"ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ. . . ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" ጠ/ሚ ዐቢይ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ. . . ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅናው የተሰረዘበት ህወሓት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ካስወገደ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ባለበት ጊዜ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ እና ምላሽ ማጠቃለያ ላይ "ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ፣ አእምሮ ከገዛ ለመነጋገር፣ ሰላም ለማምጣት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘውም "ከሰላም ውጪ ያለው ሁኔታ አይጠቅመንም" በማለትም ክለዋል።

በትግራይ ክልል ያለውን ውጥረት በተለያየ የንግግራቸው ክፍል ላይ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በትግራይ ክልል ጦርነቱ እንዲነሳ ሰፊ ፍላጎት አለ፤ እምቢ ያልንበት ምክንያት ትርፍ የለውም ብለን ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመሆን በጥምረት ጦርነት ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነው በሚል በፌደራል መንግሥቱ የሚከሰስ ሲሆን፣ ህወሓትም ተመሳሳይ ክስ በመንግሥት ላይ እያሰማ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም "እንኳን ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ሱዳን ሌላም ቢጨመር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለውም" ሲሉ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ያለው ሁኔታ ለአገሪቱ አስጊ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እና አፈሳ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች እና የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ አገራት የሰብአዊ መብት ተቋማት ገልጸዋል።

በትግራይ በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በህወሓት መሪዎች ከተወገደ በኋላ የሌላ ዙር ጦርነት ስጋት በክልሉ ተፈጥሯል።

ይህንን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በየቀኑ በርካታ ውጊያ፣ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች ትግራይ ውስጥ ባሉ ኃይሎች በየጊዜው ይፈጸማል" በማለት ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

ጨምረውም "በርካታ የትግራይ ልጆች በጉልበት ታፍሰው ሱዳን ላለው ጦርነት ተሸጠዋል" በማለት በጎረቤት አገር ላለው ጦርነት ከትግራይ ወጣቶች እየተወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በሱዳን ጦርነት ውስጥ የትግራይ ወጣቶች በማያውቁት ጉዳይ ሕይወታቸውን እያጡ ነው" ብለዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከመምጣቱ ባሻገር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸውም ሪፖርቶች ወጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም "በዚህ ሁሉ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ የችግሩ ባለቤት ሳይሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ተጎጂ ነው" በማለት በክልሉ ውስጥ ለሕዝቡ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን በማንሳት የትግራይ ተወላጆች ከክልሉ ይቅል በሌሎች የኢትዮጵያ ከፍሎች ውስጥ በሰላም ወጥተው የመግባት ዕድል እንዳላቸው ተናግረዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በተናጠል ባወጡት መግለጫ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው መግለጻቸው አይዘነጋም።

የፌደራል መንግሥቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ውጥረት በተመለከተ ይፋዊ አቋሙን ባያንጸባርቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅናውን የነሳው ህወሓት በፊደራል መንግሥቱ የተሾመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማስወገድ ከጦርነቱ በፊት በነበረው ምርጫ ያሸነፈውን ምክር ቤት ከመለሰ ወራት አልፈዋል።

ህወሓት ወደ ሥራ የመለሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን እና በሞት የሚያስቀጡ ድንጋጌዎችን የያዘውን አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ ማስተላለፉም አይዘነጋም።

ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና የፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ ባለው ምርጫ የተቋቋመው የክልሉ ምክር ቤት "የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ" በሚል የወጣውን አዋጅ ያጸደቀው ባለፈው ግንቦት ላይ ነበር።

የክልሉ ምክር ቤት ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው ይህ አዋጅ ከክልሉ ፖለቲከኞች እና ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ተቃውሞ እና ውግዘት ደርሶበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓትን በመተቸት፤ 50 ዓመት የቆየ "አንጋፋ ፓርቲ ሆኖ ወጣቱን ማመን" አመቻሉን በንግግራቸው ጠቅሰው "ድል እና ህወሓት አራንባ እና ቆቦ" ናቸው ሲሉም አጣጥለዋል።

የደርግ መንግሥት በወደቀበት "ስሌት" መንግሥታቸውን ለመጣል የሚያስቡ ኃይሎች ስጋት እንደማያሳድሩ ገልጸውም፤ አሰላለፋቸውን "ምኞት" ብለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ኃይሎች "መከላከል የሚያስችል ብቃት እየገነባን ነው ያለነው" ብለዋል።

"ባረጀ ባፈጀ ስልት፤ ድሮ በሠራ ስልት አሁን ለመጠቀም መሞከር ጠቃሚ አይደለም" ያሉት ዐቢይ፤ ለዚህም የሰጡት ምክንያት ራሱን በድሎ የሚዋጋ ኃይል የለም የሚል ነው።

"ጊዜው ተቀይሯል" ሲሉም ተናግረዋል።

"ሃብት እያፈራህ፤ ሃብትን እያጣጣምክ ራስን ደግሞ ለመስዋዕትነት ማዘጋጀት አብሮ አይሄድም። አልፎበታል። ይህ ምኞት አይጠቅምም" ብለዋል።

አሁን ያለውን የአዲስ ትውልድ አስተሳሰብ እና አቅጣጫ አለመቀበል "የትም አያደርስም" ሲሉም አክለዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ "አሸናፊ እና ተሸናፊ እኩል ቁጭ ብለው የተደራደሩበት ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አያይዘውም የትግራይ ሕዝብ በክልሉ ካለው አንጻር "በደሴ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር. . ." በሰላም ወጥቶ መግባት ይችላል ብለዋል።

ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ አርባ ምንጭ. . . እና ሌሎችም ከተሞችን በመጥቀስ "ኮሪደር ልማት በመቀለ ማየት ነው ምኞታችን ከዛ ውጭ ያለውን አንፈልግም" ብለዋል።

ይሄንኑ ንጽጽር ለአማራ ክልል እና ለኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ተጠቅመው "ዜጎች በገዛ ቀዬአቸው እየታመሱ ነው" ብለዋል።

"ከቀዬ ሸሽቶ መኖር የተሻለ ሰላም የሚሰጥ" ሆኗል ሲሉ አክለዋል።

የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ቀውስ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን "የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ" ሲሉ ገልጸውታል።

"ትግራዋይ እና ኢትዮጵያዊ የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ ሆኗል" ሲሉ የሚስተዋለውን አለመረጋጋት አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት "የሻዕቢያን" ተልዕኮ እያስፈጸመ ያለ፤ 'የራሱ ዓላማ የሌለው' "መጥረቢያ" ነው ሲሉ ከስሰዋል።

"ኢትዮጵያ የሰላሟ መድፍረስ ምንጭ የት እንደሆነ ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳው ማንኛውንም ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና በመፍጠር ላይ የምንገኝ መሆኑን ለተከበረው ምክር ቤት መግለፅ እፈልጋለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስሩ ስለ ሰላም እጦት ሲያነሱ ችግሩ የትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እንደሚስተዋልም ተናግረዋል።

"ልታገልልህ" የሚሉ ኃይሎች ባሉባቸው ቦታዎች ነዋሪው "የበለጠ ፍራቻ፣ የበለጠ ግድያ፣ የበለጠ ዘረፋ እና መታገዶች አሉ" በማለት የክልሎቹ ነዋሪዎች ከራሳቸው ክልል ይልቅ በሌሎች ክልሎች ሰላም እና ደኅንነት አላቸው ብለዋል።

እነዚህን የሕዝቡን ደኅንነት ስጋት ላይ ጥለዋል ያሏቸውን ክስተቶች መንግሥታቸው በትዕግስት የሚያየው እና ወደ ግጭት ያልገባው "ግጭቱ ዓላማ ቢስ በመሆኑ" እንደሆነ ጠቁመዋል።

"ይህንን ግጭት ከፈጸምን በኋላ አሳካን ብለን የምንናገረው አንዳች ቁም ነገር የለም፤ በዚህም በዚያም ብንገድልም ብንሞትም ትርጉም የለውም" በማለት መንግሥት ቁጥብ የሆነበትን ምክንያት አስረድተዋል።