ሞሳድ ወደ ኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስልክ በመደወል የሚያቀርበው እንግዳ ጥያቄ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በቅርብ ጊዜ ውስጥ በእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ እና በኢራን ባለሥልጣናት መካከል "ቀጥተኛ ግንኙነት ተደርጓል" የሚሉ ሪፖርቶች በቴህራን መገናኛ ብዙኃን እየተሰሙ ነው።

ከፍተኛ የኢራን የስለላ፣ የደኅንነት እና የፖለቲካ ባለሥልጣናት ሞሳድ በቴህራን ላይ ያለው ጫና ምን ያህል የሰፋ ነው የሚለው እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ይገኛሉ።

ኢራን እና እስራኤል ለ12 ቀናት ጦርነት ካደረጉ በኋላ በቴህራን የደኅንነት መዋቅር ውስጥ "ክፍተት አለ" የሚለው ሕዝቡን እያነጋገረ ነው።

"የደኅንነት ክፍተት" በኢራን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎች ዘንድ ያሉ መረጃዎች ሾልከው እየወጡ መሆኑን ይጠቁማል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ይሄንን ቃል የሚጠቀሙት የአሜሪካ እና እስራኤልን ደኅንነት ለመግለጽ ነው።

ከ12 ቀናት ጦርነት በኋላ ሞሳድ በኢራን ደኅንነት መዋቅር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ አዲስ ዕይታ ተፈጥሯል።

የኢራን የፖለቲካ እና የደኅንነት ባለሥልጣናት "የሞሳድ ወኪሎች" እንደደወሉላቸው እና እንዳስፈራሩዋቸው ይፋ አድርገዋል።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት እነዚህ የስልክ ጥሪዎች ዓላማቸው ባለሥልጣናትን "ማዋረድ"፣ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡን ሥልጣን መገዳደር እና "የበላይነትን ማሳየት" ነው።

የደዋዩቹ ማንነት በገለልተኛ ወገን አልተጣራም። ሁሉም የሞሳድ ወኪሎች ስለመሆናቸው ወይም ከሞሳድ ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለመሆኑም አልተረጋገጠም።

የኢራን የነዳጅ ሚኒስትር ጃቫድ ኦጂ በአውሮፓውያኑ ጥር 2024 ላይ የሞሳድ ባልደረባ እንደደወለላቸው ነሐሴ 2026 ላይ ገልጸዋል።

ወቅቱ በኢራን የነዳጅ ማስተላለፊያ ላይ ፍንዳታ የደረሰበት ነበር።

ደዋዩ ግለሰብ "የተለያዩ ስልቶች" መጠቀሙን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ሦስት ዋነኛ የኢራን የነዳጅ ማስተላለፊያዎች በሰከንዶች ልዩነት ፈንድተዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት የደወለላቸው ግለሰብ "3 + 5 ስንት ነው? 4 + 5 ስንት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቋል። ከዚያም መልሱን ከሰማ በኋላ ስለ ነዳጅ ማስተላለፊያዎቹ ፍንዳታዎች ገልጿል።

ከደቂቃዎች በኋላ ፍንዳታዎቹ መከሰታቸው ተረጋግጧል።

ሚኒስትሩ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቁጥጥር ማዕከል ሲደርሱ ፍንዳታውን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ከፍንዳታው በኋላ የነዳጅ አቅርቦት ያልተቋረጠው "የበላይነትን" ለማሳየት መሆኑን አክለዋል።

በወቅቱ ሦስቱ ፍንዳታዎች የተከሰቱት "በአሸባሪዎች" ነው ቢሉም እስራኤልን በስም አልጠቀሱም።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን የሚኒስትሩን ንግግር "እንግዳ" ብለውታል።

'ዘ ታባንክ' የተባለው ድረ ገጽ ባወጣው ጽሑፍ "ከታሪኩ ይዘት በላይ ትርክቱ የበለጠ አሳሳቢ ነው። የግለሰቡን ሥልጣን ሳይሆን የጠላትን የኃይል የበላይነት የሚያሳይም ነው" ሲል ተችቷል።

ድረ ገጹ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅትባ ኻሜኒ ወታደራዊ አማካሪ ለሆኑት ሞህሴን ራይዚ ቅርበት እንዳለው ይነገራል።

የሚኒስትሩን ንግግር በማጣጣል "ሁሉም ነገር ለመገናኛ ብዙኃን የመብቃት ዋጋ የለውም" ሲልም ድረ ገጹ አስነብቧል።

የሚኒስትሩ ትርክት "የጠላትን የሥነ ልቦና ዘመቻ እና ተነሳሽነት" የሚያሳይ እንደሆነ ገልጾ "አለማውራት ይሻላል" ብሏል።

ከ12 ቀናት ጦርነት በኋላ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ያለውን አቅም ለሕዝቡ ለማሳየት በመገናኛ ብዙኃን መረጃ ያወጣል።

ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ ወግ አጥባቂ መገናኛ ብዙኃን የሚኒስትሩ ንግግር ከቀድሞው የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ ንግግር ጋር የተለያየ መሆኑን ዘግበዋል።

አሊ ላሪጃኒ ባደረጉት ንግግር "ኢራን ያላትን የኃይል የበላይነት" ሲጠቁሙ የጃቫድ ኦጂ ትርክት ግን "ባልተሰበ ሁኔታ የጠላትን አቅም" የሚያሳይ ነው ተብሏል።

የቀድሞው የነዳጅ ሚኒስትር ያደረጉት ሞሳድን የሚጠቅስ ንግግር የመጀመሪያው አይደለም። ሞሳድ የተጠቀሰው በ12 ቀናቱ ጦርነት ወቅት ብቻ እንዳልሆነም ተገልጿል።

ሚኒስትሩ ከዚያ ቀደም ቢያንስ አንድ ጊዜ ሞሳድን በይፋ ጠቅሰዋል።

ሞሳድ ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች

ዋሽንግተን ፖስት በአውሮፓውያኑ ሰኔ 23/2025 ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ፍንዳታው በተከሰተ በሰዓታት ውስጥ የእስራኤል የደኅንነት ባልደረቦች ኢራናውያን ባለሥልጣናትን ለማስፈራራት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

ለኢራን ባለሥልጣናት በመደወል አገዛዙን የማይቃወሙ ከሆነ እንደሚገደሉ በመግለጽ ሲያስፈራሩ ነበር።

እነዚህ የስልክ ጥሪዎች የኢራንን መንግሥት ለመከፋፈል እና አለመረጋጋት ለመፍጠር ያለሙ መሆናቸውን የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ይጠቁማል።

ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ሥር በተለያየ እርከን ያሉ አመራሮችን ማስፈራራት እንዲሁም የተገደሉ አመራሮችን ለመተካት ከባድ እንዲሆን ማድረግም ተጠቅሰዋል።

ዋሽንግተን ፖስት የጠቀሳቸው አንድ ምንጭ 20 የኢራን ባለሥልጣናት ጋር ስልክ መደወሉን ተናግረዋል።

ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ ውስጥ በተካተተ የድምጽ ቅጂ የእስራኤል የደኅንነት ባልደረባ ከኢራን ባለሥልጣን ጋር ሲነጋገር ይሰማል።

ተቀንጭቦ የቀረበው ድምጽ "ከሚስትህ እና ከልጆችህ ጋር ለማምለጥ 12 ሰዓት አለህ። ካልሆነ ዒላማ ትደረጋለህ" ይላል።

የኢራናዊው ባለሥልጣን ማንነት አልተጠቀሰም። እስራኤላዊው የደኅንነት ባልደረባ ማንነት እንዳይታወቅም ድምጹ ተለውጧል።

ይህ የስልክ ጥሪ የኢራን ወታደራዊ እና ደኅንነት ባለሥልጣናትን ለማስፈራራት እና የሥነ ልቦና ጫና ለማሳደር ያለመ እንደሆነ ዘገባው ያሳያል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ አሊ ላሪጃኒ የዋሽንግተን ፖስትን ዘገባ ትክክለኛነት በማረጋገጥ እሳቸውም በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን የማስፈራሪያ የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው ይፋ አድርገዋል።

እስራኤል በስልክ ጥሪዎቹ አማካኝነት የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ያለውን ድጋፍ ለመቀነስ መሞከሯን ተናግረዋል።

የስልክ ጥሪው የደረሳቸው ወታደራዊ አዛዦች ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲከኞች እና የደኅንነት አመራሮች ጭምር መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አንድ የሞሳድ ባልደረባ ደውሎ ከኢራን ለመውጣት ያላቸው 12 ሰዓታት ብቻ እንደሆነ ጠቅሶ፤ ከቴህራን ርቀው የማይሄዱ ከሆነ ግን "የጓደኞቻቸው ዕጣ ፈንታ እንደሚጠብቃቸው" መግለጹን አክለዋል።

እሳቸውም ለደዋዩ "ለኔታንያሁ የሚመጥን" መልስ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

የስልክ ጥሪ ከደረሳቸው አመራሮች መካከል የደዋዩን ፍላጎት ያሟሉ እንደሌሉ ገልጸዋል።

እነዚህ የስልክ ጥሪዎች የኢራን ባለሥልጣናትን ለማስፈራራት ያለሙ ናቸው ብለዋል።

አመራሩ ለ40 ቀናት በቆየው ጦርነት ወቅት በአውሮፓውያኑ የካቲት 16/2026 በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

ከሞሳድ ተደርገዋል የተባሉት የስልክ ጥሪዎች ከኢራን ለመውጣት ወይም ከአገዛዙ ለመራቅ ለባለሥልጣናቱ 12 ሰዓት መስጠታቸው ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል።

"ከ20 እስከ ሁለት ሺህ" የሚደርሱ ምስክርነቶች ሞሳድን በስም ጠቅሰዋል።

በ12 ቀናት ጦርነት ወቅት የኢራን መንግሥት ደጋፊ መገናኛ ብዙኃን ባወጧቸው ዘገባዎች ሞሳድ ለኢራን ባለሥልጣናት ያደረጋቸውን የስልክ ጥሪዎች ጠቅሰዋል።

ዋሽንግተን ፖስት 20 ባለሥልጣናት ከሞሳድ የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው ጠቁሟል።

'አግህ' የተባለው ወግ አጥባቂ መገናኛ ብዙኃን እንዳለው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 1/2026 ባወጣው ዘገባ እንደጠቀሰው ከሁለት ሺህ በላይ ባለሥልጣናት ከሞሳድ ጥሪ እንደደረሳቸው "አስተማማኝ ማስረጃ" አግኝቷል።

ወታደራዊ አዛዦች፣ የደኅንነት ባልደረቦች እና የአገዛዙ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይገኙበታል።

የስልክ ጥሪ፣ ምሥጢራዊ መልዕክት እና ጦርነቱ በተጀመረበት ቀን ኢሜይሎች ደርሰዋቸዋል።

የስልክ ጥሪዎቹ ዓላማ ማስፈራራት ብቻ ሳይሆን አገዛዙ አብቅቶለታል በሚል ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው እንዲለቅቁ ወይም ከቴህራን እንዲወጡ ማድረግ ነው።

ዋሽንግተን ፖስት የጠቀሳቸው ምንጭ "ከ20 በላይ ባለሥልጣናት" የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው ይናገራሉ።

አግህ ግን ቁጥሩን "ከ2,000 በላይ" ያደርሰዋል። እዚህ ቁጥር ላይ በምን መንገድ እንደደረሰ አልጠቀሰም።

ከሳምንታት በኋላ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑት የፖለቲካ ተንታኙ ሙስጠፋ ኮሽቺሳም በኢራን ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ቀርበው እንደተናገሩት ወደ 100 የሚጠጉ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ አዛዦ በጦርነቱ ወቅት ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል፤ አልያም ለመመልመል ተሞክሯል።

የስልክ ጥሪዎቹ ዓላማ "ለማስፈራራት" ወይም "ለመግዛት" እንደሆነ አክለዋል።

"ትልልቅ ባለሥልጣናት" መሰል የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው የፖለቲካ ተንታኙ ተናግረዋል። ይህም አሊ ላሪጃኒን ያካትታል።

በዚህ ረገድ "የሞሳድ ተልዕኮ" ከሽፏል ሲሉም ተናግረዋል።

መግለጫቸው ትርክቱን በተለየ መንገድ ያሳያል። ሞሳድ የደኅንነት መዋቅርን ሰርስሮ የገባ "ክፍተት" እንዳልሆነ በመግለጽ፤ የእስራኤል "የሥነ ልቦና ጦርነት እንደከሸፈ እና ደካማ እንደሆነ" ገልጸዋል።

ሞሳድ፡ ከስለላ ድርጅትነት ትርክትን እስከመቆጣጠር

ሞሼን ፋክሀሪዛዴህን ጨምሮ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ላይ ግድያ ከመፈጸሙ ባሻገር ሞሳድ ወታደራዊ እና የኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ማሴሩ ተገልጿል።

የእስራኤል ሰላዮች እንቅስቃሴ እና በቅርብ ጊዜ የታየው የስልክ ጥሪ ከ12 ቀናቱ ጦርነት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም።

ሞሳድ ለዓመታት በኢራን የፖለቲካ እና ደኅንነት ሪፖርቶች ሲጠቀስ ቆይቷል። በግለ ታሪክ፣ በመጻሕፍት እና በፊልምም ሳይቀር ሞሳድ ይጠቀሳል።

ለዚህም 'ዴይስ ኦፍ ቴህራን' የተባለው መጽሐፍ ይጠቀሳል። መጽሐፉ በፓህላቪ አገዛዝ ወቅት የነበረውን የእስራኤል የስለላ ድርጅት እንቅስቃሴን ያሳያል።

የሞሳድ ተወካይ እና ኋላ ላይም በኢራን የእስራኤል ወታደራዊ ልዑክ ያቁብ ኒምሩዲ በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት መካከል ነው።

እነዚህ መጻሕፍት ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የስለላ ፉክክር የሚደረግባት አገር እንደሆነች ይገልጻሉ።

ፉክክሩ በእስራኤሉ ሞሳድ፣ በአሜሪካው ሲአይኤ እና በሶቪየቱ ኬጂቢ መካከል ነው። ይህም ውስብስብ የስለላ መረብ እንደሆነ ይጠቀሳል።

በኢራን የሚሠሩ ልብ ወለዳዊ ፊልሞች እና ተከታታይ ፊልሞች ላይም ሞሳድ ይጠቀሳል።

በ2020 የተለቀቀው 'ቴህራን' የተባለው ተከታታይ ፊልም የሞሳድ ሰላዮች በኢራን ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ፣ ተልዕኮ እንደሚፈጽሙ እና ከደኅንነት እንዲሁም ወታደራዊ ተቋማት ጋር እንደሚቀራረቡ ያሳያል።

ልብ ወለዳዊ ቢሆንም ሞሳድ በኢራን ሰርጎ ለመግባት ያለውን አቅም የሚጠቁም ነው።

በእርግጥ ይሄ የእስራኤልን መንግሥት ፖሊሲ እና ኢራናውያን ላይ ጫና ለማሳደር ያለውን ፍላጎት በቀጥታ የሚያሳይ ነው ለማለት አይቻልም።

ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ስለ እስራኤል የስለላ ሥራዎች የሚወጡ የተመረጡ መረጃዎች የሥነ ልቦና ጫና ለማሳደር ያለሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተንታኞች ያምናሉ።

የእስራኤልን የስለላ ብቃት ለመሳየት፣ የኢራንን ባለሥልጣናት ለማስፈራራት እንዲሁም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ያለውን ተቀባይነት ለማሳጣት ያለሙ እንደሆኑ ይታመናል።

የስለላ ተቋማት በሌሎች አገራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በብዛት በምሥጢር ይይዛሉ። አንዳንዴ ግን የተመረጡ መረጃዎች እና ትርክቶች ይለቀቃሉ።

እነዚህ ቁጥጥር ተደርጎባቸው የሚወጡ መረጃዎች የሥነ ልቦና ጫና ለማሳደር ይውላሉ።

በስለላው ዓለም 'ፐርሰፕሸን ማኔጅመነት' በሚል አገላለጽ ይታወቃል። ሰዎች አንድን ድርጊት ወይም ተቋም የሚመለከቱበትን መንገድ ለመቆጣጠር የሚውል አሠራር ነው።

በዚህ መንገድ የሕዝብን ዕይታ፣ አስተያየት ወይም ባህሪ ለመለወጥ ይሞከራል።

የሥነ ልቦና ዘመቻ ማድረግ፣ መረጃ ማሠራጨት እና ምሥጢራዊ እርምጃ መፈጸም ተጠቃሽ መንገዶች ናቸው።

ሞሳድ አድርጓቸዋል የተባሉት የስልክ ጥሪዎች በኢራን መገናኛ ብዙኃን ሽፋን የተሰጣቸው፤ ሞሳድ የኢራን ባለሥልጣናትን እንደሚያስፈራራ በሚጠቁም መንገድ ነው።

የኢራን የደኅንነት ተቋማት በእስራኤል የስለላ እና የደኅንነት ተቋማት ላይ ጫና ማሳደር እንደሚችሉ ሲገልጹ ቆይተዋል።

የስልክ ጥሪዎች የእስራኤል ደኅንነት መዋቅር አንድ ገጽታ ብቻ ናቸው።

በ12 ቀናቱ ጦርነት እንዲሁም በ40 ቀናቱ ጦርነት ወቅት እስራኤል ብዙ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲሁም የፖለቲካ እና ደኅንነት ኃላፊዎችን ዒላማ አድርጋ ገድላለች።

እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙበት ወቅት እና ትክክለኛ ዒላማ መምታታቸው፤ እስራኤል የባለሥልጣናቱን የስልክ ቁጥር እና የግል መረጃ ከማግኘቷ ጋር ተደማምሮ የደኅንነት ጫናዋ ምን ያህል እንደሆነ ጥያቄ አጭሯል።

"የደኅንነት ክፍተት" ሲባል የሞሳድ ሰላዮች ለኢራን ባለሥልጣናት መደወላቸው ብቻ አይደለም።

የግል መረጃ፣ ትክክለኛ ቦታ፣ እንቅስቃሴ እና በኢራን ባለሥልጣናት መካከል የሚደረግ ውይይትን በተመለከተ ለእስራኤል መረጃ የደረሰበት መንገድ ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

የኢራን የደኅንነት መዋቅር ምን ያህል ለውጭ ጣልቃ ገብነት የተጋለጠ ነው? የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነው።