ኢራን የብሔራዊ ቡድኑ ልዑካን አባላት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከላከላቸውን አስታወቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኢራን ዋሽንግተን የኢራን እግር ኳስ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫ ላይ እንዲሳተፉ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ካረጋገጠች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አሜሪካ ለብሔራዊ ቡድኑ ልዑካን ቪዛ ከልክላለች ስትል ከሰሰች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት አርብ ዕለት ኢራን እአአ ሰኔ 8 2018 ዓ.ም. በሎስ አንጀለስ ከምታካሄደው ጨዋታ 10 ቀናት ቀደም ብሎ ለሁሉም ተጫዋቾች እና "አስፈላጊ ለሆኑ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች" ቪዛ መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ኢራን "ይህንን ስርዓት በመጠቀም አሸባሪዎችን ወደ አሜሪካ ለማስገባት እንድትጠቀም" እንደማይፈቀድላትም ተናግረዋል።

በቱርክ የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ አሜሪካ "ለአብዛኛዎቹ የአስተዳደር እና የሥራ አስፈፃሚ ሠራተኞች" እና "ለቴክኒክ አማካሪዎች" ቪዛ በመከልከሏ "በስፖርት ላይ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት" ፈጽማለች ሲል ከስሷል።

ከኢራን መንግሥት ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ኃላፊ፣ ምክትላቸውን እና የሚዲያ ዳይሬክተርን ጨምሮ 15 የአስተዳደር ባለሥልጣናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ከተከለከሉት መካከል መሆናቸውን ዘግበዋል።

ቡድኑ ቅዳሜ ዕለት በቱርክ ከሚገኘው የልምምድ ሜዳቸው ተነስተው ለውድድሩ መቀመጫቸው ወደ ሆነው ሜክሲኮ ጉዞ ጀምረዋል። ቡድኑ እሁድ ዕለት ማለዳ ሜክሲኮ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በቪዛቸው መሠረት ቡድኑ ጨዋታው በሚካሄድበት በተመሳሳይ ቀን ወደ አሜሪካ ገብቶ መውጣት እንዳለበት የኢራን አምባሳደር ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል።

የአሜሪካን መግለጫ "ለመሸፋፈን የሚሞክር" ሲል ገልጾ "አሁን በኢራን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ላይ ሆን ተብሎ የሚደረግ አድልዎ የተሞላበት አያያዝ ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋግራችኋል" ሲል ኮንኗል።

የኢራን ኤምባሲ የዓለም አቀፍ እግር ኳስን ወደሚያስተዳድረው ፊፋ በመደወል ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል።

የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና በካናዳ በጥምረት የሚዘጋጅ ሲሆን ሰኔ 4 2018 ዓ.ም. ይጀመራል።

የኢራን እግር ኳስ ቡድን ዓለም ዋንጫን ማጣሪያ ማለፉን ያረጋገጠው ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እአአ በ2025 መጋቢት ወር ላይ ነው።

በዓለም ዋንጫ ታሪክ አስተናጋጅ አገር ጦርነት ውስጥ የገባችበትን አገር ብሔራዊ ቡድን ስትቀበል የመጀመሪያው ይሆናል።

ቡድኑ በግንቦት ወር በአሪዞና የነበረውን የልምምድ ሜዳ ወደ ሜክሲኮ ቀይሮታል።

የአሜሪካ አገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ በኢራን ብሔራዊ ቡድን እና በልዑካን ቡድኑ ላይ ስለጣለው እገዳ ምንም ያለው ነገር የሌለ ሲሆን ለቢቢሲ መስሪያ ቤቱ "ለአሜሪካውያን እና ለዓለም ዋንጫ ተሳታፈዎች ሰላም እና ደህንነት ቁርጠኛ መሆናችንን ማረጋገጥ እነፈልጋለን" ብሏል።

ኤጀንሲው "ሎስ አንጀለስን ጨምሮ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 11 ከተሞችን ለመጠበቅ በሚደረገው አጠቃላይ የመንግሥት አካሄድ ውስጥ በጥልቀት እንደሚሳተፉ" አስታውቋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለሕግ አውጪዎች እንደተናገሩት የኢራን የእግር ኳስ ልዑክ ከኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች ማካተት እንደማይፈቀድለት ተናግረዋል።

በኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ውስጥ የተካተቱ በርካታ ተጫዋቾች አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ስልጠናን ጨርሰዋል።

ኢራን ከቤልጂየም ጋር በካሊፎርኒያ እና ከግብፅ ጋር ደግሞ በሲያትል ጋር እንደምትጫወት የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።