በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊትን ለማስወገድ አዲሱ ስኬታማ ግኝት

የፎቶው ባለመብት, Maria Patzwald
"ይህ ሕክምና ባይኖር ኖሮ ልጄ ካለ ጊዜው ይወለድ ነበር ብዬ አስባለሁ፤ እናም በሕይወት መቆየት በጣም ይከብደው ነበር" ትላለች ማሪያ ፓትዝዋልድ።
የ38 ዓመቷ ሴት ሁለተኛ ልጇን ባረገዘችበት ወቅት መጀመሪያ ላይ ምንም ስጋት አልነበራትም። "ችግሮች እስኪከሰቱ ድረስ ሁሉ ነገር ሰላም ነበር" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከዚያም ማሪያ የ32 ሳምንት ነፍሰጡር እያለች፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት (ፕሪ-ኤክላምፕሺያ) እንደገጠማት እና እስክትወልድ ድረስ በሆስፒታል መቆየት እንዳለባት ተነገራት።
ልጇን በሰላም እስክትወልድ ድረስ ተመራማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የችግሩን ዋና መንስኤ ለማከም ይቻል ይሆናል ብለው ተስፋ ያደረጉት ምርምር ላይ እንድትሳተፍ ከ16 ሴቶች ጋር መረጧት።
ፕሪ-ኤክላምፕሺያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ70 ሺህ በላይ እናቶች እና 500 ሺህ ሕፃናት እንዲሁም ከሌሎች የደም ግፊት ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ሞቶች ምክንያት ነው።
በሽታው በስፋት የሚከሰት ቢሆንም ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሕክምናው ለውጥ ሳያሳይ ባለበት ቆይቷል። ዶክተሮች ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ለመቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ብቸኛው አማራጭ ልጁ ካለጊዜው እንዲወለድ ማድረግ ብቻ ነው።
በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራ የአሜሪካ ተመራማሪዎች ችግሩን ሊያስከት ይችላል ብለው ባመኑት ፕሮቲን ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል። ይህንንም ከእናቲቱ ደም ውስጥ በማስወገድ ጤናዋን ሊያሻሽል እና እርግዝናዋን ጤናማ አድርጎ ያስቀጥል እንደሆነ ለማየት ነው።
ይህም በአማካኝ በእርግዝና ወቅት ከባድ የደም ግፊት ያለባቸው 16 ሴቶች እርግዝናቸውን በ10 ቀናት ውስጥ መራዘም መቻሉን አረጋግጠዋል። ይህ ውጤታቸውም በኔቸር ሜዲስን ጆርናል ላይ ታትሟል።
ለማሪያ ይህ ማለት ልጇ ቤኔት በ34 ሳምንቱ እንዲወለድ በማድረጉ ያለጊዜያቸው የተወለዱ ሕፃናት በሕይወት የመትረፍ ዕድላቸውን የበለጠ የሚያሰፋ ትልቅ ዕድል ነው።
ደምን የማጣራት ሕክምና
ተመራማሪዎች በትክክል ባያውቁም፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ የደም ግፊት የሚከሰተው የእንግዴ ልጅ ባልተለመደ ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ይህም የደም ፍሰትን የሚቀይር እና የእናትየዋን መደበኛ የደም ግፊት ያዛባል።
ከፍተኛ የደም ግፊት ወደ ስትሮክ እና የአካል ክፍሎች ጉዳት ሊያመራ ይችላል።
ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ከ20 ሳምንታት እርግዝና በኋላ ወይም ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ወዲያውኑ ሲሆን፣ ይህም በመደበኛ የቅድመ ወሊድ የደም ግፊት ምርመራዎች እና የሽንት ምርመራዎች ሊታወቅ ይችላል።
ሌሎች ምልክቶች ደግሞ በቀላል የሕመም ማስታገሻዎች የማይጠፋ ከባድ የራስ ምታት፣ የዕይታ ችግር፣ ከጎድን አጥንቶች በታች ሕመም፣ የፊት፣ የእጅ ወይም የእግር ድንገተኛ እብጠት፣ በመድኃኒቶች የማይጠፋ ማቃር እና ማስመለስ ናቸው።
ይህ ሙከራ የሚካሄደው በአሜሪካ የሲዳርስ-ሲናይ የሕክምና ማዕከል ቡድን ሲሆን፣ በፕሮፌሰር ራቪ ታዳኒ እና ፕሮፌሰር አናንት ካሩማንቺም ይመራል።

ምርምሩ ከሴቶቹ ደም መውሰድ፣ በሽታውን እንደሚያመጣ የሚታመነውን ኤስኤፍኤልቲ-1 (sFlt-1) የተባለ ፕሮቲን ማጣራት እና ከኩላሊት ዳያሊሲስ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሂደት ወደ ሰውነት መመለስን ያካትታል።
ምርመራ የተደረገላቸው እናቶችን ከሚጥል በሽታ ለመከላከል እና የደም ግፊታቸውን ለመቆጣጠር መድኃኒት ሊሰጣቸው ቢችልም ሊድኑ የሚችሉት ልጁ ሲወለድ ብቻ ነው። ነገር ግን ያለጊዜው የሚወለድ ሕፃን ለአደጋ ይጋለጣል።
እንደ ማሪያ ከጀርመን የመጣች እናት በሙከራው ውስጥ በርካታ ጊዜዎችን አሳልፋለች።
ሕክምናው ለልጇ ወሳኝ የሆነ በማህፀን ውስጥ ተጨማሪ የሁለት ሳምንታት የዕድገት ጊዜን አስገኝቶለታል።
"አንድ ሕፃን በ34ኛው ሳምንት ወይም ከዚያ በኋላ ቢወለድ፣ ምንም ዓይነት የጤና ችግር ወይም ዘላቂ እክል የመከሰት ዕድሉ በጣም ያነሰ ነው" ትላለች። አክላም "በጣም ትልቅ እፎይታ ነበር" ብላለች።
የጥናቱ መሪ ሕክምናው እርግዝናን የበለጠ ለማራዘም የሚያስችል አቅም እንዳለው ያምናሉ።
ታዳኒ "ግቡ በጣም ቀደም ብሎ መጀመር እና ተጨማሪ ሕክምናዎችን ማድረግ ነው…ቀደም ብለን ከጀመርን እርግዝናን ለብዙ ሳምንታት ማራዘም እንችላለን" በማለት ተናግረዋል።
'የማይታወቀው ትልቁ ነገር'
"ይህ በጣም አስደሳች የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ነው" ይላሉ በለንደን በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሆስፒታል የጽንስና የማህፀን ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር አስማ ካሊል። በተለይም የበሽታውን ሥነ ሕይወታዊ መንስዔ ላይ ያነጣጠረው ሕክምና "በተለይ ተስፋ ሰጪ" እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።
"በቅድመ ወሊድ ወቅት ከባድ የደም መፍሰሰስ ችግር ላለባቸው ሴቶች፣ ለጥቂት ተጨማሪ ቀናት ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማሳለፋቸው ለሕፃኑ በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ያብራራሉ።
ነገር ግን በጣም ብዙ ሙከራዎች እንደሚያስፈልጉ ጨምረው ገልጸዋል።
የደም ማጣራት ቴራፒው ለእናቶችና ለሕፃናት ደኅንነቱ የተጠበቀ ቢሆንም አሁንም "ብዙም የማይታወቅ" ጉዳይ መኖሩን ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።
ምክንያቱም ሙከራው በጣም በውስን እናቶች ላይ የተደረገ ነበር ያሉት በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የእናቶችና የፅንስ ጤና ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሪው ሼነን ናቸው።
በእርግዝና ወቅት በሚከሰት የደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ አብዛኛዎቹ ሴቶች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው እና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት በሌላቸው አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ ተናግረዋል። እነዚህ ሴቶች "ቴክኒካዊ" በሆነ የደም ማጣራት ሕክምናን የመጠቀም ዕድላቸው አነስተኛ ቢሆንም ብዙዎቹ ቀደም ሲል በነበሩ ሕክምናዎች ሊድኑ እንደሚችሉ አክለዋል።
"ነገ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን በተሻለ ሁኔታ ብናከናውን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ በእጃችን አለ" ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ታዳኒ ደምን ለማጣራት የሚያስፈልጉት መሳሪያዎች ከኩላሊት እጥበት ማከናወኛ ማሽኖች ጋር በጣም ተመሳሳይ ናቸው በማለት ይከራከራሉ።
አነስተኛ አቅም ያላቸው ክሊኒኮች እነዚህን ማሽኖች በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊትን (pre-eclampsia) ለማከም እንደገና ማደራጀት እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Maria Patzwald
'የምኮራበት አንድ ነገር'
ታዳኒ እንደሚሉት በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሕክምናው ላይ ሰፊ ጥናት እንደሚጀመር እና በሚቀጥሉት ሦስት ወይም አምስት ዓመታት ውስጥ በመደበኛ ክሊኒኮች ውስጥ ሊሰጥ እንደሚችል ተስፋ አላቸው።
"ዛሬ ለመሳተፍ የተስማሙት ጀግና ሴቶች ባይኖሩ ኖሮ እዚህ ባልሆንን ነበር... በእርግጥ በዚህ ታሪክ ውስጥ ጀግኖች ናቸው፣ ምንም ጥርጥር የለውም" ሲል አክለዋል።
ማሪያ የተሳተፈችበት አነስተኛ ጥናት እናቶችንና ሕፃናትን ሊረዳ ይችላል ብላ ማሰብ "ትንሽ የሚያስደነግጥ" እንደሆነ ተናግራለች፤ ዕድሉ ስለተሰጣትም ታመሰግናለች።
"ከጥቂት ቀናት በፊት ስለ ጉዳዩ ከአንድ የእናቶች ቡድን ጋር እያወራሁ ነበር፤ እናም ለመሳተፍ ድፍረት ስለነበረኝ እና የሕፃናትን እና የእናቶችን የመትረፍ ዕድል ለመጨመር ስላደረግኩት ድጋፍ አመስግነውኛል" ትላለች።
"ከዚያም እኔም የምኮራበት ነገር ሊሆን እንደሚችል ተገነዘብኩ።"















