በናይጄሪያ በደረሰ የጀልባ አደጋ ቢያንስ 46 ሰዎች ሞቱ

በጀልባ የሚጓዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ሶኮቶ ግዛት ውስጥ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ቢያንስ የ46 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

ከ70 በላይ ሰዎችን ይዞ ሲጓዝ የነበረው ጀልባ ከጫናቸው ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ሕጻናት እንደነበሩ ተገልጿል።

ጎሮንዮ በተባለው የአገሪቱ አካባቢ የ46 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የፖሊስ ቃል አቀባይ አህመድ ሩፋኢ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ የ16 ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ እንደተቻለ፤ ነገር ግን 15 ሰዎች እስካሁን ደብዛቸው እንደጠፋ አስረድተዋል።

የነፍስ አድን ሥራው አሁንም መቀጠሉን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ወደ አካባቢው መጓዝ አዳጋች መሆኑን የሚናገሩት ሩፋኢ፣ የጸጥታ አካላት እና የአደጋ ሠራተኞች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አክለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው አንድ የዓይን እማኝ፣ ጀልባው ላይ ተሳፍረው የነበሩት ሕጻናት የሩዝ እርሻ ላይ ለመስራት ሲጓዙ ከነበሩ የእርሻ ባለቤቶች እና የጉልበት ሠራተኞች ጋር አብረው ነበሩ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በአቅራቢያው የሚገኝ መስጊድ ውስጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከመፈጸሙ በፊት፣ በምንጣፍ እና በባህላዊ አልባሳት የተጠቀለሉ የ50 ሰዎች አስከሬኖችን መመልከታቸውን የዓይን እማኙ ተናግረዋል።

የናይጄሪያ የአደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ኢዚኬል ማንዞ "ጎራኡ በጣም ሩቅ ቦታ ነው . . . ቡድናችን ወደዚያ ገጠራማ ሥፍራ ተጉዟል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ናይጄሪያ ውስጥ የጀልባ መገልበጥ አደጋ የተለመደ ነው። ለዚህም ጀልባዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው መጫናቸው፣ ጥገና የሚደረግላቸው አለመሆኑ እንዲሁም የደኅንነት ሕጎች አለመከበራቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ከአንድ ወር በፊት፣ በጂጋዋ ግዛት አንድ ጀልባ ተገልብጦ አምስት ሰዎች ሰጥመዋል። ጥር ላይም አርሶ አደሮችን እና አሳ አጥማጆችን አሳፍሮ ከጂጋዋ ወደ ዮቤ ግዛት ሲጓዝ የነበረ ጀልባ ተገልብጦ 26 ሰዎች ሞተዋል።

በተመሳሳይ በታኅሳስ 2024 ከ200 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ በናይጀር ወንዝ ሲጓዝ የነበረ ጀልባ ከተገለበጠ በኋላ፣ የ54 ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተጓዦች ደኅነታቸው በተጠበቁ ጀልባዎች እንዲጓዙ፣ የሕይወት አድን ጃኬት እንዲቀርብላቸው፣ ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ጠባቂዎች እንዲሰማሩ እንዲሁም የጀልባ አሽከርካሪዎች ብቃት እና ፈቃድ ያላቸው መሆኑ እንዲረጋገጥ ሲመክሩ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ሙሉ በሙሉ አልተተገበሩም ወይም በአግባቡ እንዲፈጸሙ አልተደረገም።

በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ጨምሮ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ወንዞች ወሳኝ የትራንስፖርት አማራጭ ናቸው። በርካታ መንደሮች ውሃ አቅራቢያ ይገኛሉ። ጥሩ ይዞታ ላይ ያሉ መንገዶች ማነስ እና የድልድዮች አለመኖርም የምድር ጉዞን አስቸጋሪ አድርጎታል።

ናይጄሪያ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ሰዎችን እና ዕቃዎችን ወደ ገበያ እንዲሁም ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማጓጓዝ ጥቅም ላይ የሚውሉት ከእንጨት የተሰሩ ጀልባዎች ናቸው።