የአውስትራሊያን ሕግ የሚጥሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች 99 ሚሊዮን ዶላር ሊቀጡ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውስትራሊያ መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጣለውን የዕድሜ ገደብ ለሚጥሱ ኩባንያዎች የደነገገውን ቅጣት በእጥፍ መጨመሩን አስታወቀ።

ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ ሕግ መውጣቱ ይታወሳል። ይህንን ሕግ የሚጥሱን በተመለከተ የወጣው ቅጣት በእጥፍ ጨምሮ 99 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን ተወስኗል።

የበይነ መረብ ደኅንነት ጥበቃ ክፍል እንዳለው፤ በተሻሻለው ሕግ መሠረት የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ክልከላውን ለማስተግበር ምን እርምጃዎች እንደወሰዱ በማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2025 ጀምሮ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ አውስትራሊያውያን ከ10 የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ታግደዋል።

ሆኖም ግን አሁንም ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም መቀጠላቸው ተገልጿል።

ሕጉን በመተላለፍ በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ላይ ምርመራ ተከፍቷል።

አውስትራሊያ ሕጉን ስታወጣ ብዙዎች ድጋፋቸውን ቢገልጹም መንግሥት ክልከላውን በቀላሉ መተግበር አልቻለም።

ቢቢሲ ያለፈው የካቲት ላይ ሲድኒ የሚገኝ ትምህርት ቤት ሲጎበኝ አብዛኞቹ ተማሪዎች ከክልከላው በኋላም ማኅበራዊ ሚዲያ እየተጠቀሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

የበይነ መረብ ጥበቃ ኮሚሽን እንዳለው፤ እገዳው ከመጣሉ በፊት ማኅበራዊ ሚዲያ ይጠቀሙ ከነበሩ 10 ታዳጊዎች መካከል ሰባቱ አሁንም ድረስ ገጾቹን "ማግኘት" ይችላሉ።

የአውስትራሊያ መንግሥት "የሚጠበቅባቸውን በበቂ ሁኔታ ያላደረጉ ገጾች" ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ክልከላውን የሚያስተገብረው ተቋም በቀጣይ ውጤታማ ምርመራዎች አድርጎ ደንብ የማስከበር እርምጃ እንደሚተገበርም አክሏል።

የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር "ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም አነስተኛውን ዕድሜ ከወሰንን በኋላ ስለ ጉዳዩ የምናደርገው ንግግር መለወጡ አስደስቶኛል። ሆኖም ግን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ሕጉን ለማክበር በቂ ጥንቃቄ አለማድረጋቸው ግልጽ ነው" ብለዋል።

አሁንም ድረስ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እየተጠቀሙ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

የኮምንኬሽን ሚኒስትር አኒካ ዌልስ፤ በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች "ደስተኛ" አለመሆናቸውን ጠቅሰው፤ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም እንዲቀጥሉ "የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው" ብለዋል።

"የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እንደ ቴክኖሎጂ ተቋማት ያለ መንገድ በመከተል የሚጠበቅባቸውን ከማድረግ እያመለጡ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

አውስትራሊያ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያወጣችውን እገዳ ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎችም አገራት ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

ዩኬ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ እንደምታግድ ገልጻለች።