"በስድስት ዓመቴ የወር አበባ ማየት መጀመሬ ሐኪሞችን ግራ አጋብቶ ነበር"

ጋቢ በልጅነቷ

የፎቶው ባለመብት, Gabby

የምስሉ መግለጫ, የ26 ዓመቷ ጋቢ ሰውነቷ መጎርመስ ሲጀመር በጣም ልጅ ስለነበረች ብዙም አታስታውስም
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ጋቢ የወር አባባ ማየት እና የሰውነት ፀጉር ማብቀል የጀመረችው ስድስት ዓመት ሲሆናት ነበር።

የመጀመሪያ ልጇ ላይ በሚታዩት ለውጦች የተደናገጠችው እናቷ አጣድፋ ወደ ሐኪም ወሰደቻት።

"የሕጻናት ሕክምና ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች ጥናት ማድረግ ነበረቸባው፤ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ነገር ሰምተው አያውቁም" ስትል የኢንግላንድ ነዋሪ የሆነችው ጋቢ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"እንዴት ህክምና መስጠት እንዳለባቸው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ሆስፒታሎችን ማነጋገር ነበረባቸው" ስትል ታስታውሳለች።

አሁን 26 ዓመቷን የያዘችው ጋቢ፤ 'ሴንትራል ፕሪኮሸስ ፒዩበርቲ' የተባለው የጤና ሁኔታ እንደነበረባት ተረጋግጧል። ይህ የጤና ሁኔታ ሴት ሕጻናት ከስምንት ዓመት በፊት፣ ወንዶች ደግሞ ከዘጠኝ ዓመታቸው አስቀድሞ ጉርምስናን ሲጀምሩ የሚከሰት ነው።

ምን ያህል ሰዎች ይህ ሁኔታ ያጋጥማቸውል የሚለው ከአገር አገር በከፍተኛ መጠን ይለያያል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ በብዛት ሁኔታው የሚያጋጥማቸው ሴት ልጆች ናቸው።

በየዓመቱ 10 ሺህ ሴት ልጆች ውስጥ ከ0.2 እስከ 26 የሚደርሱት ይህ ሁኔታ ይገኝባቸዋል። ከ10 ሺህ ወንድ ልጆች ውስጥ ደግሞ ከ0.02 እስከ 0.9 የሚሆኑት ሁኔታው ይታይባቸዋል።

ያለ ዕድሜ መጎርመስ የሚታይባቸው ልጆች የሚቸገሩ በአካላዊ ለውጦቹ ብቻ አይደለም። በወደፊት ሕይወታቸውም ለተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች እንዲሁም ለልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

"ከሁሉ የተለየሁ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር"

ጋቢ ፈገግ ብላ የተነሳችው ሰልፊ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Gabby

የምስሉ መግለጫ, ጋቢ ያለ ዕድሜ የሚመጣ ጉርምስና ላይ ያለውን ዝምታ መስበር እንደምትፈልግ ትናገራለች

ጋቢ ጉርምስናዋን ስትጀምር በጣም ልጅ ስለነበረች ብዙም አታስታውስም። ነገር ግን ህመም እና ብስጭት ውስጥ ትገባባቸው የነበሩ ጊዜያትን ግን ከአእምሮዋ አልጠፉም።

"በጣም ህመም ውስጥ ሁኜ መሬት ላይ ጥቅልል ብዬ የተኛሁባቸውን ጊዜያት አስታውሳለሁ" ትላለች።

ጋቢ ለአንድ ዓመት ገደማ ምርመራዎችን ስታደርግ እና ወደ ስፔሻሊስቶች ስትላክ ቆይታለች። ያደረገችው 'ኤምአርአይ' ምርመራም ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ምልክት አእምሮዋ ውስጥ አልተገኘም።

የ'ሴንትራል ፕሪኮሸስ ፒዩበርቲ' እንዳለባት የታወቀው እና ሆርሞንን የሚገድብ ሕክምና የተሰጣት ከዚህ በኋላ ነው።

"የተለዩ እንደሆንኩ በእጅጉ ይሰማኝ ነበር፤ ምክንያቱም እነዚያ ሁሉ ምርመራዎች እያደረግኩ ነበር። ሆርሞኖቼን ለማቆም በየሦስት ሳምንቱ መርፌ እወጋ ነበር" ስትል ታስታውሳለች።

ጋቢ 13 ቁጥር ያለበት የልደት ኬክ ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Gabby

የምስሉ መግለጫ, ጋቢ ታዳጊ እያለች ጓደኞቿ ታላቅ ትመስል እንደበር ተናገራለች

'ጎናዶትሮፒን-ሪሊዚንግ ሆርሞን አጎኒስትስ (GnRH) የተባለው ሆርሞንን የሚገድብ ሕክምና የሕጻናት እድገት ፍጥነቱ በተለመደው መልኩ እንዲሆን ያደርጋል።

መርፌውን መውሰድ የሚያቆሙት ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 12 ዓመት ሲደርስ ነው። ከዚያ በኋላ መደበኛው የጉርምስና ሂደት ይጀምራል።

መድኃኒቱ የጋቢን እድገት መግታት ቢችልም፤ ሰውነቷ ለአንድ ዓመት ያህል የጉርምስና ለውጦችን አስተናግዶ ነበር።

"በመስታወት ስመለከት የእውነት ማን እንደሆንኩ ልረዳ አልቻልኩም ነበር። ምክንያቱም በአእምሮዬ ከሚሰማኝ በበለጠ ዕድሜዬ የሄደ እመስላለሁ። በዕድሜዬ መሆን ከነበረብኝ በላይ የበሰልኩ መሆን እንዳለብኝ እንዲሰማኝም ያደረገኝ ይመስለኛል" ትላለች።

ያለ ዕድሜ የሚመጣ ጉርምስና እንዴት ይፈጠራል?

ከዕድሜ ቀድሞ ከሚመጣ ጉርምስና ጋር በተያያዘ ሁለት ሁኔታዎች አሉ፦

  • 'ፔሪፌሪያል ፕሪኮሸስ ፒዩፐርቲ' (PPP) የሚባለው የሚፈጠረው፣ እንቁላልን የሚያዘጋጀው እንቁልጢ (ኦቫሪ) እና የወንድ የዘር ፍሬን የሚያዘጋጀው የሰውነት ክፍል 'ሃይፖታላመስ' ከተባለው የአእምሮ ክፍል ውጪ በሆነ ሁኔታ የወሲብ ሆርሞኖችን መልቀቅ ሲጀምሩ የሚፈጠር ነው። 'ሃይፖታላመስ' የሰውነት ሆርሞኖች መቆጣጠሪያ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል የአእምሮ ክፍል ነው። ይህ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ የሚፈጠረው እንደ የኦቫሪያን ወይም የዘር ፍሬ ዕጢዎች፣ የአድሬናል ችግር ወይም ለውጫዊ የፆታ ስቴሮይዶች እንደ መጋለጥ ያሉ ሌሎች የጤና እክሎች በሚኖሩበት ጊዜ ነው።
  • 'ሴንትራል ፕሪኮሸስ ፒዩፐርቲ' (CPP) ደግሞ ሰውነት ጊዜው እጅግ አስቀድሞ ወደ መጎልመስ ሲጀመር፤ ነገር ግን ሂደቱ በመደበኛው መልኩ ሲ ቀጥል የሚፈጠር ነው። ይህ ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥመው ያለ ዕድሜ የመጎልመስ ዓይነት ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በምን እንደሚፈጠር በግልጽ አይታወቅም።

ዴንማርክ ውስጥ ከአውሮፓውያኑ 1998 እና 2017 ባሉት ዓመታት ውስጥ በ8,596 ሕፃናት ላይ የተደረገና በ2020 የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በየዓመቱ ከ10 ሺህ ሴት ልጆች ውስጥ በአማካይ 9.2 ያህሉ፤ ከ10 ሺህ ወንድ ልጆች ውስጥ ደግሞ 0.9 ያህሉ 'ሴንትራል ፕሪኮሸስ ፒዩፐርቲ' (CPP) ያጋጥማቸዋል።

በተጨማሪም ጥናቱ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ይህ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሴቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ፣ ወንዶች ደግሞ በሁለት እጥፍ መጨመሩን ደርሶበታል።

ኮሪያ ውስጥ የተደረገ ጥናትም ሴት ልጆች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ አሳይቷል።

ተመራማሪዎች ሴት ልጆች ለምን ከፍ ባለ መጠን ታጋላጭ እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ አልደረሱበትም። ነገር ግን መንስኤው የአካባቢያዊ እና የባዮሎጂ ሁኔታዎች ድብልቅ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

በአጠቃላይ የአንድ አገር ሕዝብ ውስጥ ሴት ልጆች ለጉርምስና የሚደርሱበት ዕድሜ እየቀነሰ መምጣቱን የሚያመለክት ሊሆን እንደሚችልም ተመራማሪዎች ይጠቅሳሉ።

አንጎል ጉርምስናን እንዴት እንደሚቆጣጠር የሚያሳይ ሥዕል

ሴት ልጆች ጡት ማብቀል የሚጀምሩበት አማካይ ዕድሜ በየአስር ዓመቱ በሦስት ወር ገደማ እየቀነሰ መምጣቱን ከ1977 እስከ 2013 ባሉት ዓመታት ውስጥ በተደረጉ ጥናቶች ላይ የተካሄደ ትንተና አሳይቷል።

ጥናቶች ወንድ ልጆችም የሚጎረምሱበት ዕድሜ እየቀነሰ መምጣቱን ቢያመለክቱም፤ የለውጡ ፍጥነት ሴት ልጆች ላይ እንደታየው አይደለም።

በብራዚል የሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ የሆርሞን ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አና ፒንሄሮ ማቻዶ ካንቶን፣ የአንድ ዓመት ልጅን ጨምሮ ይህ ሁኔታ ያጋጠማቸው በርካታ ሕጻናትን ማከማቸውን ይናገራሉ።

ይህ የጤና እልክ ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የሚከሰተው በሃይፖታላመስ ላይ በሚፈጠሩ ጉዳቶች ምክንያት ነው። የአእምሮ ዕጢዎችም ጉርምስና እጅግ ቀድሞ እንዲጀምር አድርገው ተገኝተዋል።

ዶ/ር ካንቶን እና የምርምር ቡድናቸው እንደ አመጋገብ እና ከባቢያዊ ሁኔታ ያሉ ውጫዊ ጉዳዮችም መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል መላ ምት አላቸው።

"ሕጻናት ላይ የሚከሰት ከመጠን ያለፈ ውፍረትም ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ መንስኤ ነው፤ ምክንያቱም ሕፃኑ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ሲኖረው፣ ጉርምስ ይፋጠናል" ሲሉ ዶ/ር ካንቶን ያስረዳሉ።

እናት እና አባለት ሁለት ሴት ልጆቻቸውን በመሐላቸው አስቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, Bruno Bernardi

የምስሉ መግለጫ, የበርናርዲ ቤተሰብ ሴት ልጆቻቸው ያለ ዕድሜ የሚመጣ ጉርምስና እንዲኖርባቸው የሚያደርግ የዘረ መል ለውጥ እንዳለባቸው በምርመራ ታውቋል

በዚህ ሂደት ውስጥ ዘረመልም (ጂኔቲክስ) ሚና አለው። 'ሴንትራል ፕሪኮሸስ ፒዩፐርቲ' እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ 'ኤምኬአርኤን3' በተባለው ዘረመል ላይ የሚከሰት ለውጥ አንዱ እንደሆነ በ2013 የወጣ ጥናት አሳይቷል።

እህትማማቾቹ የ10 ዓመቷ ላራ የ8 ዓመቷ ቢያትሪስ ይህ ዓይነቱ የዘረመል ለውጥ ተገኝቶባቸዋል። ይህ ሁኔታ እንዳለባቸው የታወቀው ላራ በሕጻንነቷ የጡት እድገት ምልክቶችን ማሳየት ስትጀምር ነው።

እናታቸው ሌያ ቤርናርዲ "በሁኔታው እጅግ ደንግጬ ነበር፤ ምክንያቱም ዕድሜዋ ገና አምስት ዓመት ከ10 ወር ነበር" ትላለች።

ዶ/ር ካንቶን እና የምትመራው ቡድን ይህ የዘረመል ለውጥ ከአባታቸው የወረሱት እንደሆነ ደርሶበታል። ታናሽ እህቷ ቢያትሪስም ያለ ዕድሜዋ ጉርምስና የምትጀምርበት ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ማወቅ ችለዋል።

ሁኔታው ቀድሞ በመታወቁ ሰባት ዓመቷ ላይ ምልክቶችን ማሳየት ስትጀምር ወዲያውኑ ሕክምና ተጀምሮላታል።

ያለ ዕድሜ ጉርምስና በአካል ላይ የሚያስከትለውን ለውጥ የሚያሳይ ሥዕል

የካንሰር እና የካርዲዮቫስኩላር ተጋላጭነት

ያለ ዕድሜ የሚመጣ ጉርምስና ሕክምና ሳይደረግለት ከቀረ በአእምሮ እና በአካል ላይ ከፍተኛ የጤና ስጋት እንደሚደቅን ዶ/ር ካንቶን ያስጠነቅቃሉ።

"አስበው፣ አንዲት ልጅ በስድስት ወይም በሰባት ዓመቷ ጡት ማብቀል ስትጀምር፤ ትምህርት ቤቷ ውስጥ ካሉ እኩዮቿ እና ከሌሎች ልጆች እጅግ የተለየች ትሆናለች። በጣም አስቸጋሪ ነው" በማለት ተጽእኖውን ያብራራሉ።

አስቀድመው ጉርምስና የሚጀምሩ ልጆች ቁመታቸው አጭር የመሆን አዝማሚያ ይታይበታል።

ከፍተኛ ሕዝብ ቁጥርን በማካተት የሚደረጉ ጥናቶች፣ ያለ ዕድሜ በሚመጣ ጉርምስ እንዲሁም ከልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች መካከል ግንኙነት መኖሩን አሳይተዋል።

እንደ የጡት ካንሰር ላሉ ከወሲብ ሆርሞኖች ጋር ከተያያዙ የካንሰር ዓይነቶች ጋርም ያለው ግንኙነት በጥናት ተደርሶበታል።

ዶ/ር ካንቶን እንደሚናገሩት፣ በተቻለ ፍጥነት ምርመራ የሚደረግ እና ሕክምና የሚሰጥ ከሆነ የጤና አደጋዎቹን መቀነስ ይቻላል።

Beatriz and Lara Bernardi stand back to back behind a gold birthday cake. In the background are silver party decorations and two gold balloons - one says 8 and the other says 10.

የፎቶው ባለመብት, Bruno Bernardi

የምስሉ መግለጫ, Beatriz (left) and Lara (right) will continue to take hormone blockers until they're around 11 years old

ወላጆቹ ሌያ እና ብሩኖ መጀመሪያ ላይ ስጋት ገብቷቸው የነበረ ቢሆንም አሁን ሴት ልጆቻቸው መደበኛ የሆነ ልጅነት ጊዜ እያሳለፉ መሆኑ እፎይታ ሰጥቷቸዋል።

እናት ሌያ "ላራ [መጎርመስ] ስትጀምር፣ ይህ ነገር ለምን በእሷ ላይ ብቻ እንደተፈጠረ ታስብ ነበር። ለምን እርሷ የተለየች ሆነች? ለምን ይህንን መድኃኒት ትወስዳለች?" ስትል ልጇ ላይ የተፈጠረውን ግራ መጋባት ታስረዳለች።

ሁለቱ ወላጆች ያለፉበትን ማጋራታቸው ሌሎች ወላጆች ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲሁም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች እርዳታ እንዲያገኙ ያስችላል የሚል ተስፋ አላቸው።

በልጅነቷ ይህንን ያሳለፈችው ጋቢም ስለ ሁኔታው በግልጽ መናገር ትወዳለች። ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሁኔታው ያጋጠማቸው ሰዎች እፍረት እንዳይሰማቸው ታግዛለች።

ያለው ግንዛቤ "ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ ስገነዘብ ትንሽ ተናድጄ ነበር" ትላለች።

"በርካታ ሰዎች እኔን ማነጋገር እንደጀመሩ ስመለከት ያለፍኩበትን ለዓለም መናገሬ ትክክለኛው ነገር እንደሆነ አውቄያለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።