሎ ንፋሱ ሳቢያ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የባርቡዳ ደሴት ነዋሪዎች ወደ አጎራባቿ አንቲጓ ተሰድደዋል።

የሚራንዳ መዝናኛ እና መኖሪያ ቤት በአውሎ ንፋሱ ወድሟል።

"ያልተጎዳ ሰው የለም። በጣም ያሳዝናል። ለሁለት ሳምንት አልቅሻለሁ" ትላለች።

መዝናኛውን ከመክፈቷ በፊት ባለቤቷን በሞት ተነጥቃለች። መዝናኛውን የገነባችበትን ቦታ ለመግዛት የውጭ አልሚዎች በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበውላታል። ሁሉንም ለመቀበል አልፈቀደችም።

"ገንዘቡን አልፈልገውም። መሬቴን ይዞ መኖር ይሻለኛል" ስትል ትገልጻለች።

አውሎ ንፋሱ ያስከተለውን ውድመት ተከትሎ ግን የውጭ አገር አልሚዎች ወደ ሥፍራው አምርተዋል። ከአውሎ ንፋሱ የተራረፈውን የመዝናኛውን ክፍል ማፍረሳቸውን ትናገራለች።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ መሬቷን ለማስመለስ በፍርድ ቤት እየታገች ትገኛለች።

በአንቲጓ እና ባርቡዳ የመሬት ሕግጋት ምክንያት የፍርድ ቤቱ ሒደት ውስብስብ ሆኗል።

የመዝናኛው የቀድሞ ባለቤት ሚራንዳ ባዘር

የፎቶው ባለመብት, Miranda Beazer

የምስሉ መግለጫ, የመዝናኛው የቀድሞ ባለቤት ሚራንዳ ባዘር

በባርቡዳ የመሬት ባለቤት መሆን የሚቻለው በሊዝ በመግዛት ነው። ዋነኛ የልማት መዳረሻ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ዜጎች የጋራ የመሬት ባለቤትነት መብት እንዳላቸውም ይገለጻል።

የመሬት ባለቤትነትን የሚመለከተው አሠራር የተዘረጋው ቅኝ ግዛትን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1834 ነው።

የአንቲጓ እና ባርቡዳ መንግሥት ለዚህ አሠራር ይፋዊ ዕውቅና የሰጠው በ2000 ነበር።

ሚራንዳ እንደምትለው በባሕር ዳርቻ 30 ካሬ መሬት በሊዝ ገዝታለች። አሁን ግን ተጠቃሚ መሆን የቻለችው በስምንት ካሬው ብቻ ነው።

ሚራንዳን የሚረዳት የጠበቃዎች ማኅበር 'ግሎባል ሌጋል አክሽን ኔትወርክ' እንደገለጸው የተቀረውን መሬት የውጭ አልሚዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተቆጣጥረዋል።

'ሙራቢ ሪዞርትስ ኤንስ ፒስ ላብ ኤንድ ሀፒነስ' የተባለ የውጭ አልሚ ኩባንያ መሬቱን በሕገ ወጥ መንገድ መያዙ ተገልጿል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫ በባርቡዳ ሕጋዊ የሊዝ ባለቤት መሆኑን ጠቅሶ "ሕጋዊ መብት በሌለው የመሬቱ ክፍል ላይ ማንኛውንም ዓይነት ግንባታ አላከናወነም" ብሏል።

ተዋናይ ሮበርት ዲኔሮ ከውጭ አገር አልሚዎች አንዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Mondadori Portfolio via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተዋናይ ሮበርት ዲ ኔሮ ከውጭ አገር አልሚዎች አንዱ ነው

በባርቡዳ መሬት በሊዝ የገዛው በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2017 ላይ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው፤ ለስምምነቶች ተገዢ ሆኖ እንደቆየ እና "መቼም ቢሆን ያለ ፈቃድ መሬት እንዳልተቆጣጠረ" አስታውቋል።

ሚራንዳ እና ሌሎችም የባርቡዳ የመብት ተሟጋቾች ይህንን ውድቅ አድርገዋል።

"መጥታችሁ ብታዩት ለምን ለዚህ ትንሽ አለታማ ሥፍራ እንደምንታገል ይገባችኋል" ትላለች።

የሚራንዳ መሬት በደሴቷ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ የሚገኝ እና ለሕዝብ ተደራሽ ሆኖ የዘለቀ ብቸኛው አካባቢ ነው።

በካሪቢያን ባሕር ዳርቻ እንደሚገኙ ሌሎች ሥፍራዎች ሁሉ ለአገሬው ነዋሪዎች ከለላ የሚሰጥ የመሬት ሕግ የለም። ስለዚህም ከሃብታም አልሚዎች ስጋት ተደቅኖባቸዋል።

የሃብታም አልሚዎች ግንባታ ትኩረቱን ያደረገው ቱሪስቶች ላይ ነው።

ዴቨን ቴይለር

የፎቶው ባለመብት, Devon Taylor

የምስሉ መግለጫ, ዴቨን ቴይለር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሚራንዳ መሬት አካባቢ ከሚገኙ የአልሚዎች ስብስብ በአንዱ ውስጥ ተዋናይ ሮበርት ዲ ኔሮ ይገኝበታል።

አውስትራሊያዊው ቢልየነር ጄምስ ፓርከር የሚገኝበት 'ፓራዳይዝ ፋውንድ' ሌላው ተቋም ነው።

400 ካሬ የሚሸፍነው ሪዞርት ባለንበት የአውሮፓውያኑ ዓመት ማገባደጃ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሪዞርቱ ውስጥ ቅንጡው ሆቴል ኖቡ ቢዝ ኢንን ጨምሮ 17 ቪላዎች እና 25 የባሕር ዳርቻ ቤቶች ይገኛሉ።

የአገሪቱ ነዋሪዎች እንደሚሉት ሪዞርቱ የሚገነባበትን አካባቢ መድረስ እንኳ አይችሉም።

በባሕር ዳርቻው ላይ ከ7 ሚሊዮን ዶላር አንስቶ መሬት መግዛት ይቻላል።

ሪዞርቱ በድረ ገጹ አካባቢውን የሚገልጸው "በካሪቢያን አካባቢ ማንም ባልነካው መሬት ላይ የሚገኝ ማኅበረሰብ መገኛ" በሚል ነው።

አካባቢውን የሚያስተዳድረው የባርቡዳ ምክር ቤት ኃላፊ ጆን ሙሲንግተን በበኩላቸው አካባቢው በዚህ መንገድ የተዋቀረው በ2007 የመሬት ድንጋጌ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።

በባሕር ዳርቻው ግንባታ የሚከናወነው ደግሞ መንግሥት በ2015 ባወጣው 'ፓራዳይዝ ፋውንድ' በተባለ ሕግ አማካኝነት ነው።

የመብት ተሟጋቾች ጉዳዩን በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የአንቲጓ እና ባርቡዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስደውታል።

ፍርድ ቤቱ በ2022 የደረሰበት ውሳኔ የአንቲጓ እና ባርቡዳን መንግሥት አሸናፊ አድርጓል።

"ሰዎች የባርቡዳ ዜጋ በመሆናቸው የሚገኘው መብት በቀጥታ የንብረት ባለቤትነትን አያረጋግጥም" የሚል ብይን ተላልፏል።

ፓራዳይዝ ፋውንድ በባሕር ዳርቻው የሚያለማው መሬት "ሕጉን መሠረት ያደረገ እንዲሁም ከአንቲጓ እና ባርቡዳ የተገኘውን ፈቃድ የተመረኮዘ" መሆኑን አስታውቋል።

ፕሪንሰስ ዳያና ቢች በመባል የሚታወቀው እና ለሕዝብ ተደራሽ የሆውነ የባሕር ዳርቻው ክፍል ላይ "አሁንም ድረስ ለውጥ አለመደረጉን" ገልጿል።

የመብት ተሟጋቾች ደሴቱን መልሰው ለማግኘት ይታገላሉ

የፎቶው ባለመብት, BLRRC

የምስሉ መግለጫ, የመብት ተሟጋቾች ደሴቱን መልሰው ለማግኘት ይታገላሉ

ባርቡዳ የቅኝ ግዛት ዘመን ሕግ የሚተገበርባት ብቸኛዋ የካሪቢያን አገር አይደለችም።

ከባሕር ዳርቻው በስተምሥራቅ ጃማይካ ውስጥ የሚገኝ 1,600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሥፍራ ለአገሬው ሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን ንቅናቄ ተጀምሯል።

የጃማይካ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ ፕሬዝዳንት ዴቨን ቴይለር እንደሚለው የአገሪቱ የመሬት አስተዳደር ሕግ በአጠቃላይ ሲታይ "ጃማይካውያንን ያገለለ" ነው።

"በባሕር ዳርቻው ላይ ምንም መብት እንደሌለን በግልጽ ያስቀምጣል" ሲል ዴቨን ይናገራል።

የጃማይካ መንግሥት በቅርቡ ያወጣው ረቂቅ ሕግ ለአገሬው ነዋሪዎች የባሕር ዳርቻ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ያስችላል።

ዴቨን እንደሚለው ከሆነ ግን የመሬት ባለቤትን በተመለከተ የሚወጣው ሕግ ሆቴሎች የባሕር ዳርቻ መግቢያን እንዲሸጡ በማበረታታት "ነዋሪዎች መሄድ የሚችሉበትን ቦታ የሚገድብ" ነው።

በአሁኑ ወቅት በሕዝቡ ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የመሬት ይዞታ አካሄድ "የቅኝ ግዛት አመክንዮን የተከተለ ነው" ሲል ያስረዳል።

ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ከጃማይካ መንግሥት ምላሽ ጠይቋል።

የመብት ተሟጋቹ እንደሚለው ከጃማይካ የባሕር ዳርቻ አንድ በመቶው ብቻ ለነዋሪዎች በነጻ ተደራሽ ነው።

በዚህም የተነሳ የጃማይካ መንግሥት እና የግል አልሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ሕጋዊ ሒደቶች ተጀምረዋል።

ቱሪስቶች አብዛኛውን የባሕር ዳርቻ ሲጠቀሙበት የአገሪቱ ነዋሪዎች በአንጻሩ እምብዛም ወደማይታወቁ መዳረሻዎች ሄደው ለመዝናናት ይገደዳሉ።

ግሪናዳ ላንድ አክተርስ የተባለው የመብት ተሟጋች ቡድን መሪ ክሪስ ዴቪስ እንደሚለው በግሪናዳ የግዙፍ ሪዞርቶች መስፋፋት የደሴቷን መልክ ሊያሳጣ ይችላል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ካሪቢያንን "በቱሪዝም ላይ ጥገኛ ከሆኑ" የዓለም ክፍሎች መካከል በግንባር ቀደምነት ያስቀምጣል።

የካሪቢያን መንግሥታት የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች ያደርጋሉ።

"ጉዞ ምጣኔ ሃብታዊ ብቻ ሳይሆን የሞራል ጉዳይም የያዘ ነው" ሲል ዴቨን ይናገራል።

የተለያዩ የመዝናኛ መዳረሻ ልማቶች ነዋሪዎች ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሱትን መሬት እያሳጡ እንደሆነም ያስረዳል።

በርካቶች አገራችን የሚሉትን ቦታ መልክ እየለወጠ መሆኑንም ያክላል።