ትራምፕ በአዲስ የታሪፍ 'ጥቃት' የንግድ ጦርነት መጀመራቸውን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ፣ አሜሪካ የጣለችው አዲስ የታሪፍ ናዳ ካናዳን "ለመጉዳት እና ለመከፋፈል" የተነደፈ "የተሳሳተ ስሌት" መሆኑን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አርብ ዕለት የንግድ ድርድሩ ከተቋረጠ በኋላ ነው።
ትራምፕ በድርድሩ ከካናዳ ብዙ መጠየቃቸውን እና በእነርሱ በኩል ግን ትንሽ ማቅረባቸውን የተናገሩት ካርኒ፣ አሁን ላይ አሜሪካ እና ካናዳ በንግድ "ጦርነት" ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ጥቃት ሲሰነዘርባችሁ ጦርነት ውስጥ ትገባላችሁ፤ ጥቃት ተሰንዝሮብናል" ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ከመስከረም 8 ጀምሮ በብረት ፣ በወተት፣ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እና በመሳሰሉት ላይ ከአገሪቱ የሚገቡ ምርቶች ላይ በአሜሪካ ታሪፍ ልክ ቀረጥ በመጣል ምላሽ እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።
የንግድ ውይይቱ መቋረጡ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነትን የሚያባብስ ይሆናል። ወደ መፍትሔ የሚወስድም ግልጽ መንገድ የለም። የአሜሪካው ፕሬዚደንት እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።
ካርኒ " ያቀረቡትን ሁሉ መቀበል አንችልም። የጠየቁትንም አንሰጥም" ብለዋል።
ሁለቱም አገራት በውይይቱ ስምምነት ላይ እንደርሳለን የሚል ተስፋ ሰንቀው የነበረ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች በመጨረሻው ሰዓት ሃሳባቸውን በመለወጥ ከተካሰሱ በኋላ ውይይቱ ተቋርጧል።
ይህንንም ተከትሎ ካናዳ ከዚህ ቀደም በብረት፣ በአልሙኒየም፣ በአውቶሞቢል እና በእንጨት ምርቶቿ ላይ በአሜሪካ ተጥሎባት ከነበረው ታሪፍ በተጨማሪ በምርቶቿ ላይ 50 በመቶ አዲስ ታሪፍ ተጥሎባታል።
አዲሱ ታሪፍ ውስን ሲሆን ወይን፣ የወተት ተዋፅኦ፣ ሲሚንቶ ፣ ልብስ እና የስፖርት ቁሳቁሶችን ጨምሮ ከካናዳ ወደ አሜሪካ በሚገቡ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ላይ ወይም በአጠቃላይ አምስት በመቶ የሚሸፍን ነው።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ካናዳ ፍላጎቶቿን ለመጠበቅ "ያለማመንታት" የበቀል እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ተናግረዋል። የእርምጃዎቹ ዝርዝር በሚቀጥሉት ቀናት ይፋ እንደሚደረግም ካርኒ ተናግረዋል።
ወግ አጥባቂ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በካናዳ የሚገኙ ሌሎች የፌዴራል ፓርቲዎች መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ሰጥተዋል። አንዳንድ የካናዳ ግዛቶች መሪዎችም እንዲሁ ከጎናቸው መሆናቸውን አሳይተዋል።
ከሌሎች አገሮች በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣል ቀረጥ የትራምፕ የንግድ ፖሊሲ ቁልፍ አካል ሲሆን፣ ይህም የአሜሪካን የማኑፋክቸሪንግ ፖሊሲ እንደሚያሳድግ እና በአገር ውስጥም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ትራምፕ ይከራከራሉ።
ተቺዎች ግን ታሪፉ ለአሜሪካን ሸማቾች የፍጆታ ዋጋን ያናረ፣ የዓለም ኢኮኖሚን ያስተጓጎለ እና ያበላሸ እንደሆነ ይናገራሉ።
ካርኒ ውይይቱ መቋረጡን ካስታወቁ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ለዜጎቻቸው ባዳረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው፣ አሜሪካ በመጨረሻው ሰዓት "ፍትሃዊ " እና "ተመጣጣኝ " ያልሆኑ ለውጦችን አድርጋለች ሲሉ ከስሰዋል።
የአሜሪካ ተደራዳሪዎች በበኩላቸው ካናዳ ቀደም ሲል በተስማሙባቸው ስምምነቶች ላይ "አዲስ ፍላጎቶችን በማቅረብ ወደኋላ ተመልሳለች" ብለዋል።
ውይይቱን ለመቀጠል ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌለም የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሬር ቅዳሜ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል። ጨምረውም አሜሪካ ከዚህ ቀደም በካናዳ ላይ ጥላው የነበረውን ታሪፍ ለመቀነስ ተዘጋጅታ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች በካናዳ ብረት እና አልሙኒየም ላይ የተጣለው የአሜሪካ ታሪፍ ከ50 በመቶ ወደ 25 በመቶ እንዲሁም በካናዳ አውቶሞቢሎች ላይ የተጣለው ቀረጥ ደግሞ ከ25 በመቶ ወደ 15 በመቶ እንዲቀነስ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲነገጋሩ እንደነበር ተሰምቷል።
በምላሹም የካናዳ ግዛቶች እንደገና የአሜሪካ የአልኮል መጠጦችን መሸጥ እንዲጀምሩ የማድረግ ሀሳብ ተነስቶ ነበር።
ካርኒ ግን አሜሪካ ካናዳ ከሌሎች አጋሮች ጋር አዲስ የንግድ ስምምነቶችን የመፍጠር አቅምን መገደብን ጨምሮ "ተቀባይነት የሌላቸው" ውሎችን አቅርባለች ብለዋል። ካናዳ በመጨረሻው ሰዓት ሃሳቧን ለውጣለች በሚል የቀረበውን ክስም ካርኒ አጣጥለዋል።
የድርድሩ መክሸፍ፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የአሜሪካ እና የካናዳ ባለሥልጣናት ሁለቱንም አገራት የሚጠቅም ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ሲሰጡት የነበረውን ተስፋ የቀለበሰ ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ወዲህ በሁለቱ ግዙፍ የንግድ አጋሮች መካከል ውጥረት ተፈጥሯል። ትራምፕ ሰፊ ዓለም አቀፍ ታሪፍ መጣላቸውም ለብዙ አሥርተ ዓመታት በካናዳ እና በአሜሪካ መካከል የነበረውን ነጻ የንግድ ገበያ አፍርሷል።















