በሳዑዲ መዲና በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች ሲገደሉ 309 ሰዎች ተጎዱ

ንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት አቋርጧል
የምስሉ መግለጫ, ንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት አቋርጧል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሳዑዲ አረቢያ መዲና ሪያድ በሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች እንደተገደሉ እና 309 ሰዎች እንደተጎዱ ተገለፀ።

የአገሪቱ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት እንዳሉት የተገደሉት ሰዎች አራት የሳዑዲ ዜጎች፣ ሁለት የባንግላዲሽ ዜጎች፣ አሜሪካዊ፣ ዮርዳኖሳዊ፣ ፍልስጤማዊ፣ ሶሪያዊ፣ ሱዳናዊ እና ግብፃዊ ናቸው።

ንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት አቋርጧል።

በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ጥቃቱ የተፈጸመው በሁቲ አማጺያን መሆኑን ገልጿል። ጥቃቱን "የጦር ወንጀል" ያለው ሲሆን የአጸፋ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቋል።

ትናንት ቅዳሜ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች እስካሁን ድረስ አስተያየት አልሰጡም።

ባለፈው ሐሙስ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ግን ኃላፊነቱን ወስደዋል። በዚህ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ አንድ አውሮፕላን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 6 እና 7 በሁለት አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ሌሎች ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

ቅዳሜ የደረሰው ጥቃት ከግንቦት 2015 ወዲህ በሳዑዲ ላይ የደረሰ የከፋው ጥቃት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሳዑዲ በሚደገፈው የየመን መንግሥት እና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማጺያን መካከል ውጊያው ተባብሶ ቀጥሏል።

ቅዳሜ በሪያድ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰው ጥቃት በተጨማሪ በምሥራቃዊ ሳዑዲ ዳማም በሚገኘው በንጉሥ ፋሀድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመሣሪያ ስብርባዎች መውደቃቸው ተገልጿል።

የሳዑዲ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባወጣው መግለጫ ከተጎዱት ሰዎች የተወሰኑት "በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ብሏል።

በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑ ተገልጿል።

አንድ የዐይን እማኝ እንደተናገሩት፤ መግቢያ በር 401 አካባቢ በደረሰ ጉዳት የተጎዱ ሰዎች ተመለክተዋል። "ሁሉም ሰው እየሮጠ ነበር" ብለዋል።

በርካታ አምቡላንሶች ወደ አውሮፕላን ማረፊያው መጓዛቸውን የዐይን እማኝ ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት ቃል አቀባይ ሜጀር ጄነራል ቱርኪ አል-ማሊኪ እንደገለፁት፤ በደረሰው ጥቃት ከተጎዱ ሰዎች መካከል ተጓዦች እና የአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኞች ይገኙበታል።

"መጠነ ሰፊ የጦር ወንጀል" ሲሉም ጥቃቱን አውግዘዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጥቃቱን ኮንነዋል።

አሜሪካ ሁቲዎች ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ሳዑዲን ትደግፍ እንደሆነ ከጋዜጠኞች ተጠይቀው "ልናደርገው እንችላለን። እናስብብበታለን፤ ስለ ጥቃቱ የሰማነው አሁን ነው፤ ውሳኔ ግን እንሰጣለን" ሲሉ መልሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጥቃቱ "ክፉኛ መደንገጣቸውን" ገልፀዋል።

የደረሰው ጥቃት "ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር" የተናገሩት ዋና ጸሐፊው "በአፋጣኝ እንዲቆም" ሲሉም አሳስበዋል።

ግብፅ፣ ፍልስጤም እና ኳታርም ጥቃቱን አውግዘዋል።

ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸው ከሪያድ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲርቁ አሳስበዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 6 እና 7 በሁለት አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ሌሎች ሦስት ሰዎች ተገድለዋል
የምስሉ መግለጫ, በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 6 እና 7 በሁለት አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ሌሎች ሦስት ሰዎች ተገድለዋል

በርካታ የባሕረ ሰላጤው አገራት ወደ ሪያድ እና ከሪያድ የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዛቸውን የፍላይትራዳር መረጃ ይጠቁማል።

ሁቲዎች ሳዑዲን ዒላማ ያደረጉት ለየመን መንግሥት ድጋፍ በመስጠቷ መሆኑን ተናግረዋል።

አማጺያኑ በቀይ ባሕር ያለውን ወሳኝ መተላለፊያ በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ ውጊያው ተጠናክሯል።

ሁቲዎች ዋነኛ ዓለም አቀፍ መተላለፊያ የሆነውን የባብ ኤል-ማንዳብ ሞክሀ ወደብን በቁጥጥር ሥር አውለው ነበር።

ከዚያም የየመን መንግሥት ደጋፊ የሆኑ ኃይሎች አካባቢውን መቆጣጠር መቻላቸውን ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።

በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር።

አብዛኛው የአረብ አገራት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የየመን መንግሥት በሁቲ አማጺያን እንዳይሸነፍ ድጋፍ ይሰጣሉ።

ለዓመታት ከዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በ2022 ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ነበር።

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በውጊያው የሞቱ ሲሆን ዓለም አቀፍ ቀውስም አስከትሏል።