"የግድያ ሙከራ" ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት የትግራይ ሊቃነ ጳጳሳት "የቁም እስር" ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ

የፎቶው ባለመብት, Tigray Orthodox Tewahedo Church Diocese Of Humera

የምስሉ መግለጫ, ቤተ ክህነቱ "የግድያ ሙከራ" ሲል የጠራው የማክሰኞ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም. ክስተት ያነጣጠረው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ላይ እንደሆነ አስታውቋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአክሱም ከተማ "የግድያ ሙከራ" እንደተፈጸመባቸው የተነገረው ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት "የቁም እስር" ላይ እንደሚገኙ የቅርብ ሰዎቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተነጠሉ አባቶች የተቋቋመው የመንበረ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ላዕላይ ቤተ ክህነት ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት በጸጥታ አካላት ጥበቃ ሥር የሆኑት ከቅዳሜ ሐምሌ 4/2018 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ተገልጿል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከክልሉ ማዕከላዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሺሻይ ግርማይ እና የአክሱም ከተማ የሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ቴዎድሮስ በየነ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ቤተ ክህነቱ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በተባሉት አባቶች መኖሪያ ቤት ላይ ተኩስ መከፈቱን ገልጾ ነበር። ድርጊቱንም "የግድያ ሙከራ" ሲል ገልጾታል።

ከክስተቱ በኋላ ከቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት አቡነ ናትናኤል፤ ሰኞ ሰኔ 9 ሌሊት ስድስት ሰዓት ተኩል ተኩስ መከፈቱን ተናግረው ነበር።

"በተለይ አቡነ አረጋዊ ማረፊያ ክፍል የሚገኝበት ሕንጻ ላይ አርፎ በተወሰነ መልኩም ሕንጻውን ነድዶ፤ ግማሽ ብሎኬት ተገንጥሎ ወድቋል" ሲሉም ሁኔታውን ገልጸዋል።

የአክሱም ከተማ ፖሊስ ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ ሦስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጾ ነበር።

የከተማዋ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ አሰፋ ገብረማርያም "በተደረገው ማጣራት" ድርጊቱ በሊቃነ ጳጳሳቱ መኖሪያ ቤት "ጥበቃ እንደተፈጸመ መረጋገጡን" እንደተናገሩ ትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ተነጥሎ የተቋቋመው የትግራይ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቡነ አረጋዊ እና አቡነ ናትናኤል ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እንደነበር የአንዱ አባት ረዳት ዲያቆን የማነ ሃይላይ ተናግረዋል። የጳጳሱ አሽከርካሪ የሆኑትን አብርሃ ገብረገርግስም ይህንኑ ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።

የአቡነ ናትናኤል ረዳት የሆኑት ዲያቆን የማነ እንደሚያስረዱት፤ በዕለቱ ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ ላይ ሁለቱ አባቶች ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ለጥያቄ እንደሚፈለጉ" ተነግሯቸው ነው።

የአቡነ ናትናኤል አሽከርካሪ የሆኑት አብርሃ ገብረገርግስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተከትለው መሄዳቸውን ተናግረዋል። ከሰዓታት በኋላ ፖሊስ ሊቃነ ጳጳሳቱ "በከባድ ወንጀል እንደተጠረጠሩ" እንዲሁም ለመለቀቅ ለእያንዳንዳቸው "የ300 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ" መጠየቁን አብርሃ አስረድተዋል።

የአቡነ ናትናኤል ረዳት የሆኑት ዲያቆን የማነም ሊቃነ ጳጳሳቱ ምሽት 4፡00 ሰዓት ገደማ የተለቀቁት ይህ "የዋስትና ገንዘብ ተከፍሎ" መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፖሊስ አቡነ ናትናኤልን "ትግልን ማደናቀፍ" በሚል እንደጠረጠራቸው በጣቢያው ከተገኙ ሰዎች መስማታቸውንም ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ይህንን ክስ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም። ስለዚህ ክስ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራም አልተሳካም።

እንደ የማነ ገለጻ፤ ሁለቱ አባቶች ወደ መኖሪያቸው ከተመለሱ በኋላ ሊያገኟቸው አልቻሉም።

"በምሽት 4:15 ገደማ ተመልሰዋል። ከዚያ በኋላ መግባትም መውጣትም አይቻልም። ስልካቸውንም በተደጋጋሚ ብንሞክርም አልሰራም፤ ስልካቸው ከእነርሱ ጋር እንደሌለ እና ከማንም ጋር መገናኘት እንደማይችሉ ነው ያለኝ መረጃ" ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቱ የመንበረ ሰላማ ዋና ጽሕፈት ቤት ውስጥ ባለ መኖሪያ ቤት እንደሚገኙ የሚገልጹት የማነ፤ "ማንም ሰው እንዲገባም ሆነ እንዲወጣ አይፈቀድም። ሁላችንም ተከልክለናል" ብለዋል።

"በተደጋጋሚ ስልክ ብንሞክርም አይሰራም። ስልካቸው እነርሱ ጋር እንዳልሆነ እና ከማንም ጋር መገናኘት እንደማይችሉ ነው ያለኝ መረጃ" ሲሉም አክለዋል።

ወደ መኖሪያ ሕንጻው በመግባት አባቶቹን ለማነጋገር ቢሞክሩም "ከላይ የወረደ ትዕዛዝ ነው" በሚል "በፖሊስ እንደተከለከሉ" ተናግረዋል።

የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች መግባት ቢፈቀድላቸውም እነርሱም ሊቃነ ጳጳሳቱን እንዳላገኙ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በሁለቱ አባቶች መኖሪያ ላይ ተኩስ ከተከፈተ በኋላ አቡነ ናትናኤል በቅርቡ በትግራይ ክልል የሚታየውን "የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ" በተመለከተ ሰጥተውታል የተባለው አስተያየት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በመቀለ ከተማ የአብነት ተማሪዎች "በታጠቁ ኃይሎች ተይዘው ወደ ወታደራዊ ሥልጠና ካምፕ" እንደተወሰዱ አንድ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወቅቱ ስለዚህ ጉዳይ አስተያየት የሰጡት አቡነ ናትናኤል፤ "ይህን ጉዳይ መቆም አለበት፤ እጃችሁን ከቤተክርስቲያን ላይ አንሱ" ብለው ነበር።

ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በባለፈው ሳምንቱ ክስተት የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ በተወሰኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ከታየው ተቃውሞ ጋር ይያያዛል የሚል እምነት ይኖራቸው እንደሆነ ተጠይቀዋል።

"ይቅርታ እንዲጠይቁ" በሚል የተሰጡትን አስተያየቶች መመልከታቸውን የገለጹት አቡነ ናትናኤል፤ ክስተቱ ግን ከዚህ ጋር ይገናኛል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

"እኔ ሃሳቤን ነው የተናገርኩት። ለትውልድ ይሆናል፣ ለሀገር ይጠቅማል፣ እውነት መስሎ የታየኝን ነው የተናገርኩት። አንድ ሰው ደግሞ እውነት በመናገሩ ሌላ ነገር ይመጣበታል ብዬ ብዙም አላስብም" ብለው ነበር።