ወደ ዩኬ ሊላክ የነበረ 28 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኮኬይን ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, NDLEA
ከዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መረብ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የተጠረጠረ አንድ ናይጄሪያዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሊላክ የነበረ ዋጋው ወደ 28 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኮኬይን መያዙን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ዋለ።
አፎላቢ ካዜም ማይክል የተባለው ተጠርጣሪ ባለፈው ሳምንት ወደ ፓሪስ ለመብረር በዝግጅት ላይ እያለ በሌጎስ አውሮፕላን ማረፊያ መያዙን የናይጄሪያ የአደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር ኤጀንሲ አስታውቋል።
በኢንስታግራም ላይ 700,000 ተከታዮች ያሉት እና "ኬሲ ለግዠሪ" (KC Luxury) በመባል የሚታወቀው የ49 ዓመቱ ግለሰብ፣ በኦንላይን ገጾቹ ላይ በወርቅ እና በቅንጦት ዕቃዎች ንግድ ላይ የተሰማራ ነጋዴ ሆኖ ራሱን ያቀርብ ነበር።
ባለሥልጣናት ግን፣ ግለሰቡ ከደቡብ አሜሪካ በናይጄሪያ በኩል ወደ አውሮፓ እና እስያ ኮኬይን የሚያዘዋውረው ሕገ ወጥ ቡድን የናይጄሪያ "ዋና አስተባባሪ" እንደነበር ይከስሳሉ።
ማይክል ስለቀረቡበት ክሶች እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
የናይጄሪያ ብሔራዊ የአደንዛዥ ዕፅ ሕግ አስፈፃሚ ኤጀንሲ (ኤንዲኤልኢኤ)፣ ሰኞ ሐምሌ 27 በሌጎስ በሚገኝ የእቃ መላኪያ ማዕከል ውስጥ በቡናማ ሳጥኖች ውስጥ ተደብቆ የነበረ 184.5 ኪሎ ግራም ኮኬይን መገኘቱን አስታውቀዋል።
ኮኬይኑ፣ ለዓመታት ዕፆችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሌሎች የአውሮፓ ክፍሎች እና እስያ ለማዘዋወር ናይጄሪያን እንደ መተላለፊያ ማዕከል ይጠቀም በነበረ ዓለም አቀፍ የአዘዋዋሪዎች መረብ ሊላክ የነበረ መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል።
ማይክል ከአገር ለመውጣት ወደ ፈረንሳይ ዋና ከተማ በቢዝነስ ክፍል በረራ ሊሳፈር ሲል ከ10 ቀናት በኋላ በሌጎስ ሙርታላ ሞሐመድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዟል።
"ሀገሪቱን ጥሎ ለመውጣት ስለማቀዱ በደረሰን ታማኝ መረጃ መሠረት፣ ሰራተኞቻችን በወሰዱት ቆራጥ እርምእጃ ከሕግ ለማምለጥ ሲሞክር ከአውሮፕላኑ መሳፈሪያ በር ላይ ተይዟል" ሲሉ የብሔራዊ አደንዛዥ ዕፅ ሕግ አስፈፃሚ ኤጀንሲው ኃላፊ ጄኔራል ቡባ ማርዋ ተናግረዋል።
ኤጄንሲው አያይዞም፣ ማይክል ሲያዝ በሦስት ዓይነት ገንዘቦች ማለትም በዩሮ፣ በፓውንድ እና በናይራ ከ12,840 ዶላር በላይ ጥሬ ገንዘብ እንዲሁም "ከሕገ-ወጥ ንግዱ ገቢ ጋር የሚያያዙ" ውድ ጌጣጌጦችን ይዞ እንደነበር ገልጿል።
ኮኬይኑ የተጓጓዘበት የሎጂስቲክስ ኩባንያ ሰራተኛ እንደሆነ የተገለፀ ላዋል ሙጃብ ኬሂንዴ የተባለ ግለሰብም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ግንኙነት እንዳለው ተጠርጥሮ ተይዟል።
የ33 ዓመቱ ወጣት ለውጭ ገበያ የሚዘጋጅ ኮኬይንን በማሸግ በጥሬ ገንዘብ ይከፈለው እንደነበር የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ሌሎች የዚህ አውታረ መረብ አባላት ናቸው ተብለግ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችም በውጭ አገር ባሉ አጋር የሕግ አስከባሪ አካላት መያዛቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።
ቢቢሲ ከዩኬ ባለሥልጣናት አስተያየት ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይገኛል።















