ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነትን ለማረም ፍላጎት እንዳላቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሦት ወራት በፊት የተጀመረውን የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ለመቋጨት የሚያስችለውን ስምምነት ለማስተካከል ፍላጎት እንዳላቸው የዋሽንግተን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ለውጦቹ በሆርሙዝ ወሽመጥ እና የተብላላ የዩራኒየም አወጋገድ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ዋይት ሐውስ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።
የኢራን ዋና ተደራዳሪ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ እሑድ ዕለት የኢራን መብት ሙሉ ለሙሉ እስካልተጠበቀ ድረስ ቴህራን ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም ብለዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም በሚያስችለው ማዕቀፍ ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር አርብ ዕለት ለንግግር ቢቀመጡም፤ ስብሰባው ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ግልፅነት ሳይኖረው ተጠናቋል።
በስምምነቱ ላይ የተሰማው የአሁኑ ለውጥ የማድረግ ፍላጎት በመጀመሪያ አክሲዮስ በተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የተዘገበ ሲሆን፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በ60 ቀናት ማራዘም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም የመክፈት ጥሪ እና በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ድርድር ማድረግ የሚያስችል ማዕቀፎችን ያካትታል።
ስምምነቱ ለኢራን የማዕቀብ እፎይታ ሊሰጥ እንደሚችል የተዘገበ ሲሆን፤ ይህም ቴህራን የተያዘባትን በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ሃብቷን እንድታገኝ ያስችላታል።
ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱን ለማሻሻል ይፈልጋሉ የሚለው ዜና የተሰማው በቴህራን እና ዋሽንግተን መካከል ግጭቱን ማስቆም የሚችል የስምምነት ማዕቀፍ ላይ ለአንድ ቀን ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት 'የመግባቢያ ስምምነት' የተባለ ማዕቀፍ ላይ ሁለቱ አገራት መስማማታቸውን አስታውቀው፤ የፕሬዝዳንቱ እና የኢራን መሪዎች ይሁንታ እየተጠበቀ ነው ብለው ነበር።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ሐሙስ ዕለት ባደረጉት ቃለ ምልልስ "አንድ ማስተማመኛ ማግኘት ያለብኝ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖር ነው። ይህን ተስማምተዋል፤ እናም በጣም አስደሳች ነው" ብለዋል።
ስምምነት ለመፈፀም እንደማይቸኩሉም ትራምፕ ተናግረዋል።
አርብ ዕለም 'በስቺዌሽን ሩም' ትራምፕ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ስብሰባ ከመቀመጣቸው በፊት ስምምነቱን ለመቀበል እያዘነበሉ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከስብሰባው በኋላ ዋይት ሐውስ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ የሚጠቅም እና ቀይ መስመሯቸውን የሚያሟላ ስምምነት ብቻ ነው የሚፈፅሙት። ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ መቼም ሊኖራት አይገባም" ብሏል።
አርብ ዕለት በተደረገው ስብሰባ ትራምፕ ስምምነቱ ላይ በርካታ ማሻሻያዎችን መጠየቃቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።
ከዚህ በኋላ ደግሞ ተጨማሪ ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚፈለጉ ተዘግቧል።
በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት ሲንጋፖር የነበሩት የአሜሪካ የጦር ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚፈልጉትን ስምምነት ኢራን ካልፈፀመች ጥቃቶች ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢራን ባለሥልጣናት ዋይት ሐውስ በሚያሰስተላልፋቸው መልዕክቶች ላይ ጥርጣሬ አድሮባቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ "ግልፅ ድምዳሜ ላይ ካልደረስን እየተነገረ ያለው ሁሉም ነገር ግምት" ብለዋል።















